ጎልጎታአዲስ ኪዳን ወንጌሎች መሰረት በኢየሩሳሌም አካባቢ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ቦታ ስም ነው። ይህ ቦታ በዮሐንስ 19፡20 «ለከተማ ቅርብ ነበረ» ሲባል እንዲሁም በዕብራውያን 13፡12 «ከበር ውጭ» መሆኑን ይመሰክራል።

በአራቱ ወንጌሎች ሁሉ ስለ ስፍራው ተመሳሳይ ታሪክ አለ፦

  • ማቴዎስ 27፡33፦ ትርጓሜው የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሆን ጎልጎታ ወደሚባለው ስፍራ በደረሱ ጊዜም፥
  • ማርቆስ 15፡22፦ ትርጓሜውም የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሆን ጎልጎታ ወደ ተባለ ስፍራ ወሰዱት።
  • ሉቃስ 23፡33፦ ቀራንዮም ወደሚባል ስፍራ በደረሱ ጊዜ፥ በዚያ እርሱን ክፉ አድራጊዎቹንም አንዱን በቀኝ ሁለተኛውንም በግራ ሰቀሉ።
  • ዮሐንስ 19፡17፦ ኢየሱስንም ይዘው ወሰዱት፤ መስቀሉንም ተሸክሞ በዕብራይስጥ ጎልጎታ ወደ ተባለው የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሉት ወጣ።

ሉቃስ ወንጌል ያለው ስም ቀራንዮምግሪኩ ቃል Κρανίον /ክራኒዮን/ (የራስ ቅል) ደረሰ። ነገር ግን «ጎልጎታ» (Γολγοθα) የሚለው ስም ዕብራይስጥ ሳይሆን የአራማያ ቃል גלגלתא /ጉልጋልታእ/ (የራስ ቅል) ይመስላል።

አዲስ ኪዳን ከኢየሩሳሌም በር ውጭ እንደ ነበር ምንም ቢገልጽም፣ በ317 ዓ.ም. የሮሜ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ቅድስት ሄሌና ወደ ከተማው ሄዳ፣ የዛኔ በከተማው ውስጥ የአረመኔ ጣኦት ቤተ መቅደስ በሆነበት ስፍራ ጎልጎታን እንዳገኘች ገመተች። ከዚያ ጀምሮ ሄሌና ያገኘችው ኮረብታ እንደ «ጎልጎታ» ሆኖ ከብሯል። ይህ ቦታ ከደብረ ጽዮን (ከሰሎሞን ቤተ መቅደስ) ወደ ምዕራብ ቢገኝ፣ በዚያ ዘመን የኖረው ክርስቲያን ጸሐፊ አውሳብዮስ ግን ጎልጎታ ከደብረ ጽዮን ወደ ስሜን ይገኛል ብሎ ጻፈ።[1] ስለዚህ ሄሌና ያመለከተችው ኮረብታ በእውኑ ጎልጎታ መሆኑ አጠያያቂ ሆኗል።

ከዚህ በላይ ከኢየሩሳሌም በር ውጭ ወደ ስሜን በኩል ሌላ ኮረብታ «የራስ ቅል ኮረብታ» ይባላል፤ ይህም ኮረብታ የጭንቅላት ቅርጽ አለው። ስለዚህ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ያው ወደ ስሜን የሚሆነው ኮረብታ በእውነት ጎልጎታ ነው ያሚያስቡ ጥቂቶች አይደሉም።

በአንዳንድ ጥንታዊ መጻሕፍት ልማድ ዘንድ[2]ሴምመልከ ጼዴቅ ወደ አራራት ሔደው የአዳምን ሬሳ ከኖህ መርከብ አወጡት። ከዚያ በሗላ፣ በመላዕክት ዕርዳታ ወደ ኢየሩስሌም ዞረው በጎልጎታ ኮረብታ ውስጥ አቀበሩት። በዚሁ ልማድ፣ ይህ ኮረብታ በአለም መካከል እንደሚቀመጥ ይባላል። በተጨማሪ፣ እግዚአብሔር አዳምንና ሕይዋንን ከኤደን ገነት ከጣላቸው በኋላ፣ የእባቡን ራስ ጨመቀውና በዚያው ኮረብታ ውስጥ ደግሞ እንደሚገኝ ይባላል።

  1. ^ አውሳብዮስ፣ ኦኖማስቲኮን 365.
  2. ^ የቅሌምንጦስ ጽሑፎች፤ የአዳምና ሕይዋን ታሪክ፣ የመዝገቦች ዋሻ፣ ወዘተ.