የራዲዮ ሞገዶች ልክ እንደ ብርሃን እና ኤክስሬይኤሌክትሮመግነጢስ ማዕበል አካል ናቸው። ልዩነታቸው ሞገዳቸው በጣም ረጅም መሆኑ ነው።

በዓይን የሚታየው ብርሃን የሞገድ ርዝመት ከሰው ልጅ ፀጉር እጅግ የሚያንስ፣ ከማይክሮ ሜትር በታች የሆነ ጥቃቅን ነው። የራዲዮ ሞገድ በአንጻሩ ሞገዱ በሴንቲሜትርና በሜትር የሚለካ ሲሆን በአይን ግን አይታይም።

የራዲዮ ሞገድ ተቀባይ አንቴናወች ሲተለሙ ለሚቀበሉት ሞገድ ርዝመት ተመሳሳይ ቁመት እንዲኖራቸው ተደርጎ ነው። ለዚህ ነው የራዲዮ አንቴናወች ረጅም የሆኑት። ርዝመታቸው ከሚቀበሉት ሞገድ አንጻር አጭር የሆኑ አንቴናወች ሞገድ የመቀባልቸው ሃይል የተዳከመ ነው።

ሰው ሰራሽ የራዲዮ ሞገዶች መረጃን ለመለዋወጥና ዜና ለማሰራጨት ሲያገለግሉ ከ100 አመት በላይ አስቆጥረዋል። ራዲዮን፣ ቴሌቪዥንሳተላይቶችየዕጅ ስልኮች ወዘተ መረጃን የሚያሰራጩትና የሚቀበሉት እኒህን ሞገዶች በመጠቀም ነው።

ከዚህ በተጨማሪ የራዲዮ ሞገዶች ነገሮችን "ለማየት"ም ሲያገለግሉ ይታያሉ። ራዳር ከኒህ ወገን ሲሆን የሚሰራውም የራዲዮ ሞገዶችን ርቀው ወዳሉ ነገሮች በመላክ ነጥረው ሲመለሱ የሚወስዱትን ሰዓት በመለካት ሩቅ ያሉ ነገሮችን "ለማየት" ይረዳል። በተረፈ ራዳር መሬት ውስጥ ተቀብሮ ያለን ቤንዚን መርምሮ ለማግኘት፣ የአፈርን ኬሚካላዊ ባህርይ ለማወቅ ይረዳል።

ራዲዮ ሞገዶች ሰው ሰራሽ ብቻ ሳይሆኑ፣ በተፈጥሮም ይገኛሉ።