ምስካዬ ኅዙናን መድኀኔ ዓለም

ምስካዬ ኅዙናን መድኀኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን፣ አዲስ አበባ

ምስካዬ ኅዙናን መድኀኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን

የዚህ ቤተ ክርስቲያን ጽላት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አገራችን ኢትዮጵያ በፋሺስት ኢጣልያ በተወረረች ጊዜ በስደት እንግሊዝ አገር ባዝ በተባለ ከተማ ሲኖሩ፣ ጥር ፲፫ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ/ም በጊዜው በስደት ኢየሩሳሌም ለነበሩት ወደ ብፁዕ እጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ (በኋላ አቡነ ባስልዮስ) አንድ ፅላትና ለአገልግሎት የሚበቁ አምስት መነኮሳትን ወደእንግሊዝ አገር እንዲልኩላቸው በአባ ሐና ጅማ በላኩት ደብዳቤ መሠረት ተልኮ በስደት የኖረ ፅላት ነበር።


  • 'ንሆይ]] የስደት መልእክት==

“ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ፤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሥዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥትኢትዮጵያ

ይድረስ ከብፁዕ አባቴ እጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ እንደምን ሰንብተዋል ፤ እኛ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነን። እስካሁን ባለነው አኳኋን የምናስበው ለናንተ ነው እንጂ ወደኛ ምንም የሚያሳስብ የለም። ይልቁንም የኛ እዚህ መሆንና በየጊዜው ጀኔቭ በሚደረገው ስብሰባ ፤ ቢፈቀድልን የኛ መሄድ ባይፈቀድልንም መላክተኛችንን መላክ ለመጣንበት ጉዳይ ዋና ረዳታችን ስለሆነ የፈጣሪያችን ፍርድ የኢትዮጵያን ጉዳይ እስካጠቃለልን ድረስ እዚሁ ሆኖ ማዳመጥ የሚያስፈልግ መሆኑን ስለተረዳነው የፈጣሪያችንን ቁርጥ እስክናውቅ ድረስ በዚሁ በእንግሊዝ አገር ለመቆየት ቆርጠናል።

የእግዚአብሔር ቸርነት ፈቅዶልንና አሰናብቶን ወደ ኢየሩሳሌም እስከምንመጣበት ቀን ድረስ የሃይማኖት ችግር እንዳያገኘን የሚያድጉትም ልጆቻችን የሃይማኖታቸውን መሠረት እንዳያጡት አስበን አንድ ጽላትና አምስት መነኮሳት የሚያስፈልጉትን ንዋየ ቅድሳትና መጻሕፍት ሰጥተውት ይዞ እንዲመጣ አባ ሐናን ልኬዋለሁና ከመምህር ገሪማ ጋራ ተማክራችሁ ዐቢይ ጾም ሳይገባ እንዲደርስ አድርጋችሁ እንድትልኩልን ይሁን።

በየጠረፋችንም ተሰደው በሰው ግዛት ላሉትም ሰዎቻችን እንደዚሁ ሰው መላክ አስፈላጊ ሳይሆን አይቀርምና እየተመካከራችሁበትና ፈቃዱ የሚሆን መነኩሴ እየመረጣችሁ እስክናስታውቃችሁ ድረስ መጠበቅ ነው።

ጥር ፲፫ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ/ም ፣ ሎንዶን

እጨጌ ገብረ ጊዮርጊስም ይሄ መልእክት እንደደረሳቸው በኢየሩሳሌም ዴር ሡልጣንኢትዮጵያ ገዳም የነበረውን፣ በስመ መድኀኔ ዓለም የተጠራ ጽላት ፤ ለቁርባንና ለጸሎት የሚያስፈልጉትን ንዋየ ቅድሳት እና መጻሕፍት ጭምር በአምስት መነኮሳት እጅ አስይዘው በፍጥነት ወደእንግሊዝ አገር ላኩ።

የተላኩትም መነኮሳት፦

  • ፩ኛ/ መምህር ገብረ ኢየሱስ - መነኮስ ወቆሞስ
  • ፪ኛ/ አባ ሐና ጅማ - መነኮስ
  • ፫ኛ/ አባ ማርቆስ - መነኮስ
  • ፬ኛ/ አባ ኃይሌ ብሩክ - መነኮስ
  • ፭ኛ/ አባ ገብረ ማርያም - መነኮስ

ናቸው። እነዚህ መነኮሳትም እንግሊዝ አገር እንደደረሱ፣ ሚያዝያ ፳፯ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ/ም አንድ መካነ ጸሎት ባርከው እንደ ቤተ ክርስቲያን ሕግ የጸሎትና የቁርባን ሥርዓት ያደርጉ ጀመር። ከዚያም የተነሳ ያች ቤተ ክርስቲያን በስደት ያለች ኦርቶዶክሳዊት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተብላ ትጠራ ጀመር።

የፋሺስት ኢጣልያ ኃይል ተደምስሶ የኢትዮጵያ ነጻነት ሲመለስ ይሄ በስደት እንግሊዝ አገር የነበረው የመድኀኔ ዓለም ጽላትም ከግርማዊት እቴጌ መነን ጋር ነሐሴ ፳፫ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ/ም ተመልሶ አገሩ ገባ። ከዚያም በኋላ ሚያዝያ ፳፯ ቀን ፲፱፻፴፭ ዓ/ም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሆስፒታል ቅጽር ግቢ በታነፀው ቤተ ክርስቲያን “ምስካዬ ኅዙናን መድኀኔ ዓለም” ተብሎ ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ።

በስደት በነበሩበት ዘመናት ሥርዓተ ቅዳሴ እንደተለመደው በግዕዝ ሲዘመር፣ በሥርዓቱ ውስጥ የተካተቱት ጸሎቶችም ሆኑ የቅዱስ ወንጌል ምንባብ፣ ወዘተ. ግን በአማርኛ ቋንቋ ነበር የሚነበቡት። አሁንም ይሄ ታቦት ተመልሶ ከገባ በኋላ በአባ ሐና ጅማ እና በአባ ኃይሌ ብሩክ መሪነት ሥርዓቱ ቀጠለ። በአገሪቱም ይሄ አዲስና ምእመኑን የሚያሳትፍ ተራማጅ ሥርዓት በኢትዮጵያ በጊዜው ያልተለመደ ቢሆንም የከተማው ምእመናን ጧት እና ማታ የምስካዬ ኅዙናን መድኀኔ ዓለምን ቤተ ክርስቲያን ማዘውተር ልምድ ሆነ። በተጨማሪም፣ የአጥቢያው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት እና እቴጌ መነን ትምህርት ቤት ተማሪዎች እሑድ እሑድ የማይለዩ አስቀዳሾች ነበሩ። በዚህ ዓይነት እስከ ፲፱፻፵ ዓ/ም ቆይቶ በጊዜው የነበረበት የቅዳሴ ቤት መጥበብ ግልጽ ስለሆነ ንጉሠ ነገሥቱ አሁን ቤተ ክርስቲያኑ የሚገኝበትን ቦታ ለአዲስ ቤተ ክርስቲያን ግንባት እንዲሆን አዘዙ።

የቤተ ክርስቲያን ግንባታ

ለማስተካከል

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የአዲሱን የምስካዬ ኅዙናን መድኀኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን መሠረት ድንጋይ ሚያዝያ ፳፯ ቀን ፲፱፻፵ ዓ/ም ሲያስቀምጡ አትኩሮታቸው ወጣቱ ትውልድ ላይ እንደነበር ያደረጉት ንግግር ያመለክታል።

“… በተፈሪ መኮንን ተማሪ ቤት ክበብ ውስጥ ይህን የአዲሱን ቤተ ክርስቲያን መሠረት ስንመሠርት በዚህ ተማሪ ቤት የሚማሩት ክርስቲያናውያን ወጣቶች የኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖታቸውን ሥርዓት እንዲጠቀሙበት አስበን ነው።

የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው ፤ ሃይማኖቱን የማያከብር ሃይማኖት የሌለው፣ እርሱም የሚያምነው ደገፋ የሌለው፣ እርሱንም ማንም የማያምነው የሁለት ዓለም ስደተኛ ነው። ፍሬውን ለማየት ተስፋችን እርሱ ምስካዬ ኅዙናን መድኀኔ ዓለም ነው።” [1]

የቤተ ክርስቲያኑ ሕንፃ ግንባታ በሚካሄድበት ጊዜ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በቅርብ እንደተረዳው፣ ንጉሠ ነገሥቱ፣ ልዑላን እና ልዑላት ቤተ ሰቦቻቸው፤ መሳፍንቱ እና መኳንንቱ የሕንፃውን መገንቢያ ድንጋይ በትከሻቸው እያቀረቡ እንደተሳተፉ ተገንዝቧል።

በዚህ ዓይነት እርምጃ ተገንብቶ፣ ልክ በሁለት ዓመቱ በ፲፱፻፵፪ ዓ/ም ግንባታው ተፈጽሞ ቤተ ቅዳሴው ሚያዝያ ፳፯ ቀን ተመረቀ።

ዋቢ ምንጭ

ለማስተካከል
  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሐዋርያዊ ድርጅት፣ “ትንሣኤ፡ የሃያ አምስት ዓመታት መንፈሳዊ እርምጃ” (፲፱፻፶፱ ዓ/ም) ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት።
  1. ^ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴሚያዝያ ፳፯ ቀን ፲፱፻፵ ዓ/ም (የምስካዬ ኅዙናን መድኀኔ ዓለም ቤ/ክ መሠረት ሲጥሉ ያደረጉት ንግግር)