ገብረ ክርስቶስ ደስታ

በኢትዮጵያ የተገኙ የጥበብ ሰዎች በሥራዎቻቸው የቱንም ያህል መለኪያ ቢቀመጥላቸው ለገ/ክርስቶስ ግን ”ይህ ቀረው” ለማለት ማጣፊያው ያጥር ይሆናል፡፡ በሀሳቡና በስሜቱ ተፈትለው በጌጡት ስራዎቹ የተደነቅነውን ያክል ከአስተዋይነቱ፤ ከሥብእናውና ከማንነቱ እንደዚሁም ከጠንካራ ሠራተኝነቱ የምንማራቸው ብዙ ቁምነገሮች አሉ፡፡ በተወለን ሥራዎቹ ቀን ቀንን እየወለደው ሲቀጥል የዚህ ሠው ሥራዎች ውርስ ሆነው ለሁል ጊዜም አብረውን ይኖራሉ፡፡ ገብረ ክርስቶስን በስዕል ሥራው ዓለም አውቆታል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ለስሜቱም ቢሆን፤ በማጣትና በማግኘት ፣ በሞት ጭካኔ ፣ በብቸኝነት፣ በትካዜና ፍቅር በአጠቃላይ በሠው ልጅ ጠባይ ተለይተው የሚነሱ ማንነቶችን ነቅሶ…በግጥሞ የተወልን ሥራዎቹ ዘመን ተሻጋሪ ናቸው፡፡ የገብረክርስቶስ ደስታን ነገር ባስበው ሳስበው እንዲያው ደርሶ አንዳች የማልፋተው ሀሳብ በውስጤ ይራወጣል፡፡ መሽቶ እስኪነጋ ለኔ የዚህ ሰው ሥራ አዲስ ነው፡፡ በዛ ዘመን የተነሱ አስደናቂዎቹ ብእረኞች በአለም ተወዳደሪ መሆናቸውን ስመስክር ኩራት አለኝ፡፡ ነገርግን በቅጡ ለመዘከር የበቁት እጅግ ጥቂቶቹ መሆናቸውን ስረዳ “አደራ በላ“ መሆናችን ይታየኛል፡፡ ይሄ አስደናቂ ሰው ለአገሩ የነበረውን ፍቅር “ኢትዮጵያ እናቴ“ ሲል በሰጣት ቦታ የአገሩን ናፍቆት “አገሬ“ “እንደገና“ በተሰኙ ግጥሞቹ እንደዚሁም የአገር ቁጭቱን “የጾም ቀን“ እና “በባእድ አገር“ በተሰኙት ግጥሞቹ በሚገባ ገልጾታል፡፡ በተለይ አገሬ የተሰኘው ግጥሙ አንጀት ይበላል፡፡ ምን ይደረግ ይህ ታላቅ ሰው በስደት እንደማሰነ የአገሩን አፈር ለመቅመስ አለመታደሉ ያስቆጫል፡፡ ገብረ ክርቶስ ከአባቱ ከአለቃ ደስታ ነገዎ ከእናቱ ከወ/ሮ አፀደ ማርያም ወንድማገኝ በ1924 ዓ.ም በምስራቁ የሀገራችን ክፍል ሀረር ከተማ ተወለደ፡፡ ከዘር የሚወረስ አንዳች ነገር ካለ አባቱ አለቃ ደስታ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሀይማኖታዊ ትምህርት ሊቅና በብራና የዕጅ ጽሁፎቻቸው በባህላዊው ሥዕሎቻቸው የተደነቁ ሰው እንደ ነበሩ ይነገራል፡፡ ገብረ ክርስቶስ ወላጅ እናቱን (ወ/ሮ አፀደ ማርያም ወንድማገኝ) ገና በልጅነቱ በሞት ተነጠቀ፡፡ መቸም የእናት ሞት ከባድ ነው፡፡ ብቻ አምላክ ጨርሶ አልከፋም አያቱ እማሆይ ብርቅነሽ ሳሳሁ ልክ እንደ እናት ማስረሻ…ልክ እንደናት ሆነው አሳደጉት ፡፡ የአባቱን እውቀት ብሎም የሥዕል ሥራ እያደነቀ ላደገው ትንሹ ገ/ክርስቶስ የሕይወት ጥሪውን የለየው ገና በጠዋቱ ነበር፡፡ በተለይ የሚደንቀው እዚህጋ ነው! እኮ ምን? ካላችሁ ገና የስድስት አመት ልጅ እያለ ”እናትነት” ብሎ የሠየማትን የእርሳስ ሥዕል አየን፡፡ ገና ብዙ የብዙ ብዙ ያሳየናል፡፡ ገብረ ክርስቶስ ለአባቱ የነበረው ፍቅር መቸም የተለየ ነው፡፡ የቱንንም ያህል አድናቆት ”እረፍት አድርግ አሁን” በሚለው ግጥሙ ገልጾታል፡፡ አንጀት የሚበላ ግጥም ነው! ገብረ ክርስቶስ 1961 ከ ሄድ ሲድኒ ጋር ባደረገው አጭር ቃለ መጠይቅ ስለ አባቱ የሚከተውን ብሎ ነበር፡- አበቴ ቅዱሳን መጻህፍትን በእጁ ይጽፍ ነበር፡፡ በዘመኑ ዘመናዊ የህትመት መሳሪያ በሀገራችን የነበረ ቢሆንም በኖረው ባህል መሠረት በእጅ የተዘገጁ መጻህፍቱን ተመራጭ ነበሩ፡፡ ለመጸሀፍቱ ዝግጅት የሚያስፈልገውን መጻፊያም ሆነ ቀለሙን ያዘጋጅ የነበረውና እራሱ ሲሆን በቅዱሳን መጻህፍቱ ውሥጥ የሚካተቱ ምስሎችን ይሠራ ነበር፡፡ በልጅነት ጊዜዬ የአባቴን ሥራዎች እያየው እደነቅ ነበር፡፡ በየቀኑ ሥዕል እንደሠራም ያበረታታኝ ነበር፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በትውልድ ከተማው ሀረር ራስ መኮንን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሮ ሲያጠናቅቅ ለሁለተኛና ለከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱ አዲስ አበባ ተቀበለችው፡፡ ሸገር የሁሉም አድባር! እንደመጣ በቅድሚያ የተመደበው በኮተቤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው በጄኔራል ዊንጌት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡ በዛ ዘመን በንጉስ ኃይለ ሥላሴ መልካም ፈቃድ ለባለ ብሩሕ አእምሮ ተማሪዎች ከተዘጋጁት የትምህር ተቋማት መካከል ኮተቤና ጄኔራል ውንጌት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቀዳሚዎቹ መሆናቸውን ልብ ይሏዋል፡፡ በኮተቤ ሁለተኛ ደረጃ አጭር ቆይታው በኢትዬጵያ የጥበብ ዘርፍ ከፍተኛ ዝና ያላቸውን ስመጥሮቹን በተለይ መንግስቱ ለማንና አፈወርቅ ተክሌን የመተዋወቅ ዕድል አግኝቷል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በጥሩ ውጤት ካጠናቀቀ በዃላ ለከፍተኛ ትምህርት በቀዳማዊ ሐይለ ስላሴ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ሳይንስ ፋካልቲ የተመደበው ገብረ ክርስቶስ ትምህርቱን የተከታተለው ለአጭር ጊዜ ነበር ፡፡ ደረቁን ሳይንስ ሳይወደው ቀርቶ ወይም በሌላ ምክንያት የሁለተኛ ዓመት ተማሪ እያለ የኑቨርሲቲ ትምህርቱን አቋርጦ ወጣ፡፡ በሳይንስ ትምህርቱ ገፍቶበት የበቃ የግብርና ባለሙያ እንዲሆንላቸው ሲመኙ ለነበሩት ቤተሠቦቹ አጋጣሚው እንደ ዱብ እዳ የከፋ ነበር፡፡ እሱ ግን ሙያ በልብ ነው ብሎ በውሳኔው ፀና፡፡ በጥበብ ስኬት ሲታሰብ መቸም ያለ ገቢ ብቻውን አይሆንም፡፡ ገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡ ለምግብም ቢሆን፤ ለልብስ ወይም ደግሞ ለዛች ለምናቃት ነገር ወይም አንዳንዴ ውቤ በረሃ ጎራ ለማለት ካስፈለገ፡፡ ገብረ ክርስቶስ ማንንም አላስቸገረም፡፡ ለዚሁም በቀድሞው የንጉሰ ነገስት መንግስት መስሪያ ቤቶች ተቀጥሮ መሥራት አንዱ አማራጭ ሆኖ ተገኘ እናም ጥበብን እረዳት ለሱም ደሞዝ ተቆረጠለት፡፡ ገብረ ክርስቶስ ከሠራባቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች መካከል የንጉሠ ነገስት መንግስት የአፈር ምርምር ላቦራቶሪ፤ አውራ ጎዳና ባላስልጣን እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚጠቀሱ ሲሆን አዲስ አበባ በሚገኘው ስብስቴ ነጋሲ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መመህር ሆኖም ሰርቷል፡፡ ማምሻም ዕድሜ ነው እንደሚባለው የቀድሞዋ ምዕራብ ጀርመን እንዲማር ልትጠራው ጥቂት ጊዜ ሲቀር በሥዕል ሙያው የመጀመሪያ የሆነውን የሥራ ቅጥር አገኘ፡፡ በዘመኑ በአሜሪካ መንግስት ድጋፍ ሲደረግለት በነበረ የመማሪያ መጻህፍት ዝግጅት ፕሮጀክት የተቀጠረው ገብረ ክርስቶስ በወቅቱ የነበረው የሥራ ሀላፊነት ለሕጻናት በሚዘጋጁ መጻህፍት እንዲካተቱ የተመረጡ የሥዕል ሥራዎችን ማዘጋጀት ነበር፡፡ ገብረ ክርስቶስ በ ሃያ አንደኛው ዓመቱ አካባቢ ያልታሰበ ነገር ገጠመው፡፡ ቆዳን በሚያሳስርና የቆዳን ቀለም በሚለውጥ ለምጥ መሳይ መጥፎ በሽታ ተያዘ፡፡ ላገኘው በሽታ ፈውስ በሀገር ቤትና በውጭ ፈለገ አስፈለገ፡፡ ነገርግን መፈትሄ አልተገኘም፡፡ እያዋለ ሲያድር በሽታው በአካሉ ላይ ሠለጠነ የሰውነቱን ቆዳ በላው፤ ቅርጸ ሰውነቱ ብቻ ሲቀር የፊቱን ቀዳ ጨርሶ ለወጠው፡፡ ሳይደግስ አይጣላም! ትላለች ወ/ሮ ጠንፌ፡፡ ጠንፌን እዚህ ምን አመጣት? እሷ ምን አውቃ ነው? ለኔ ግን ቀለሞችን ለምን እንከን እንደሚከተላቸው አይገባኝም፡፡ እንደ ወ/ሮ ጠንፌ ለአፍታም ቢሆን አሠብኩኝ ግን እውነቱ እንደዚህ ነው በገብሬ ላይ የመጣው በሽታ ለቀጣዩ ሥራው የፈየደው አንዳች ነገር ከሌለ በሽታው በህይወቱና በሥራው ላይ ያሳደረው ተጽእኖ በቀላሉ ሊገመት አይችልም፡፡ ገብረ ክርስቶስ በውጭ ሀገር ሥነ ጥበብን ለመማር 1949 ወደ ቀድሞዋ ምዕራብ ጀርመን አቀና፡፡ ወቅቱ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ካበቃ ከ12 ዓመት በዃላ ሲሆን ጀርመን ከጦርነቱ አገግማ የጥበብ ሥራዎች በሠፊው መሠራት የጀመሩበት ነበር፡፡ እንደሚታወቀው የናዚ አጋዛዝ በጥበብ ሥራዎች ላይ በነበረው ቁጥጥር ምክንያት የስዕል ሥራ ከመዳከሙም በላይ ብዙ ባለሙያዎች ሥራቸውን ማቆም ወይም ከሀገር መሰደድ እጣቸው ነበር፡፡ የጦርነቱ ማብቃትንን እንደዚሁም የናዚ መንግስት መወገድን ተከትሎ ባሉት ጥቂት ዓመታት በጀርመን የጥበብ ሥራ በእጅጉ መነቃቃት የታየባት ሀገር ነበረች፡፡ በዚህ እረገድ በተለይ ኮለኝ የሚገኘው የጥበብ ትምህርት ቤት የጦርነቱ ማብቃትን ተከትሎ ወደ ሀገራቸው የተመለሱ የሥዕል ባለሙያዎችና ከሌሎች ሀገራት የሚመጡ ተማሪዎችና ምሁራን መሠብሰቢያ ከመሆኑም በላይ የጀርመን የረቂቅ ሥዕል ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀበት ተቋም እንደሆነ ይታመናል፡፡ ገብረ ክርስቶስ በኮለን የጥበብ ትምህርት ቤት በቆየባቸው አምስት ዓመታት ሥለ ሥዕል አሠራር፤ቅብ አጠቃቀምና ሌሎች የሥዕል መሳሪያዎችና አጠቃቀማቸውን በሚገባ ከማወቁም በላይ በረቂቅ ሥዕል ሥራ ከፍተኛ ዝና የነበራቸውን ምሁራን ለማወቅና ሥራቸውን ለመመልከት እድል ያገኘበት አጋጣሚም ነበር፡፡ ገብረ ክርስቶስ በጀርመን ሀገር እያለ በረቂቅ ስዕል አሳሳሉ ከታወቀው ሩሲያዊ ዋሲስኪ ካዲስኪና ከሌሎች የአውሮፓ ረቂቅ ሥዕል ጠቢባን ጋር መገናኘቱን ተከትሎ ለረቂቅ ስዕል ሥራ ከፍተኛ ፍቅር እንዳደረበት ይነገራል፡፡ ሠዓሊ ዮሀንስ ገዳሙ የጀርመን ኢንባሲና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ባዘጋጁት የገብረ ክርስቶስ መታሰቢያ ጥራዝ ላይ እንደገለጸው ገብረ ክርስቶስ የኮለኝ ትምህርቱን ተከትሎ ባሳየው ለውጥ ከቀደሙት የሥዕል ሥራዎቹ በተለየ ለረቂቅ ሥዕል ሥራ ትኩረት ከመስጠቱ በተጨማሪ በቅብ አመራረጡ ከደማቅ ቀለም ይልቅ ጥቁርና ግራጫ ቀለሞችን በአብዛኛው ይጠቀም እንደነበር ገልጿል፡፡ ከኮለኝ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት በከፍተኛ ውጤት መመረቁን ተከትሎ በተበረከተለት የስዕል መስሪያ ስቱዲዬ የተለያዩ ሥዕሎችን በማዘጋጀት የአንድ ሰው የሥዕል አውደ ርእይ ለማቅረብ ችሏል፡፡ ይህንን የሥዕል አውደ ርዕይ ለማቅረብ ከዓንድ ዓመት በላይ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጉና በተለይ በመሀሉ ለትምህርታዊ ጉብኝት በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች ባደረገው ትምህርታዊ ጉዞ ያገኘው ልምድ ስኬታማ አውደ ርዕይ ለማዘጋጀት እንዳስቻለው ይነገራል፡፡ ገብረ ክርስቶስ በይበልጥ የሚታወቀው በሥዕል ሥራዎቹ ቢሆንም ለስሜቱም ቢሆን የጻፋቸው ጥቂት ግን ተወዳጅ የግጥም ሥራዎቹ በኢትየጵያ በዘርፉ ትልቅ ስም ካላቸው ሰዎች ተርታ አስቀምጠውታል፡፡ ገብረ ክርስቶስ በረቂቅ የሥዕል አቀራረቡ በሀገራችን መነጋገሪያ የሆነውን ያክል ግጥሞቹ የራሳቸው የቃላት አሰላለፍን የሚከተሉና የቤት አመታታቸው ቁጥር ከተለመዱት የግጥም ቤቶች የተለዩ መሆናቸው በጥበብ ቤተሠቦች መነጋገሪያ መሀናቸው አልቀረም፡፡ ገብረ ክርስቶስ የተለያዩ ጭብጦችን ነቅሶ የጻፋቸው የግጥም ሥራዎቹ የተለዩና ሥሜት የሚኮረኩሩ ከመሆናቸው በላይ የቃላት አመራረጡ እጅግ ግልጽና ቀላል በመሆናውቸው ማንኛውም አንባቢ የሚረዳቸው ናቸው፡፡ ገብረ ክርስቶስ በግጥሙ በይበልጥ የታወቀው 1959 ዓም ጀመሮ ሲሆን በተለይ በዛው ዓመት መጨረሻ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ገብሬን፤ መንግስቱ ለማና ጸጋዬ ገብረመድህን ጨምሮ ሌሎች በወቅቱ በግጥም ሥራቸው የታወቁ ጥበበኞች በታደሙበት መድረክ ባቀረበው ግጥም በልዩ አጻጻፉና በዜመኛ አነባቡ ያልተደነቀ ታዳሚ እንዳልነበረ በወቅቱ ፕሮግራሙን የቀረጸው ጋዜጠኛ ወርቁ ተገኝ ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ ገብረ ክርስቶስ በወቅቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መድረክ ካነበባቸው ግጥሞች መካከል ˝የፍቅር ቃጠሎ˝ ቀጥሎ ቀርባለች፡፡


የፍቅር ቃጠሎ

ጉንጭሽ ፅጌረዳ
ሞቆት የፈነዳ
አይንሽ የጠዋት ጨረር
የበራ ማለዳ፡፡
የማትጠገቢ የሥንዴ ራስ ዛላ
አገዳ ጥንቅሽ
ጠብ አትይ አንጀቴ ባኝክ ብመጥሽ፡፡
ቆንጀ ነሽ አንቺዬ
እሳት ነበልባል ነሽ ንዳድ ባከላቴ
ሆነሻል ሙቀቴ
ሆነሻል ህይወቴ፡፡
የጋለው ትንፋሽሽ
የሞቀው ምላስሽ
ማርኮኝ በከንፈርሽ
እጄን ሰጥቻለው
እስረኛ ሆኛለው፡፡
ያቀጠቅጠኛል ወባ ቅናት ገብቶ
ልቤን አስፈራርቶ
ትኩሳት አምጥቶ፡፡
ፍቅርሽ አቃጠለኝ በመልክሽ ልተክዝ
እቀፊኝ ልቀዝቅዝ
ንከሺኝ ልደንዝዝ፡፡
(ገብረ ክርስቶስ ደስታ፤ ህዳር 11 ቀን 1951 ዓ.ም)

የገብረ ክርስቶስ ግጥሞች ከምናውቃቸው ከመደበኛዎቹ የግጥም ቤት አሠላለፍ የተለዩ ናቸው፡፡ በተለይ ግጥም የግድ ቤት መምታት አለበት ወይም የለበትም በሚል በወግ አጥባቂ የኪነ ጥበብ ሰዎችና በተቃራኒው በተሠለፉ እንደ ገብረ ክርስቶስና ደረጄ ደሬሳ ያሉት የሚነሳው ሙያዊ ክርክር በልዩነት ሲቀጥል በማንኛውም ደረጃ በሚጻፉ ግጥሞች የሚነሱ ጭብጦች፤ የሥንኝ ትስስር እንደዚሁም የመነሻና መድረሻ ስንኞችን የሚደግፉ ሀሳቦች ይዘት መቸም ቢሆን ትኩረት የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ ከላይ በቀረበው የገብረ ክርስቶስ ˝የፍቅር ቃጠሎ˝ ግጥም አይንሽ የጠዋት ጨረር እና ቆንጀ ነሽ አንቺዬ የሚሉት ስንኞች ቤት አልባ ሆነው ቢታዩም ለቀጣይ የግጥሞቹ ስንኞች ደጋፊ መነሻና ውበት ሆነዋል፡፡ በተለይ ግጥሙ በንባብ ሲሰማ የተጠቀሱትን ስንኞች ያላቸውን ሚና በግልጽ መመልከት ይቻላል፡፡ የገብረክርስቶስ ግጥም የተለየ ቃናን ለመረዳት ቀጥሎ ያለቸውን ግጥም እንመልከት ሚስጥር

ሁሉ እንደዘበት
ሁሉም በዘልማድ
ሁሉም እንዲያው እንዲያው
የሚሆን መስሎሃል::
ጉንዳንን ተመልከት-
የወፍ ቤትን አጥና-
ንቦችን አስተውል-
አንድ የውሻ ጩኽት ሙዚቃ እየሆነ…
አለምን ያነጋል፡፡

ቀደም ሲል እንዳመለከትኩት የገብረ ክርስቶስ የጻፋቸው ግጥሞች እንደ ሥዕሎቹ በሰፊው አልታወቁም፡፡ ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ለሥዕል ሥራው ቅድሚያ መስጠቱ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገርግን ገብረ ክርስቶስ በሕይወት እያለ በተለያየ አጋጣሚ ያነበባቸውን፤ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ በተለያየ ጊዜ የታተሙትንና በሀገር ቤትና በውጭ ሀገር እያለ በማስታወሻው የተዋቸውን ግጥሞቹን ከያሉበት በማሰባሰብና በመተየብ ለህዝብ እንዲደርሱ ጥረት ላደረጉት በተለይም ለላስ ቬጋሱ አሠፋ ገብረ ማርያምና ጓደኞቹ ከፍተኛ አድናቆት አለኝ፡፡ በዚህ ግለ-ታሪክ ውስጥ የተካተቱት ግጥሞች በሙሉ የተገኙት እነ አሰፋ ካዘጋጁት የግጥም መድብል ሲሆን ገብረ ክርስቶስ በተለያየ ጊዜ የጻፋቸው አርባ ያህል ግጥሞች ተካተዋል፡፡ (This Day in Ethiopian History