ግዝፈት በአንድ ነገር ውስጥ ያለ የቁስ ብዛት ማለት ነው። ወይንም፣ በተፈጥሮ ኅግጋት ጥናት የሚሰራበት ትርጉም፣ ግዝፈት ማለት የአንድ ቁስ ግዑዝነት መለኪያ ነው። የበለጠ ሲመነዘር፣ የአንድ ቁስ ግዝፈት፣ ያ ቁስ የያዘውን ፍጥነት እንዳይቀይር የሚያሳየው ተቃውሞ ልኬት ነው።

ለምሳሌ በአንድ ዓይነት ጉልበት ፣ ትንሽ እና ትልቅ ድንጋይ ለማንቀሳቅስ ቢሞከር፣ ትንሹ በፍጥነት ያለብዙ ተቃውሞ ፍጥነቱን ሲቀይር ፣ ትልቁ ግን ዝግ ባለ ፍጥነት፣ በብዙ ተቃውሞና እልህ ይንቀሳቀሳል። ስለዚህ ትንሹ ድንጋይ ከትልቁ ድንጋይ ያነሰ ግዝፈት አለው እንላለን።

አንድ ነገር ያለው ግዝፈት የትም ቦታ እኩል ነው። ከባህር ወለልም ሆነ ከተራራ ላይ፣ አንድ ቁስ አንድ ዓይነት ግዝፈት አለው ምክንያቱም በአንድ አይነት ሁኔታ ፍጥነቱን ለመቀየር እኩል ጉልበት ስለሚጠይቅ። በሌላ አባባል፣ ለጉልበት እሚያሳየው ተቃውሞ የትም ቦታ እኩል ነው። በጠፈር ኦና ሳይቀር፣ ይህ ተቃውሞው እኩል ነው።

ግዝፈት በ SI ስርዓት መለኪያው kilogram (ኪሎግራም) በምህጻረ ቃል kg (ኪ.ግ.) ነው።

የግዝፈትና ክብደት ልዩነት ለማስተካከል

ግዝፈት ከክብደት ይለያል። ግዝፈት ያላቸው ማናቸውም ነገሮች እርስ በርሳቸው እንደሚሳሳቡ የተፈጥሮ ኅግጋት ጥናት ያዎቀውና ያጸናው ሐቅ ነው። የክብደት አመጣጥም ከዚህ የተፈጥሮ ባህርይ ነው። ለምሳሌ በመሬት ላይ የሚኖር ማናቸውም ቁስ፣ በመሬት ይሳባል። ይህ ጉልበት፣ የቁሱ ክብደት ይባላል። ትልቅ ግዝፈት ያላቸው ነገሮች፣ በግስበት ሕግጋት ምክንያት በትልቅ ጉልበት ይሳባሉ፣ ትንሽ ግዝፈት ያላቸው ደግሞ በትንሽ። ስለዚህ ክብደትና ግዝፈት ተመጣጣኝ ዝምድና አላቸው።

ወርቅ በግዝፈት እና ክብደት ለማስተካከል

የአንድ ቁስ ክብደት ከግዝፈቱ ቢመነጭም ክብደቱ በተለያየ ቦታ የተለያየ ሆኖ እናገኘዋለን። በተፈጥሮ ኅግጋት መሠረት፣ አንድ ቁስ ወደ መሬት ማህከል እየተጠጋ በሄደ ጊዜ፣ መሬት በላዩ ላይ የምታሳርፍበት ስበት እየጨመረ ይሄዳል። በተቃራኒ ከመሬት እየራቀ ሲሄድ ክብደቱ ይቀንሳል። ስለሆነም ብልጥ ነጋዴ፣ አንድ የወርቅ አምባር ተራራ ላይ ገዝቶ፣ ያን አምባር የባህር ወለል ላይ ቢሸጠው፣ ክብደቱ ስለሚጨምርለት፣ ብዙ ትርፍ ሊያገኝ ይችላል። ማንም እንደሚገነዘበው ግን፣ አምባሩ በምንም ዓይነት አልተቀየረም፣ ያልተቀየረው ነገሩ፣ ግዝፈቱ ይባላል። በውስጡ የያዘው የወርቅ ብዛት፣ ወይንም የቁስ ብዛት ምንጊዜም አንድ አይነት ስለሆነ። ምንም እንኳ ክብደቱ ቢቀያየርም።