አሌ ሆይ አላሌ ሆይ

ልጆች እግራቸውን ዘርግተው በመደዳ መሬት /ወለል ላይ ይቀመጣሉ። አጫዋች ወይም ከተጫዋቾቹ አንዱ የግር ጠቋሚ ይሆንና በሚዘመረው አንድ ቃል አንድ እግር ይጠቁማል። በመጨረሻው ቃል የሚጠቆመው እግር ይሰበሰብና ከጨዋታ (ከጥቆማ) ውጪ ይሆናል። ጨዋታው እየተደጋገመ ሁለቱም እግሩ የተጠቆመበት (ቁልቢት ያረፈችበት) ልጅ ከጨዋታው ይወጣል። እንዲህ እየተባለ አንድ ልጅ እስኪቀርና አሸናፊ እስኪሆን ጨዋታው ይቀጥላል።

አሌ ሆይ አላሌ ሆይ
ገረዴን አያችሁ ወይ
ገረዴን ማርያም ስማ
በርኩማ አሸክማ
በርኩማ የዳገቴ
የሸማ ቅዳዶቴ
ቀድጄ ቀዳድጄ
ሰጠኋት ላበልጄ
አበልጅ ብትወደኝ
ጨረቃ ሳመችኝ
ጨረቃ ድንቡል ቦቃ
አጤ ቤት ገባች አውቃ
አጤ ቤት ያሉ ልጆች
ፈተጉ ፈታተጉ
በቁልቢት አስቀመጡ
ቁልቢት
ስንዴ ቆሎ
ዳቦ ቆሎ
ይችን ትተሽ
ይቺን አንሺ ቶሎ

አሌሆይ .......... አንድ እግር ይጠቆማል
አላሌሆይ ........ ሁለተኛ እገር ይጠቆማል ..
ገረዴን ..............3ኛ እግር
አያችሁ ወይ ....4ኛ እግር .....እንዲህ እያለ ይቀጥላል

ይችን አንሺ ቶሎ ተብሎ የተጠቆመው እግር ይሰበሰባል፤ የተሰበሰበው እግር ከጨዋታ ውጪ ነው አይጠቆምም።

ጨዋታው ይደገማል ። ጨዋታው ከወጣው እግር ቀጥሎ ባለው እግር እንደገና ይጀምራል ። ሁለቱም እግሮቹ የተጠቆሙበት ከጨዋታ ይወጣል ። ሁሉ ወጥተው አንድ አሸናፊ ልጅ ብቻ እስከሚቀር ይቀጥላል ። ልጆቹ ግጥሙን አውቀው ሁሉም ባንድ ላይ ሲሉት ደማቅ ጨዋታ ይወጣዋል ። አዘማመሩ እንደ « -ግዕዝ ሁ -ካዕብ» አባባል ዜማ ነው