ሲሉራውያን በደቡባዊ ዌልስ ቢያንስ ከ30 ዓክልበ. ግድም ጀምሮ የተገኘ የብሪቶናውያን (ኬልቲክ) ነገድ ነበሩ።

ኬልቲክ ነገዶች በዌልስ ከሮማውያን በፊት

የሮማ ታሪክ ጸሐፊ ታኪቱስ በ90 ዓም እንደ ጻፈው፣ ሲሉራውያን ጥቁር ጥቅል ጽጉር ስላላቸው ትውልዳቸው ከእስጳንያ እንደ ደረሰ መሰለው። ወደ ስሜኑ በካሌዶኒያ (ስኮትላንድ) የነበሩ ኬልቶች ግን ስለ ቀይ ጽጉራቸው ይታወቁ ነበር።

ሮማውያን ከ35 ዓም ጀምሮ ታላቅ ብሪታንያን ደሴት ከደቡብ ወረሩ፤ ብዙ ብሔሮችም ተሸንፈው ወደ ሮሜ መንግሥት አስተዳደር ተጨመሩ። ሲሉራውያን ግን በትጋት ታግለው እስከ 66 ዓም ተከላከሏቸው።

ከዚያ በኋላ ዌልስ ደግሞ ለሮሜ አስተዳደር ተጨመረች፣ ሆኖም የሲሉራያን ንጉሦች እስከ 172 ዓም ድረስ እንደ ሮሜ ደንበኛ-ንጉሦችና የብሪቶናውያን ከፍተኛ ነገሥታት እንደ ተቆጠሩ ይታስባል። በትውፊት ዘንድ እንደ ታወቀው፣ መጨረሻው ንጉሣቸው ሉኪዮስ (146-172 ዓም?) በ170 ዓም ግድም ለሮሜ ፓፓኤሌውጤሪዩስ ጽፈው በክርስትና እንዲጠመቁ ለመኑዋቸው። ሰባኪዎችም ከሮሜ ተላኩና ከዚህ ሰዓት ያሕል (170 ዓም) ጀምሮ ብሪቶናውያን ክርስትናን እንደ ተቀበሉ ይመስላል። በአንድ ቤተክርስቲያን በለንደን (ቅዱስ ጴጥሮስ በኮርንሂል) ውስጥ በተቀረጸ ጽሑፍ፣ ሕንጻው በንጉሥ ሉኪዮስ በ171 ዓም እንደ ተመሠረተ ይላል።

የሉኪዮስ ታሪክ በጽሕፈት መጀመርያው የተገኘው ከ6ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሲሆን፣ ብዙ የዛሬው መምኅሮች ልማዱ እንደ ተሳተ ያምናሉ። ሆኖም ክርስትና ወደ ታላቅ ብሪታኒያ በሰፊው የገባው በ2ኛው ክፍለ ዘመን በውነት እንደ ነበር በሥነ ቅርስ ይስማማል። የሉኪዮስ ሕልውናና ጥምቀት ታሪክ ትክክል ከሆነ፣ ሲሉራውያንና ብሪቶናውያን ከኦስሮኤኔ (በስሜን መስጴጦምያ) ጋር ለመጀመርያው ክርስቲያን መንግሥት ቅድምትነት ይግባኝ ማለት አላቸው።