ኡላም-ቡርያሽ ከ1463 እስከ 1447 ዓክልበ. ግድም ድረስ የባቢሎን (ካራንዱኒያሽ) ካሣዊ ንጉሥ ነበረ።

የኡላም-ቡርያሽ ዱላ ራስ

1 ቡርና-ቡርያሽ ልጅና የወንድሙ የ3 ካሽቲሊያሽ ተከታይ ነበር። «የቀድመኞች ነገሥታት ዜና መዋዕል» (ABC 20) በተባለው ሰነድ እንዲህ ይላል፦

ኤዓ-ጋሚል፣ የባሕር ምድር ንጉሥ፣ ወደ ኤላም ሸሸ።
ከሄደ በኋላ፣ ኡላም-ቡርያሽ፣ የካሽቲሊያሽ ወንድም፣ ካሣዊው፣
ሥራዊትን ሰብስቦ የባሕር ምድርን ያዘ። የሐገሩ ጌታ ሆነ።

ሆኖም ከዚህ በኋላ የካሽቲሊያሽ ልጅ 3 አጉም ደግሞ በባሕር ምድር ላይ እንደ ዘመተ ስለሚለን፣ ኹኔታው በሙሉ ግልጽ አይደለም። ኡላም ቡርያሽ በባቢሎን ከወንድሙ ቀጥሎ እና ከአጉም በፊት እንደ ገዛ ይታስባል፤ ሆኖም ከዚህ በቀር የታወቀው በባቢሎን በተገኘ የዳዮሪቴ ዱላ ራስ ላይ በተቀረጸው ጽሑፍ «ኡላም-ቡርያሽ፣ የባሕር ምድር ንጉሥ» ነው። ስለዚህ ምናልባት ኡላም-ቡርያሽ በባቢሎን እንዳልነገሠና አጉም የአባቱን ግዛት ወርሶ በአጎቱ ላይ የዘመተው እንደ ሆነ ይቻላል።

ከዚህ በቀር በአንድ ትልቅ መቃብር በአርሜኒያደብረ አራራት ሸለቆ፣ «፩ ሰቀል፤ ኡላም-ቡርያሽ የቡርና-ቡርያሽ ልጅ» በኩኔይፎርም የሚል የጓጉንቸር ቅርጽ ክብደት ተገኝቷል። ይህ መቃብር ብዙ የሰዎችና የእንስሶች መሥዋዕት ስለነበሩበት የበጣም ትልቅ ሰው መሆን አለበት፤ ካሣውያን እራሳቸው እስከ አርሜኒያ ድረስ እንዳልገዙ እርግጥኛ ነው። የባሕር ምድር ከያዙ በኋላ ከአሦር ጠረፍ ደቡብ በመስጴጦምያ ያለውን ሁሉ ገዝተው ነበር።

ቀዳሚው
3 ካሽቲሊያሽ
ባቢሎን ንጉሥ
1463-1447 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
3 አጉም