ማኒኪስም
ማኒኪስም በፋርስ ነቢይ ማኒ (208-268 ዓም የኖረ) ትምህርቶች የተመሠረተ ሃይማኖት ነበር። ይህ አነስተኛ ሃይማኖት ለጊዜው በምዕራብ በሮሜ መንግሥትና ወደ ምሥራቁ እስከ ቻይና ድረሥ ይስፋፋ ነበር። በምዕራብ፣ ተከታዮቹ እንደ ክርስቲያኖች ለማስመሰል ጣሩ፣ በምሥራቁም እንደ ቡዲስቶች አስመሰሉ። ስለዚህ ብዙ ጊዜ በድብቅ ያስተማሩት እምነት ነበር፤ ከሌሎቹ ሃይማኖቶችም ዘንድ ብዙ ጊዜ ማሳደድ ያገኙ ነበር። በጎ በክፋት ላይ ማሽነፉን የካደ ሃይማኖት ነበር። በአሁኑ ሞንጎሊያ አካባቢ በተገኘው በዊግር ኻጋናት መንግሥት ከ754 እስከ 832 ዓም ድረስ፣ ማኒኪስም የመንግሥት ሃይማኖት ነበር።
ነቢዩ ማኒ ስድስት መጻሕፍት በአራማይስጥና አንድ መጽሐፍ በመካከለኛ ፋርስኛ እንደ ጻፈ ተባለ፤ ሌሎች ግን የሰው ጽሑፍ እንደ ራሱ ያሳለፈ ሌባ አሉት። ከነዚህ መጻሕፍት ከፍርስራሽ በቀር አሁን በሙሉ አይታወቁም። ከ፮ቱ አራማይስጥ መጻሕፍት ግን አንዱ ትኩረት የሚስብ «የረጃጅሞች መጽሐፍ» ደግሞ ከማኒ ዘመን በፊት በቁምራን ብራናዎች መካከል (100 ዓክልበ - 50 ዓም) በፍርስራሽ ተገኝቷል። የማኒ ድርሰት አለመሆኑን ከማስረዳት በላይ፣ ይህ ጽሑፍ ከመጽሐፈ ሄኖክ ጋር ተመሳሳይነት አለው፣ ሆኖም በማየ አይኅ ውስጥ ከጠፉት ክፉ ዘሮች አስተያየት ይነገራል።
በቻይና ማኒኪስም በመጨረሻ ከቡዲስም ጋራ ተባበረ፤ ስለዚህ ማኒን ከቡዳዎቹ መካከል እንደ አንዱ ቡዳ የሚቆጥር አንዳንድ የቡዲስም አይነቶች አሁን በቻይና ሊገኙ ይቻላል። ከማኒ ድርሰቶች ግን ምንምን አላስቀሩም።
ቅዱስ ኦግስቲን ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት የማኒኪስም ተከታይ ስለ ነበር፣ ፍልስፍናው እንዴት እንደ ተሳተ ለመግለጽ ጽፏል።