ኤነታርዚ ወይም ኤነንታርዚ ከ2153 እስከ 2109 ዓክልበ. ግድም የላጋሽ ከተማ ገዢ ወይም ከንቲባ (ኤንሲ) በሱመር ነበር። 2 ኤናናቱምን ተከተለው፣ ነገር ግን ለአዳብ ንጉሥ ሉጋል-አኔ-ሙንዱ መንግሥት ተገዥ እንደ ነበር ይመስላል። የ2 ኤናናቱም ልጅ ሳይሆን ኤነታርዚ ከቄሳውንት ወገን ነበር፣ በኤንመተና ዘመን የቄሳውንት አለቃ ሆነ። የላጋሽ ኤንሲ ከሆነ በኋላ፣ የመቅደሶች ርስትና የመንግሥት ርስት አንድ አድርጎ በላጋሽ ካለው መሬት ከግማሽ በላይ ነበር። ይህንን ለራሱ ወዳጆች ሰጥቶ፣ ከቀደሙት ቄሶች ብዙ ከማዕረጋቸው አስወጣ። ግብርንና ቀረጥንም ከፍ አደረገ። ከላጋሽም ሰዎች ብዙዎች ተከሠሩ በዕዳም ተያዙ።

መቅደሶቹ በላጋሽ ግዛት ሓይለኛ ሆነው ወታደራዊ ተግባር ደግሞ እንደ ነበራቸው ይመስላል። የአንዱ መቅደስ አለቃ ለኤነታርዚ የጻፈው ደብዳቤ በጽላት ተገኝቷል። ደብዳቤውም እንዲህ ይላል፦

«ሉኤና፣ የመቅደሱ አለቃ፣ ምርኮ ከላጋሽ ወደ ኤላም ከሰረቁ ከ600 ኤላማውያን ጋር ተዋጋ። ኤላማውያንንም አሸነፋቸውና ከነሱ 560 ማረካቸው። በኤኒንማር አሉ። ከነርሱ አምስት የንጹሕ ብር ዕቃዎች፣ 25 ንጉሣዊ ልብስ፣ 15 ቆዳዎች መለሰ።»

የኤነታርዚ ተከታይ ሉጋላንዳ ደግሞ ከቄሳውንት ወገን የሆነ ከባድ ገዢ ነበር።

ቀዳሚው
2 ኤናናቱም
ላጋሽ ኤንሲ
2153-2109 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
ሉጋላንዳ