መምበርቱ
መምበርቱ (መስከረም 10 ቀን 1604 ዓ.ም. የሞቱ) ፈረንሳያውያን በአካዲያ (የዛሬው ኖቫ ስኮሺያ፣ ካናዳ) መጀመርያ በሠፈሩበት ወቅት የሚግማቅ ብሔር ሳግሞው (አለቃ) ነበሩ። መጀመርያ የገስፑጒትክ ክፍላገር ሳግሞው ሆነው፣ በኋላ የሌሎቹ 6 ሚግማቅ ክፍላገሮች ሳግሞዎች ዋና ሳግሞው እንዲሆኑ መረጡዋቸው።
መምበርቱ ከስሜን አሜሪካ ኗሪዎች መጀመርያ የተጠመቁት በመሆናቸው በተለይ ይታወቃሉ። በሰኔ 20 ቀን 1602 ዓ.ም. ቄሱ አቤ ዠሴ ፍሌሼ ለመተባበር ምልክት እሳቸውን ስለ ፈረንሳይ ንጉሥ 4ኛ አንሪ ስም «አንሪ» ሰይሟቸው ከቤተሠባቸው ጋር አጠመቃቸው።
ፈረንሳያውያን መጀመርያ በደረሱ ጊዜ በ1597 ዓ.ም. ዕድሜያቸው ከ100 አመት እንደ በለጠ ተብሎዋል። በወጣትነታቸው የፈረንሳይ ዠብደኛ ዣክ ካትዬን በ1526 ዓ.ም. ጉዞ ላይ መገኛነቱን ትዝ እንዳሉ ነገሯቸው። ፈረንሳያውያን ምሽግ በመምበርቱ አገር በፖርት ሮያል ሠርተው በ1599 ዓ.ም. ሁለት ሰዎች ብቻ ትተው ወጡ። በ1602 ዓ.ም. ወደ መምበርቱ እስከተመለሱ ድረስ እሳቸው ለምሽጉና ለ2ቱ ፈረንሳውያን ሰዎች ኅላፊና ታማኝ ነበሩ።
ከተጠመቁ አስቀድሞ «ሳግሞው» ወይም ፖለቲካዊ መሪ ከመሆናቸው በላይ፣ መምበርቱ ደግሞ «ኦትሟን» ወይም መንፈሳዊ መሪ ሆነው ነበር፤ ነገዳቸው የሕክምናና የትንቢት ችሎታ እንደነበራቸው ያመን ነበር። በዛሬው ሜን ክፍላገር የኖረው ፓሣማኰዲ (አርሙሺኳ) ብሔር ሌላውን የሚግማቅ ሳግሞው ፓኖኒያክን በ1598 ዓ.ም. ከገደሉ በኋላ፣ መምበርቱ ሥርዓተ ቀብር ሲያካሔዱለት ፈረንሳያውያን አዩ። ቂሙን ለመበቀል፣ መምበርቱ በዘመቻ በሐምሌ 1599 ዓ.ም. 500 ጎበዞችን ወደ አርሙሺኳ መንደር ወደ ሿኮወት (የዛሬ ሳኮ፣ ሜን) መሯቸው፣ ከጠላቶቻቸውም 20፣ ከነመሪዎቻቸው ኦንመሻንና ማርሻን ገደሏቸው።
ኢያሱሳዊው ቄስ ፒዬር ቢያርድ እንደ ጻፈው፣ እንደ ሌሎች የተነጩ ሚግማቅ ወንዶች ሳይሆን፣ መምበርቱ ባለ-ጺም ነበሩ። ከሌሎቹም ትልቅ ነበሩ፣ የመቶ አመት ሽማግሌ ቢሆኑም፣ ምንም ሽበት አልነበራቸውም። አብዛኞቹ ሳግሞዎች ከአንድ ሚስት በላይ ቢያገቡም፣ መምበርቱ ግን አንዲት ሚስት ብቻ ነበረቻቸው፤ እርሷም «ማሪ» ተብላ ተጠመቀች። የበኲር ልጃቸውም ስም መምበርቱጂች ሲሆን የጥምቀት ስም «ሉዊ መምበርቱ» ተቀበለ። ሁለተኛው ወንድ ልጅ (አክቶዲን) በጥምቀት ጊዜ አልተገኘም፤ ሦስተኛውም አክቶዲጂች «ፖል መምበርቱ» ተብሎ ተጠመቀ። ደግሞ የሴት ልጃቸው ጥምቀት ስም «ማርገሪት» ነበረ።
አባ ቢያርድ እንደ ጻፈው፣ የመምበርቱ ልጅ አክቶዲን በብርቱ በታመመ ጊዜ፣ ለማማለጃ 2 ወይም 3 ውሾች ለመሠዋት ዝግጁ ሲሆኑ፣ ቢያርድ ግን ይህ ስህተት ነው ሲላቸው አልሠዋቸውምና ወዲያው አክቶዲን ዳነ።
ከዚህ ትንሽ በኋላ፣ በ1603-4 ዓ.ም.፣ መምበርቱ እራሳቸው ታመሙ፤ በመስከረምም ዐረፉ። በመጨረሻ ቃላቸው፣ ልጆቻቸው በክርስትና ጸንተው እንዲተጉ አስጠነቀቋቸው።