ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ

የቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አዲስ አበባ ላይ በ ፲፱፻፹፫ ዓ/ም የቅድስት ማርያም የቋንቋ ትምህርት ቤት በመባል የተመሠረተ የግል የትምህርት ተቋም ነው።

ይኸው የቋንቋ ትምህርት ቤት የተማሪዎቹን የእንግሊዝኛቋንቋ ልምምድ እና ችሎታ በማዳበር የላቀ ሥራው ውጤቶች፣ በተመሠረተ በአራት ዓመት ውስጥ ተሻሽሎ የከተማዋ ዋና የቋንቋ ማዕከል ለመሆን በቅቷል። በ፲፱፻፺ ዓ/ም ላይ ድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤቱን አዋሳ ላይ አድርጎ አዲስ አበባ ላይ በአንድ ቅርንጫፍ በመወከል የቅድስት ማርያም ኮሌጅ ተባለ። በዚሁ ዓመት ኮሌጁ አዋሳ ላይ ፴፫ ተማሪዎችን እና አዲስ አበባ ፴፯ ተማሪዎችን መዝግቦ በ ሒሳብ ጥናት (Accounting)፤ ግብይት ጥናት (Marketing) እና የህግ ጥናት (Law) ማሰልጠን ጀመረ። ወዲያውም ከአዋሳ በ ፺ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዲላ ከተማ ላይ በተመሠረተው ቅርንጫፍ ፵፱ ተማሪዎችን ማስተማር ጀመረ። በዓመቱ መጨረሻ ላይ አዲስ አበባ፣ (ከልደታው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፊት ለፊት) በሚገኘው ቅርንጫፍ፣ ፫፻ ተማሪዎች እና በዲላው ቅርንጫፍ ፳፭ ተማሪዎችን አስመዝግቧል።

፲፱፻፺፩ ዓ/ም ላይ ዋና መሥሪያ ቤቱን ወደአዲስ አበባ አዛውሮ ሲሠራ ከቆየ በኋላ በመስከረም ወር ፲፱፻፺፫ ዓ/ም፤ በወቅቱ በዲፕሎማ የተጀመረውን የ ሥነ-መቀምር (Computer Science) እና የዲግሪ ህግ ትምህርት መስጠት ጀመረ። በየካቲት ወር ላይ የንግድ እና የህግ ትምህርቶችን በርቀት (Distance Education) መስጠትንም ጀመረ። በርቀት ትምህርት ኮሌጁ በአማርኛ ቋንቋ ትምህርትና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት እንዲሁም በሒሣብ ትምህርት፤ በመልክዓ ምድር እና በታሪክ ትምህርቶች የአስተማሪ ሥልጠና በመስጠት እየተሻሻለና እየዳበረ መጥቷል።

ኮሌጁ፣ ከጊዜ ጋር እይተጠናከረ እና እየዳበረ ቆይቶ በመስከረም ፲፱፻፺፭ ዓ/ም ላይ አዲስ መምህራንን በመቅጠር እና ማይጨው አደባባይ ላይ ከዋቢ ሸበሌ ሆቴል አጠገብ የሚገኘውን ሕንፃ ተከራይቶ አሁን ዋና መሥሪያ ቤቱ ወደሚገኝበት ወደዚሁ ሕንፃ አዛወረ። በትምህርትም ረገድ የግብይት ጥናት (Marketing)፣ አስተዳደር ጥናት (Management)፤ ሒሳብ ጥናት (Accounting) እና የአስተማሪ ሥልጠናዎች በዚህ ዓመት ወደዲግሪ ሲያድጉ በሚቀጥለው ዓመት የሥነ-መቀምር (Computer Science) ጥናትም ወደዲግሪ አድጓል። አውደ ትምህርቶችንም በማስፋፋት የባዮሎጂ(Biology)፤ ኬሚስትሪ(Chemistry) እና ፊዚክስ(Physic) ጥናቶችን ያካተተ የተፈጥሮ ሳይንስ ማዕከል ተጨምሯል።

እንደዚህ እያለ በማደግ በነሐሴ ወር ፲፱፻፺፯ ዓ/ም ኮሌጁ ፲፭ሺ የሩቅ ትምህርት ተከታታዮች እና ፭ሺ መደበኛ ተማሪዎችን ያካተተ የትምህርት ተቋም ለመሆን በቃ። በየካቲት ወር ፲፱፻፺፰ ዓ/ም ኮሌጁ ወደአውደ ምህር ደረጃ አድጎ በዚሁ ዓመት በሕንድ አገር ከሚገኘው የ’ኢንዲራ ጋንዲ ብሔራዊ ክፍት አውደ ምህር (The Indira Gandhi National Open University - IGNOU) ጋር በመቀናጀት የ’ማስተሬት ዲግሪ’ ትምህርትን መስጠት ጀመረ።

የቅድስት ማርያም ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የቋንቋ ትምርት ቤት ሆኖ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በሀያ አንድ የአገልግሎት ዓመታት ውስጥ በመዳበር በአሁኑ ጊዜ ወደ ፴ሺ የሚጠጉ ተማሪዎችን በርቀት ትምህርት በ ፳፪ የዲግሪ አውደ ትምህርቶች እና ከ፮ሺ በላይ ለሆኑ መደበኛ ተማሪዎች በ ፲፩ የዲግሪ አውደ ትምህርቶች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። ዓመታዊ፣ ብሔራዊ የምርምር ሥራዎችን በመደጎምና አውደ ጥናቶችን በማካሔድ ለኢትዮጵያ ትምህርት እና ለምርምር እድገት ጉልህ እገዛ እያደረገ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ቅድስት ማርያም ዩንቨርስቲ ኮሌጅ በየዓመቱ የሚያዘጋጃቸው አውደ ጥናቶች በግል የከፍተኛ ትምህርት እድገት ላይ ያነጣጠሩ ሲሆኑ፤ በተጨማሪም የተማሪዎች ምርምር መድረክን በማመቻቸት የመጀመሪያው ነው፡፡

ተጨማሪ ንባብ ለማስተካከል

ዋቢ ምንጮች ለማስተካከል