ከርቲስ ብሎው (1951 ዓም / 1959 እ.ኤ.አ. ተወለደ፤ ልደት ስም ከርቲስ ዋልከር) ዝነኛ አሜሪካዊ ዘፋኝ ሲሆን አሁን በተጨማሪ የክርስትና ሰባኪ ሆኖአል። ራፕ ሙዚቃ ለተባለው ሙዚቃዊ ዘርፍ ግምባር ቀደምትነት የያዘ አንጋፋ ራፐር ሆኗል። ይህ በ1972 ዓም በቀረጸው ራፕ ዘፈን «ዘ ብረይክስ» ሆነ። ለአለም ሕዝብ እንዲህ አይነት ቄንጥ ሰምተው ባያውቁም በዚያን ጊዜ ደግሞ ሌላ ራፕ ቡድን ሹገር ሂል ጋንግ በዘፈናቸው «ራፐርዝ ዲላይት» ቄንጡን ለአለም እንዳሳወቁት በታሪክ ይታወሳል። በቅርብ ጊዜ ውስጥ በርካታ «ራፕ» እና «ሂፕ-ሆፕ» ሙዚቃ ዘመናዊ ሆነ።

ከርቲስ ብሎው 2004 ዓም

ከዚያ በኋላ ከርቲስ ብሎው ሌሎችን ተወዳጅ ራፕ ዘፈኖች ከማስገኘቱ አላቋረጠም፤ በተለይም «ፓርቲ ታይም» (1975 ዓም) እና «ባስከትባል» (1976 ዓም) ተወደዱ። ስምንት የራፕ አልበሞች ሰርተው ነበር። በኋላ እንደ ተከተሉት እንደ ብዙ ራፐሮች ሳይሆን ዘፈኖቹ የብልግና ቃላት የተሞሉባቸው አይደሉም። በ1986 ዓም ከርቲስ ብሎው መጽሐፍ ቅዱስንና ክርስቶስን ተቀብሎ ተጠመቀ። ከ1999 ዓም እስካሁን አራት የክርስቲያን ራፕ አልበሞች ከነቡድኑ «ዘ ትሪኒቲ» (ሥላሴው) ቀርጿል። በ2001 ዓም ደግሞ እንደ ወንጌል ሰባኪ ተካነ፤ የ«ሂፕ-ሆፕ ቤተክርስቲያን» በኒው ዮርክ ከተማ መሥራች ሆነ፤ ወንጌሉን በራፕ ሙዚቃ በኩል ይሰብካሉ።