አለቃ ገብረሃና ገብረማሪያም (፲፯፻፺፯ - ፲፰፻፺፬ ዓ.ም.) ዕውቅ ኢትዮጵያዊ ደራሲ ነበሩ። አባታቸው መምህር ገብረ ማርያም ምጥኑ ሲባሉ እናታቸው ወይዘሮ ሳህሊቱ ተክሌ ይባሉ ነበር።

አለቃ ገብረ ሐና (?? ያልተረጋገጠ)

ገብረሃና ገብረማሪያም በቤገምድር ጠቅላይ ግዛት በደብረታቦር አውራጃ በፎገራ ወረዳ ልዩ ስሟ ናበጋ ጊዮርጊስ በምትባል ቦታ በ፲፯፻፺፯ ዓ.ም. ተወለዱ። ገብረሃና እቴጌ መነንን መዝሙርን፣ ውዳሴ ማርያምንና ሌሎችንም አስተምረው ከጨረሱ በኋላ ለከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት በእቴጌይቱ ትዕዛዝ ወደ ጎንደር ተላኩ። ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላም በእቴጌይቱ ትዕዛዝ የአለቃነት ማዕረግ ተሰጣቸው። ከዚያም ገብረሃና በጎንደር አካባቢ የሚገኙትን ቤተ ክርስቲያናት ብቃት በተሞላበት ሁኔታ ያስተዳድሩ ጀመር። እንደ ትልቅ ምሁር ይታዩ ጀመር። በተለይ ፍትሐ ነገስትን በመተርጎም የሚወዳደራቸው ወይም የሚስተካከላቸው አልነበረም።

አለቃ ገብረሃና አቶ ሙንሮዝ በተባለ አውሮጳዊ በ1890 ዓ.ም. ፎት እንደተነሱ ሞላቨር ይገልጻል[1]

ዓፄ ቴዎድሮስ ስልጣን ከያዙና እራሳቸውንም ዳግማዊ ቴዎድሮስ ሁለተኛ ብለው ዙፋናቸውን በጫኑበት ጊዜ በሀገሪቱ ከፍትሐ ነገስት ሌላ የተፃፈ ሕግ ባለመኖሩ አለቃ ገብረሃና በተለይ ፍትሐ ነገስትን መሠረት በማድረግ ንጉሡ ሀገርን እንዲያስተዳድሩ ይረዱዋቸው ነበር።

አለቃ ገብረሃና በቅኔያቸው የሃይማኖት አለቆቻቸውን ወይም የበላዮቻቸውን ብቻ ሳይሆን የገነት ጌታን «ኰንኖ ኃጥአን ኩሎሙ አይደልወከ ምንተ፣ አፍቅሩ ፀላእተከሙ እንዘ ትብል አንተ» ኃጥአንን በገሃነመ እሳት ማሰቃየትና መኰንን አይገባህም፣ ጠላትህንም እንደራስህ አድርገህ ውደደው የሚል ትዕዛዝ እንደሰጠህ ሁሉ ሀጢአተኞችንም ማወገዝና ወደ ሲዖል መላክና ማሰቃየት ይለብህም» በማለት ፈጣሪያቸውን በመፈታተን ብዙ የምርምር ውጤቶችን አበርክተዋል። በዚህ ጥማቸውም የምርምር ቅኔ የሚል ልዩ የመጠየቂያ ወይም የመመርመሪያ መሳሪያ ይጠቀሙ ነበር።

በተጨማሪም ግብርና ለኢትዮጵያ ኦርቶደክስ ቤተ ክርስቲያን ብሉይ ኪዳንንና አዲስ ኪዳንን በመተርጎም ትልቅ አገልግሉት ቢያደርጉም ትልቁን አስተዋጽዖ ያደረጉት በሕግና በቤተ ክርስቲያን ዜማና አቋቋም ነበር። እንደዚሁም የፈጠሩት አዲስ ዓይነት የቤተ ክርስቲያን አቋቋም ከደብረታቦር ወደ ሸዋ እና ትግራይ ተሰራጭቷል። ይህንንም አቋቋም ከብቸኛው ልጃቸው በኋላ ተክለ ብለው ሰየሙት። ይህም አቋቋም አስደሳችና ማራኪ ነው ተብሎ የሚገመት የአቋቋም ዘዴ ነው።

አለቃ ገብረሃና በአጠቃላይ ፈጥኖ መልስ በመስጠት፣ ቃላትን በመሰነጣጠቅ፣ ሁለት ትርጉም በመስጠት፣ እናም ጠለቅ ያለ ትርጉም ያላቸውና ከተናገሩት በኋላ ቆይቶ ሊረዱት የሚቻል አገላለፆችን የሚጠቀሙ ነበሩ። አለቃ ገብረሃና በብዙ ከታወቁ የኢትዮጵያ ነገስታት ዘመን በቅርበት የኖሩና በኢትዮጵያ ሰማይ የምሁራን ሰማይ ላይም እንደ ንጋት ኮከብ ተደርገው ይታዩ ነበር።

በመቅደላ ጦርነት ዓፄ ቴዎድሮስ ከሞቱ በኋላ በደጃዝማች ተክለጊዮርጊስና በደጃዝማች ካሳ ኋላ ላይ ዮሐንስ ፬ኛ በተባሉበት መካከል ዙፋኑን ለመያዝ በተደረገው ጦርነት ደጃዝማች ካሳ ጦርነቱን ካሸነፉ በኋላ አለቃ ገብረሃናን ወደ ትግራይ በማስጠራት ፍትህን በፍትሐ ነገስት መሠረት እንዲያስተዳድሩ ጠየቋቸው። በዚህን ጊዜ አለቃ ገብረሃና ጥቂት መጻሕፍትን በብራና ላይ ጽፈው ነበር። እነዚህ የብራና ጽሑፎችም እስካሁን ድረስ በአክሱም ፅዮን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይገኛል።

አለቃ ገብረሃና ትልቅ ዝና ያገኙት በዳግማዊ ምኒልክ ፍ/ቤት ነበር። አለቃ ገብረሃና በጊዜያቸው በነበሩት ምሁራን በጣም ይታወቁ ነበር። ከእቴጌ ጣይቱና ከዳግማዊ ምኒልክ ጋር ተባብረው በመስራታቸውም ዝናቸው ተሰራጨ። መጀመሪያ አለቃ ገብረሃና እንጦጦ በሚገኘው ቤተ መንግሥት ከዚያም በቅዱስ ኡራኤልና በቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን እንዲቆዩ ተደረጉ። ነገር ግን ሀገራቸው ያለውንና በጣም የሚወዱትን ናበጋ ጊዮርጊስን በጣም ይናፍቁ ነበር። ሆኖም የሀገሩቱ ዋና ከተማ ወደ አዲስ አበባ በመዛወሩ አዲስ አበባ ለመቆየት አሰቡ። ውሎ አድሮ ግን ወደ ሀገራቸው ተመለሱ። ነገር ግን በአክሱም በጎንደር የቆዩትን ያህል በአዲስ አበባም እስከማይረሱ ለረጅም ጊዜ ቆይተው ነበር።

ዋቢ ለማስተካከል

  1. ^ Reidulf K. Molvaer, Black Lions: The creative Lives of Modern Ethiopia's Literary Giants and Pioneers,1997 The red Sea Press, Asmara, p167