ሥርዓተ ነጥቦች
አማርኛ ፦ ሥርዓተ ነጥቦች
በጽሑፍ ላይ የሰፈረ ሐሳብ (ቋንቋ) መልእክቱ ሳያሻማ ግልጽ ሆኖ እንዲተላለፍ ሥርዓተ - ነጥቦች የጎላ ድርሻ አላቸው። በጽሑፍ ላይ ነጥቦችን አስተካክሎ ካለመጠቀም የተነሳ ዐረፍተ ነገሮችን ያሻማሉ፤ መልእክቶች ይዛባሉ፤ ሐሳቦች ይድበሰበሳሉ። ስለዚህ ሐሳቦችን ግልጽ በሆነ መልኩ በጽሑፍ ለማስተላለፍም ሆነ የተጻፈውን መልእክት በትክክል አንብቦ ለመረዳት ሥርዓተ - ነጥቦችን እና አገልግሎታቸውን በሚገባ ማወቅ ተገቢ ይሆናል።
ብዙዎቻችን ከሁለት ነጥብና ከአራት ነጥብ በስተቀር ሌሎቹን ሥርዓተ - ነጥቦች በሚገባ አንጠቀምም። ለምሣሌ አንዱ ድርብ ሠረዝ (፤) የሚጠቀምበትን ቦታ ሌላው ነጠላ ሠረዝ (፣)/(፥) ይጠቀማል፤ እንዲሁም አንዱ ትእምርተ - ጥያቄ (?) የሚጠቀምበትን ቦታ ሌላው ትእምርተ - አንክሮን (!) ይጠቀማል። ወጥ የሆነ የአጠቃቀም ስርዓት አይታይም። በርግጥ አንዳንዴ ድርብ ሠረዝን መጠቀም አለመጠቀም የምርጫ ጉዳይ ሊሆን ይችላል። ሐሳቦች ተደራርበው ወይም ተጣምረው እንዲቀርቡ የፈለገ ሰው ድርብ ሠረዝን ተጠቅሞ ሐሳቦቹን በአንድ ዐረፍተ ነገር ሊያጠቃልል ይችላል። በአንጻሩ ደግሞ ሐሳቦቹን ቆራርጦ የተለያዩ ዐረፍተ ነገሮች በማድረግ ለየብቻቸው ሊያቀርብ የፈለገ ሰው አራት ነጥብን መጠቀም ይችላል። ዞሮ ዞሮ የሥርዓተ - ነጥቦችን አጠቃቀም ማወቅ ተገቢ ነው።
በአሁኑ ጊዜ በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኙት ሥርዓተ - ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው።
(1) አንድ ነጥብ (.)
ለማስተካከልአንድ ነጥብ (.) በግእዝ ነቁጥ ይባላላል። በአማርኛ ደግሞ <<ይዘት>> ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በሦስት የተለያየ መልክ ያገለግላል፡፡
1.1 ቃላትን በምህፃረ - ቃል አሳጥሮ ለመጻፍ የሚያገለግል ሲሆን ሁለት የተለያዩ ሥርዓቶችን ይከተላል።
ሀ. የቃላትን መነሻ ፊደል ብቻ በመውሰድ
ምሳሌ፡ [የ]ተ. መ. ድ. = የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት
ለ. የአንድን ቃል መነሻና መድረሻ ሆሄ ብቻ በመውሰድ
ምሳሌ፡ ወ•ሮ ወይዘሮ
1.2 ብርና ሳንቲሞችን እንዲሁም ሙሉና ክፍልፋይ ቁጥሮችን ለመለየት
ምሳሌ፡ 9.50 = ዘጠኝ ብር ከሃምሣ ሳንቲም 1.90 = አንድ ነጥብ ዘጠኝ
1.3 መለያ ቁጥሮችን ወይም ሆሄያትን ከዋናው ሐሳለመለየት
ምሳሌ፡ 1. እግዚአብሔርን መፍራት
2. እናት እና አባትን ማክበር
ሀ. እግዚአብሔርን መውደድ
ለ. ሰዎችን መውደድ
(2) ሁለት ነጥብ (፡)
ለማስተካከል2.1 ቃላት በእጅ ጽሕፈት ላይ ከመጠን በላይ ተቀራርበው ስናነብ እንዳያስቸግረን ወይም ፊደላት ከቃል ክፍላቸው ርቀው ወደ ሌላኛው ቃል በመጠጋት እንዳያደናግሩን በቃላት መካከል በመግባት ድንበር በመሆን ያገለግላል።
ምሳሌ አበበ፡በሶ፡በላ፡፡
ይህ ነጥብ ቃልን ከቃል በመለየት ተግባሩ በኩል በዘመናዊ የመቀምር (computer) ጽሑፍ ላይ ቦታ የለውም። ምክንያቱም ቃል ከቃል የመለየቱ ሥራ ህዋር (space) በመስጠት ይከናወናል።
ነገር ግን
2.2 ሰዓትንና ደቂቃን ከመለየት ተግባሩ አንጻር ካየን በእጅ ጽሕፈት ላይ ብቻ ሳይሆን በመቀመር ጽሁፍም ላይ ያገለግላል።
ምሳሌ 1፡30
ይህ የስርዐተ-ነጥብ አይነት በአሁኑ ጊዜ ስዎች ፅሁፍ ሲፅፋ ቃል ለመለየት አይጠቀሙበትም።
(3) ሁለት ነጥብ ከሠረዝ (፦)
ለማስተካከል3.1 ይህ ሥርዓተ - ነጥብ መሪ ሐሳቡን ተከትለው ወደሚመጡ ዝርዝር ነገሮች ለማንደርደር ያገለግላል።
ምሳሌ፡ ቋንቋ አራት ዘርፎች አሉት። እነሱም ፦ ማዳመጥ፣ መናገር፣ ማንበብና መጻፍ ናቸው።
(4) ነጠላ ሠረዝ (፣) , (፥)
ለማስተካከልይህ ሥርዓተ - ነጥብ የተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚያገለግል ሲሆን ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው።
4.1 ተመሳሳይ ሙያ ያላቸውን ተከታታይ ቃላት ለመለየት
ምሳሌ፡ ድርጅታችን ጨው፣ ስኳር፣ ጥራጥሬ፣ ዱቄትና ዘይት ያከፋፍላል።
4.2 የባለቤት ተጣማሪ ለማቅረብ ወይም ማብራሪያ ለመስጠት
ምሳሌ፡ አቶ ገመቹ፣ ጠንካራው ገበሬ፣ ዛሬ ተሸለሙ።
4.3 በንግግር ላይ የተንጠለጠልን ሐረግ ከሌላናው ለመለየት
ምሳሌ፡ አባቱን ፈርቶ፥ ምንም ሳይናገር ወጣ።
4.4 ከአያያዥ መስተጻምሮች በኋላ
ምሳሌ፡ ሲገባ እንጂ፣ ሲወጣ አላየሁም።
4.5 በተከታታይ የሚመጡ ንዑስ ሐረጎችን ለመለየት።
ምሳሌ፡ ወረቀት ከዓለማየሁ፣ እርሳስ ከዘውዴ፣ ላጲስ ከጥሩወርቅ ተበድሮ ሒሳቡን ሠራ።
4.6 ዐረፍተ ነገር እንዳያሻማ የንባብ ቆምታ መደረግ እንዳለበት ለማመልከት
ምሳሌ፡ ለመኖር፥ ሰው፥ መብላት አለበት።
4.7 ስም ጥሪን ወይም ተናጋሪ ገፀ - ባሕሪያትን ለማመልከት
ምሳሌ፡ <<ዘነበ ፣ ለምን በርትተን አናጠናም>> አለና … <<ቶሎ ወደቤት መሄድ አለብሽ!>> አለ ንጉሤ፣ ዓይኑን አፍጥጦ።
4.8 ምዕራፍና ቁጥርን ለመለየት
ምሳሌ፡ ማቴዎስ 4 ፥ 12
4.9 በግጥም የቤት መምቻ ስንኞች መጨረሻ
ምሳሌ፡ ወንድ ልጅ ተወልዶ ካልሆነ እንዳባቱ ፣ አመልማሎ ስጡት ይፍተል እንደናቱ።
4.10 የግለሰብን ስምና አድራሻ በተከታታይ ለማመልከት
ምሳሌ፡ ታምሩ ተገኝ ፣ የሰሜን ሸዋ ጤና ማዕከል ፣ ፖ. ሣ. ቁ. 44259 ፣ ኮረማሽ።
(5) ድርብ ሠረዝ (፤)
ለማስተካከል5.1 ድርብ ሠረዝ፣ ድርብ ሐሳቦችን አጣምሮ ለማቅረብ ያገለግላል።
5.2 ሁለት ሐሳቦችን በመስተፃምር አማካይነት አጣምሮ ለማቅረብ
ምሳሌ: ልጁን ደጋግሜ መከርኩት፤ ይሁን እንጂ ሊሰማኝና ሊመለስ አልቻለም።
5.3 ተያያዥነት ያላቸው ሁለትና ከዚያ በላይ ሐሳቦችን በአንድነት፣ አከታትሎ ለማቅረብ
ምሳሌ2፡ ሥራውን በርትቶ ይሠራል ፤ ያገኘውን በደስታ ይበላል ፤ በጊዜ ገብቶ ይተኛል።
5.4 ከፊተኛው ሐሳብ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ዝርዝር ነገሮች አክሎ ለማቅረብ
ምሳሌ3: ለዕድገትና ለጥንካሬ የሚከተሉት ነገሮች አስፈላጊ ናቸው ፤ ወተት፣ ዕንቁላል፣ ሥጋ፣ አትክልትና ፍራፍሬ።
5.5 በርከት ያሉ ምዕራፎችንና ቁጥሮችን በተከታታይ ለማቅረብ
ምሳሌ4፡ ዮሐ 3 ፥ 5 ፤ 3 ፥ 16 ፤ 3
(6) ሦስት ነጥብ (. . .)
ለማስተካከልሦስት በረድፍ የተቀመጡ ነጠብጣቦችን በሚከተሉት ሁኔታዎች እንጠቀምባቸዋለን።
6.1 ከሌላው ሰው ከተወሰዱት ሐሳቦች ውስጥ የቀሩ ወይም የተዘለሉ መኖራቸውን ለማመልከት
ሀ. አላስፈላጊው መዘለሉን (መቅረቱን) ለማመልከት
ምሳሌ፡ ሰባት ሰዓት ሙሉ … ተጉዘው ኮንሶ እንደገቡ … መኝታ ፍለጋ ተበታተኑ።
ለ. ቃሉን ከፀያፍነቱ ወይም ከሌላ ሁኔታ አንፃር ላለመጥቀስ ቦታውን ክፍት አድርጎ ለማሳየት
ምሳሌ፡ <<የተናቀ … ያስረግዛል>> ይባላል።
6.2 የትንፋሽ መቆራረጥንና የሐሳብ አለመያያዝን ለማመልከት
ሀ. የደስታ ስቃ የያዘው ሰው
ምሳሌ፡ የተደረገ … ልኝን … በቃላት … መግ …ለጥ … አልች … ልም።
ለ. በሐዘን መንፈሱ የተረበሸ ሰው
ምሳሌ፡ ወይኔ … አባ … ቴን … አስገ … ደሉት።
6.3 ተመሳሳይ ነገሮች የሚቀጥሉ መሆናቸውን ለማመልከት። በሌላ አነጋገር ወዘተ. ለማለት ያገለግላል።
ምሳሌ፡ እንደ ወንበር ፣ አልጋ ፣ ጠረጴዛ … የመሳሰሉትን ብዙ ብር አውጥቶ ገዛ።
(7) ትእምርተ ጥቅስ (" ")
ለማስተካከልየጥቅስ ምልክቶችን በሁለት ከፍሎ መመልከት ይቻላል።
7.1. ሙሉ የጥቅስ ምልክት (“ ”)
ይህ ሙሉ የጥቅስ ምልክት በሚከተሉት ሁኔታዎች ሊያገለግል ይችላል።
7.1.1. ጸሐፊው ሐሳቡ ከራሱ የፈለቀ አለመሆኑን ለማመልከት
ምሳሌ፡ “ሥራ ለሠሪው እሾህ ላጣሪው” ሲባል አልሰምህም?
7.1.2. አንዳንድ የተውሶ ቃላት በቋንቋው ውስጥ ሲጻፉ ባዕድነታቸውን ለማመልከት
ምሳሌ፡ የእግሩ ሕመም መንስኤ የ“ነርቭ” መሸማቀቅ ነው።
7.1.3. ፀሐፊው በትርጉማቸው የማያምንባቸውን አባባሎች ለመለየት ሲፈልግ
ምሳሌ፡ እኔን አልሰ4ማ ካልከኝ አክስትህ እንደመከረችህ “የጨዋ ልጅ” ፈልገህ አግባ።
7.1.4. የሁለት ሰዎችን ምልልሳዊ ንግግር ለየብቻ በጥቅስ ቀንብቦ ለማሳየት
ምሳሌ፡ “ዛሬ ትምህርት ቤት ሄደሃል?” “አዎና! ግን ለምን ጠየቅከኝ?” “የትራንስፖርት ችግር ስለነበረ”
7.1.5. ሥርወ ቃልን ለማመልከት፣
ምሳሌ፡ ሕዋር ስ. በረንዳ፣ ወለል፣ ደጀ ሰላም። ሥር. “ሖረ”ን ተመልከት
7.2. ነጠላ የጥቅስ ምልክት (‘ ‘)
ፀሐፊው በጠቀሰው ጥቅስ ውስጥ ሌላ ጥቅስ ካጋጠመው በነጠላ የጥቅስ ምልክት መለየት ይኖርበታል።
ምሳሌ፡ “በርትተን ለመማርና ጥሩ ውጤት ለማምጣት ‘ሁልጊዜ ትጉ’ የሚለውን የመምህራችንን ምክር እናስታውስ” በማለት የክፍል አለቃው ጓደኞቹን መከረ።
(8) ትእምርተ - አንክሮ (የቃለ አጋኖ ምልክት) (!)
ለማስተካከልይህ ምልክት መገረምንና መደነቅን ፣ ግዴታና ትዕዛዝን ፣ ማሞካሸትና ማድነቅን ፣ ቁጣን ፣ ልመናን ፣ ጩኸትና ለቅሶን የመሳሰሉትን ለማመልከት ያገለግላል።
8.1 መገረምና መደነቅ
ምሳሌ፡ ፈተናውን አለፈ እንዴ !
8.2 ትዕዛዝና ግዴታ
ምሳሌ፡ ዛሬ መሄድ አለብህ !
8.3 ማሞካሸትና ማድነቅ
ምሳሌ፡ ጎሽ ! አንጀቴን አራስከው !
8.4 ቁጣ
ምሳሌ፡ ኤጭ ! ወዲያ ሂድልኝ !
8.5 ልመና
ምሳሌ፡ ጌታ ሆይ ! እባክህን ተለመነኝ !
8.6 ጩኸት
ምሳሌ፡ ኡ ኡ ! ድረሱልኝ !
8.7 ለቅሶ
ምሳሌ፡ ወንድሜ ! ወንድሜ !
(9) ትእምርተ - ጥያቄ (የጥያቄ ምልክት) (?)
ለማስተካከል9.1 ለብቻው ሲያገለግል
- ምሳሌ፡ የቤት ሥራህን ሠርተሃል?
9.2ከትእምርተ - አንክሮ ጋር ሲያገለግል
- ምሳሌ፡ አንተ ሰውዬ ትሄዳለህ አትሄድም?
(10) እዝባር (አቆልቋይ) (/)
ለማስተካከልይሄ ምልክት አንዳንዴ ሰፃፍ መስመር ይባላል።
10.1 አንድን ቃል በመጀመሪያውና በመጨረሻው ፊደላት አሳጥሮ ለመጻፍ
ምሳሌ፡ ወ/ሮ = ወይዘሮ ወ/ር = ወታደር
10..2 የጥምር ቃሉን የመጀመሪያ ፊደል ብቻ አሳጥሮ ለመጽአፍ ሲፈለግ
ምሳሌ፡ ት/ቤት = ትምህርት ቤት ጽ/ቤት = ጽሕፈት ቤት ቤ/ክርስቲያን = ቤተ ክርስቲያን
10.3 ተራ ቁጥሮችን ወይም ቅደም ተከተሎችን ቁጥሮች ወይም ሆሄያት ለመለየት
ምሳሌ፡ 1/ ሀ/ 2/ ለ/
10.4 <<ወይም>> የሚለውን ቃል ተክቶ እንዲያገለግል ሲፈለግ
ምሳሌ፡ በዐረፍት ነገር ውስጥ የቃላትን / ሐረጎችን ትርጉም ማጤን ተገቢ ነው።
10.5 የመሥሪያ ቤት ደብዳቤ መለያ ቁጥሮችንና ዓመተ ምኅረትን ለመለየት
ምሳሌ፡ ቁጥር 385/ 31/ 2001
10.6 ተመሳሳይ ፍቺ ያላቸውን ቃላት ለመግለጽ
ምሳሌ፡ ጽሒፍ/ጽሒፎች = መጻፍ ሐቲት/ሐቲቶች = መመርመር ተሐሠየ/ተሐሥየ = ተደሰተ፣ እሰይ አለሇ።
(11) ቅንፍ ( )
ለማስተካከል11.1 <<ወይም>> የሚለውን አማራጭ ቃል ተክቶ እንዲያገለግል ሲፈለግ ምሳሌ፡ ነገ ጧት ወላጅህን (አሳዳጊህን) ይዘህ መምጣት አለብህ።
11.2 የቃላትን ትርጉም ለማመልከት ሲፈለግ ምሳሌ፡ ከቤተ ሰቦቹ የወረሰው ጥሪት (ሀብት ንብረት) አለው።
11.3 ለተባለው / ለተጻፈው ነገር ማብራሪያ ማቅረብ ሲፈለግ ምሳሌ፡ በደሀው ሕብረተ ሰብ ገንዘብ የተማሩ ሰዎች (በተለይም በዩኒቨርሲቲዎችና በኮሌጆች ውስጥ የሚገኙ ምሁራን) ለአገሪቱ እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
ይህ ምልክት በላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ አንድ ሃሳብ / አረፍተ ነገር የተቀነጨበበትን በምዕራፍና በቁጥር የተሸነሸነ ምንጭ ለማመልከትም በስራ ላይ ይውላል። ለምሳሌ የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በሌሎች ፅሑፎች ሲጠቀሱ።
ካስተዋልኳቸው፦
የተጠቀሰው የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍል ለብቻው በተለየ አተያየብ በዋናው ፅሑፍ መካከል ሲቀርብ፥ የተጠቀሰው ክፍል ለብቻው ከተፃፈ በኋላ የተጠቀሰበት ጥቅስ በቅንፍ ውስጥ ይቀመጣል።
ምሳሌ፦ለሰዎች ትታዩ ዘንድ ምጽዋታችሁን በፊታቸው እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፤ያለዚያ በሰማያት ባለው አባታችሁ ዘንድ ዋጋ የላችሁም። እንግዲህ ምጽዋትስታደርግ፥ ግብዞች በሰው ዘንድ ሊከበሩ በምኩራብ በመንገድምእንደሚያደርጉ በፊትህ መለከት አታስነፋ፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። (ማቴዎስ 6፥1-2)
ፀሐፊው በራሱ ቋንቋ የጠቀሰውን ክፍል እያብራራ የሃሳቡ መነሻ ግን ያነበበው መሆኑን ለማሳየት ከዚህ እንደሚከተለው ያመለክታል።
ሰዎች ለጋስ እንዲሏችሁ ልግስናችሁ ያደባባይ አይሁን (ማቴዎስ 6፥1)። አራት ነጥቡ የተቀመጠው ከቅንፉ ውጭ ነው።
የተጠቀሰው ክፍል (አርፍተ ነገር) የሚያልቀው በትእምርተ ጥያቄ ወይም በትእምርተ አንክሮ ከሆነና ፀሐፊው እንዳለ ከጠቀሰው፥ የተጠቀሰው ክፍል በትእምርተ ጥቅስ ውስጥ ከትእምርተ ጥያቄው ወይም ከትእምርተ አንክሮው ጋር ይቀመጣል። ከዚያም የተገኘበት ክፍል በቅንፍ ተቀንብቦ ከተቀመጠ በኋላ በአራት ነጥብ ይዘጋል።
ምሳሌ፦ "ይህችም የአብርሃም ልጅ ሆና ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ ሰይጣን ያሰራት በሰንበት ቀን ከዚህ እስራት ልትፈታ አይገባምን?" (ሉቃስ 13፥16)።
የተጠቀሰው ክፍል (አርፍተ ነገር) የሚያልቀው በአራት ነጥብ ከሆነ፥ የተጠቀሰው ክፍል በትእምርተ ጥቅስ ውስጥ ያለ አራት ነጥብ በትእምርተ ጥቅስ ጥቅስ ውስጥ ይቀመጣል። ከዚያም የተገኘበት ክፍል በቅንፍ ተቀንብቦ ከተቀመጠ በኋላ በአራት ነጥብ ይዘጋል።
ምሳሌ፦ "ለእውነት እየታዘዛችሁ ግብዝነት ለሌለበት ለወንድማማች መዋደድ ነፍሳችሁን አንጽታችሁ እርስ በርሳችሁ ከልባችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ" (1ኛ ጴጥሮስ 1፥22)።
(12) ሠረዝ (ጭረት) ( - )
ለማስተካከልሠረዞችን ንዑስና ዐቢይ በማለት በሁለት ይከፈላሉ።
12.1 ንዑስ ሠረዝ (-)
ሀ/ ጥምር ቃላትን ለማመልከት
ምሳሌ፡ ቃለ - ጉባዔ ሰው -ሠራሽ
ለ/ ዝርዝር ነጥቦችን ለየብቻ ለማሳየት
ምሳሌ፡ የቋንቋ ትምህርት ዋነኛ ዓላማዎች፦-ጥሩ አዳማጭ-ጥሩ ተናጋሪ-ጥሩ አንባቢ-ጥሩ ፀሐፊ መሆን ነው።
12.2 ዐቢይ ሠረዝ (—)
ይህ ሠረዝ <<እስከ>> የሚለውን ትርጉም ይዞ የተላለፈ ነው።
ምሳሌ፡ ከአዲስ አበባ — ሰበታ በእግሬ ተጓዝኩ።
ነገ ፣ ከ 3 — 4 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ አደርሳለሁ።
(13) ዕሩይ (=)
ለማስተካከል13.1 ዕሩይ ወይም ተመሳሳይ መሆንን ያመለክታል።
ምሳሌ፡ አረፈ = ሞተ 3 + 4 = 7
(14) ረድፍ (*)ወይም የኮከብ ምልክት
ለማስተካከል14 .1 የግርጌ መግለጫ ለማቅረብ - ለአንድ ቃል፣ ሐረግ፣ ዐረፍተ ነገር ወይም ሐሳብ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ወይም ማጣቀሻ በህዳግ ላይ ለመስጠት የምንጠቀምበት ምልክት ነው። ብዙ የግርጌ ማስታወሻዎች ሲኖሩ ግን በቁጥር ይተካል። ምሳሌ፡ ግእዝ* ፊደል በኦሮምኛ ውስጥ የለም፡
14.2 የአማርኛ የመጀመሪያ ፊደላት (በ ፣ ሰ ፣ ሸ …)
14.3 የተጀመረውን ሐሳብ ቆም አድርጎ ወደ ሌላ ሐሳብ መሸጋገርን ለማመልከት በአንድ ረድፍ ሁለት ወይም ሦስት በመሆን ይታያሉ። (* * *)
(15) አራት ነጥብ (።)
ለማስተካከል15.1 አራት ነጥብ እርግጠኛና ቀጥተኛ የሆኑ ጉዳዮች በዐርፍተ - ነገር ተጽፈው ሙሉ ዕረፍት ሲደረግና ሐሳቡም ሲቋጭ መደምደሚያ ሆኖ ይገባል።
ምሳሌ፡ አስተማሪው ተማሪዎቹን ከልብ ያስተምራል።