ሥነ ባህርይጄኔቲክስ ወይም ሥነ በራሂ ማለት የበራሂዎች ጥናት ነው።

ጄነቲክስ የሚለዉ የጉዳይ ስነ ባህርይ የሚለው ትርጉም አይወክለዉም፤ ስነ ባህሪ ማለት በቀጥተኛ ትርጉሙ የባህሪ- ጥበብ ማለት ነው። ጄነቲክስ፡ ማለት ግን፤ የዘር-ውርስ ማለት ነው።

ሥነ ባሕርይ እንዲህ ይሠራል፦

ሰውነታችን እንዲሁም የሕያዋን ሁሉ ሁለንተኖች ከብዙ ህዋስ ይሠራል። እያንዳንዱም ህዋስ የዚያው ፍጡር መለያ በራሂያዊ ኮድ በዲ ኤን ኤ ሞለኩሎች ይሸክማል። የሕያዋን ህዋሶች ሁሉ እንስሳትም ሆነ እፅዋት ለየራሳቸው ይህን መለያ ኮድ መሸከማቸው አስገራሚ ሁኔታ ነው።

በዚህም ዲ ኤን ኤ ውስጥ አንዳንድ ሐብለ በራሂ ሞለኩሎች አሉ። ቁጥሩም በየዝርያው ይለያያል፣ ለምሳሌ ለሰው ልጅ በጠቅላላ 23 (46) ሐብለ በራሂዎች አሉ፤ ለጦጣ ግን 24 (48) አሉ።

እያንዳንዱም ሐብለ በራሂ እጅግ ብዙ በራሂዎች አሉበት። የነዚህ በራሂዎች ቀደም-ተከተል እንደ መለያ-ቁጥር ከማገልገሉ በላይ፣ በራሂዎቹ ፕሮቲኖችን በማሠልጠናቸው ልዩ ከሃሊነቶች አሉዋቸው። ይህም በሥነ በራሂ ጥናት አሁን እየተፈታ ነው።

በራሂዎቹ የሰውነቱን ባሕርይ የሚሰጡት ክፍሎች ስለ ሆኑ «ሥነ ባሕርይ» ተብሏል። እያንዳንዱም በራሂ ከሁለት ቅንጅበራሂዎች ይሠራል። ከነዚህ አንዱ ቅንጅበራሂ ከአባት፣ አንዱም ከእናት በአራያው ሲፀነስ ይወረሳል።

አንዳንድ ቅንጅበራሂ ጎልባች፣ አንዳንድ ተጎልባች ይባላል። የአንዱ በራሂ ሁለት ቅንጅበራሂዎች (ከእናትና ከአባት) ሁለቱ ተጎልባች ከሆኑ፣ የሰውነትን ባሕርይ ሊቀይር ይችላል።

ምሳሌ፦ አንድ አባትና እናት ሁለቱ ቡናማ ቀለም ዓይን አላቸው። በሁለቱ በራሂያዊ ኮድ ግን፣ የ«አይን ቀለም» የሚያስተዳደረው በራሂ ውስጥ አንድ ተጎልባች ቅንጅበራሂ እና አንድ ጎልባች ቅንጅበራሂ አሉዋቸው። ጎልባቹ ቅንጅበራሂ ለአይናቸው ቡናማ ቀለም ይሰጣል። ለዚሁ በራሂ፣ ልጆቻቸው በአራት አይነቶች ሊሆኑ ይችላሉ፦

  1. የእናት ተጎልባች ቅንጅበራሂ እና የአባት ጎልባች ቅንጅበራሂ የወረሰው ቡናማ አይን አለው።
  2. የእናት ተጎልባች ቅንጅበራሂ እና የአባት ተጎልባች ቅንጅበራሂ የወረሰው ሰማያዊ አይን አለው። ጎልባቹንም ቅንጅበራሂ አይሸክምም።
  3. የእናት ጎልባች ቅንጅበራሂ እና የአባት ጎልባች ቅንጅበራሂ የወረሰው ቡናማ አይን አለው። ተጎልባቹንም ቅንጅበራሂ አይሸክምም።
  4. የእናት ጎልባች ቅንጅበራሂ እና የአባት ተጎልባች ቅንጅበራሂ የወረሰው ቡናማ አይን አለው።

ስለዚህ ከልጆቻቸው ሁሉ በምናልባትነት ለ25% (1/4) ሰማያዊ አይን ይኖራቸዋል፤ ለ75% ቡናማ አይን ይኖራቸዋል ለማለት እንችላለን።

በሌላው ትዳር፣ አባትና እናት ሁለቱ ሰማያዊ አይን ቢኖራቸው ኖሮ፣ ጎልባቹ ቅንጅበራሂ አይገኝባቸውም ማለት ነውና ልጆቻቸውም ሁሉ ሰማያዊ አይን እንደሚኖራቸው ማወቅ እንችላለን። ይህ በጣም ቀላል የሆነ ምሳሌ ነው፤ እንዲያውም ብዙ አይነት ባሕርዮች በአንድ በራሂ ሳይሆን በበርካታ በራሂዎች ሊገዙ ይችላሉ።