ዳሪዎስ ሞዲ
ከፐርሺያ የሚሳብ የዘር ግንድ ያላቸው በዜግነት እንግሊዛዊ በትውልድ ሕንዳዊ አባቱና ከኢትዮጵያዊት እናቱ በአዲስ አበባ ከተማ ራስ መኰንን ድልድይ አካባቢ በ1938 ዓ.ም.የተወለደው ዳርዮስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ነበር፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ትምህርቱን መከታተል ቢጀምርም በወቅቱ በነበረው የተማሪዎች ንቅናቄ ሳቢያ የቅርብ ጓደኛውና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ጥላሁን ግዛው መገደልን ተከትሎ የPolitical Science ትምሕርቱን አቋርጦ ወጣ፥ በመካነየሱስ ቤተ ክርስቲያን ሥር የነበረውና በዓለም ሉተራን ፌዴሬሽን በሚረዳው የዘመኑ ታዋቂ የሬዲዮ ጣቢያ ብሥራተ ወንጌል ሬዲዮ በ1964 ዓ.ም. በመቀጠር ጣቢያውን ደርግ እስከ ወረሰበት ጊዜ ድረስ ሠርቷል፡፡ ድኅረ አብዮት በአብዮታዊት ኢትዮጵያ ድምፅና በብሔራዊ ሬዲዮ እስከ 1980ዎቹ መገባደጃ ድረስ በዜና አንባቢነት፣ በፕሮግራም አዘጋጅነት የሠራ ሲሆን፣ ጡረታ እስከወጣበት 1994 ዓ.ም. ድረስ ያገለገለው በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የውጭ ቋንቋ ዴስክ ነበር፡፡ HUMAN IMMUNO DEFICIENCY VIRUS (HIV) የሚለውን ቃል ሕዝብ ሊረዳው በሚችለው ቃል በራሱ መንገድ ተርጉሞ "ቅስመ ተፈጥሮ መከላከያ ሰባሪ በሽታ" ብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕዝብን ስለ በሽታው ያስተማረውም ይሄው ሙያተኛ ነበር፥ ለዚህ ውለታው ግን ሽልማት ቀርቶ ምሥጋና ሊደርሠው ቀርቶ ይብሱን "ያልተገቡ ቃላትን በመጠቀም" በሚል ከደመወዙ ሠማንያ ብር ተቀጥቷል። Surrogate Mother የሚባሉትን ያለ ተፈጥሯዊ የግንኙነት መንገድ በጽንሳቸው ልጅ የሚታቀፉ (ማሕጸን የሚያከራዩ ሴቶች) ጉዲፈቻ የሚል ኦሮሚፋ ቃል እና ጽንስ የሚለውን በማዋሃድ "ጽንሰ-ፈቻ" ብሎ የሰየመውም ዳርዮስ ነበር። ዳርዮስ ከቀደሙ የሙያ አባቶቹ አሃዱ ሳቡሬ፡ አሠፋ ይርጉ ብዙ እንደተማረ በዚህም ለንደን ሳይሆን ሎንዶን፡ ዋሺንግተን ሳይሆን ዋሽንግቶን ብሎ በመዘገብም ይታወቅ ነበር። ጋዜጠኛው ከሙያ አባቶቹ ያገኘውን ለራሱ ሳያስቀር ለተተኪዎቹ በማስተማር ብንያም ከበደ፡ ነጋሽ መሃመድ፡ ብርቱኳን ሐረገወይን፡ ሳምሶን ማሞ ዓይነቶቹን ሙያተኞች ምሳሌ ሆኗቸዋል። ጋዜጠኛ ዳርዮስ ሞዲ ሠኔ 13 ቀን 2007 በ68 ዓመቱ ሕይወቱ አልፏል፥ ዳርዮስ ሞዲ ባለትዳርና የሠባት ልጆች አባትም ነበር። ሠኔ 14 ቀን ወዳጅ ዘመዶቹ በተገኙበት በፈረንሳይ ጉራራ ጊዮርጊስ ቤተክርሥትያን የቀብር ሥነ-ሥርዓቱ ሲፈጸም የሙያ ልጁ ጋዜጠኛና የማስታወቂያ ባለሙያ ብንያም ከበደ እንዲህ የሕይወት ታሪኩን አንብቦታል፡-
“ጋሽ ዳሪዮስ ጋዜጠኛ ብቻ ሳይሆን የጋዜጠኞች አባትም ነበረ። ይሄ ታሪክ ብቻ ሊሆን ይችላል። ነበር ቅርብ ነው። ነበር እያልን ዳርዮስን ብቻ ሳይሆን ሙያውንም አብረን እንቅበረው።
በፒያሳ ራስ መኮንን ድልድይ፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ፎቶ ቤት ሞሪስ እልቪስን የከፈቱት የሚስተር ሞዲ ጉስታቭ ልጅ ነው፤ ዳሪዮስ ሞዲ።
በትውልድ ፐርሺያዊ በዜግነት እንግሊዛዊ ከሆኑት ከሚስተር ጉስታቭ እና ከወ/ሮ አማረች መኩሪያ ታህሳስ 12 ቀን 1939 ዓ.ም እዚያው ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ ተወለደ።
የድርሰትና የግጥም ዝንባሌ የነበረው ዳሪዮስ ሞዲ ማንበብ፣ ሁኔታዎችን በጥልቀት ማስተዋልና መመርመር የጀመረው ከልጅነቱ ጀምሮ ነው።
በኢትዮጵያ ስር ነቀል ለውጥ እንዲመጣ ሲታገሉ ከነበሩት ተማሪዎች በተለይም ከጥላሁን ግዛው ጋር ለአንድ አላማ ተሰልፈው በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ላይ ቢቆይም የጥላሁን ግዛውን መገደል ተከትሎ ድርጊቱን በፅኑ ካወገዙት አስር ጓደኞቹ ጋር የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን ጥሎ ወጥቷል።
ዘመኑም 1962 ዓ.ም ነበር። በወቅቱ በነበረው መንግሥት አመለካከቱ ያልተወደደለት ዳሪዮስ፣ ድፍን ሁለት ዓመት ሙሉ ስራ የሚቀጥረው አላገኘም ነበር።
ይሁንና በግሉ የትርጉም ስራዎችን ይሰራ ስለነበር በ1964 ዓ.ም በብስራት ወንጌል ራዲዮ ጣቢያ ለመቀጠር ምክንያት ሆነው። ህይወቱ መስመር ያዘ፡- በመልካም ፀባይ እና ባህሪዋ የቁንጅና ጣሪያ ከሆነችው መሰረት ኃይሌ /መሳይ/ ጋር ትዳር መሰረተ። ትዳሩም ፀንቶ አራት ወንድ ልጆችን እና ሶስት ሴት ልጆችን አፈራ።
ዳሪዮስ ሞዲ ለሬዲዮ የተፈጠረ ምሉዕ በኩልዔ የሆነ ጋዜጠኛ ነበረ። ተስምቶ የማይጠገብ፣ እያነበበ የሚስረቀረቅ የሬዲዮ ሞገድን የሚገዛ ባለግርማ ድምፅ የታደለው ዳሪዮስ ሞዲ፣ ከዜና ባህሪው ተነስቶ አነባነቡን የሚከተል እንከን አልባም ዜና አንባቢ ነበር።
መንግሥታት በተለዋወጡ ቁጥር የሚሉት ጎልቶ ይደመጥላቸው ዘንድ የሚዲያው ልሳንና የድምፅ ሞገድ ዳሪዮስ ነበር። እንደየጊዜው የአዳዲስ ምዕራፍ መሸጋገሪያ ድልድይ ድምፅ ሆኖም አገልግሏል። እስከ ዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ ሚዲያ ስራ ውስጥ እንደ ዳሪዮስ አይነት የትርጉም ጌታ አልተገኘም።
ዳሪዮስ ዘንድ በይመስለኛል እና ይሆናል በሚል አቻ ትርጉም አይገኝም። የቀደምት አባቶቹን መዝገብ እየፈተሸ፣ ለዘመናዊው አለምም እንዲስማማ የራሱንም የትርጉም መንገድ እየፈለገ የሚማስን የቃላት ዲታ እና ታላቅ ሙያተኛ ነበር።
የራሱን ትርጉም የሕዝብ ቋንቋ ማድረግ የቻለ፣ የቋንቋ ምሁራንም ደግመው ደጋግመው የሚመሰክሩለት የትርጉም መምህር ነበር። አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ጀርመንኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጣሊያኒኛ የመተርጎም ብቃት የመነጨው ካልተቋረጠ የንባብ ብቃቱ ነው።
ስራው ላይ እንዳቀረቀረ እስከወዲያኛው ያንቀላፋው ይህ ሰው በቁሙ አስታውሶ፣ ሙያዊ ልቀቱን መዝኖ መሸለም ባልተለመደበት ሀገር እንደዋዛ ኖሮ ማለፉን ለምናውቅ ለኛ የእግር እሳት ነው።
በብስራተ ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያ የጀመረው የሬዲዮ ጋዜጠኝነት ሕይወቱ በኢትዮጵያ ሬዲዮ እና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ለ30 ዓመታት ቢቀጥልም ይከፈለው የነበረው ደሞዝ የሰውየውን አስደናቂ ችሎታና የሙያ ልቀት የሚመጥን ቀርቶ ለወር አስቤዛ የማይበቃ ነበር። እንዲህም ሆኖ ህይወት ለዳሪዮስ ሬዲዮ ነው። ጡረታም ወጥቶ የናፈቀውን ሬዲዮ ለተወሰነም ጊዜ ቢሆን በሸገር እና በሬዲዮ ፋና ቀጥሎበት ቆይቷል።
ዳሪዮስ ሞዲ ወር ጠብቆ ከሚያገኘው ከሶስት አሃዝ ባልበለጠ ደሞዝ ራሱን እና ቤተሰቡን ለማስተዳደር ቢቸገርም ያን ወርቃማ ድምፁን ግን ለማስታወቂያ ለማዋል፣ ማስታወቂያ ሊሰራበት ግን ፈቃደኛ አልነበረም።
ዜና ላይ የሚሰማ ድምፅ እንዴት ሆኖ ሸቀጥ ይተዋወቅበታል ሲል ይሞግታል። ይህ በራሱ የሙያውን ሥነ-ምግባር መጣስ ነው ሲል ለሙያው መርህ እና ልዕልና አጥብቆ ይከራከራል።
የመጨረሻዎቹ ሶስት ዓመታት ለዳሪዮስ ጥሩ አልነበሩም። ለዘመናት ማልዶ ከስራው ገበታው የማይታጣው ዳሪዮስ ህመም ደጋገመው። እንደ ልብ መተንፈስ ተሳነው። በኦክሲጅን እየተረዳ ቆየ።
ዳሪዮስ የልብ ትርታው ቀጥ የምትል የምትመስለው ኦክሲጅን ሲያጣ ብቻ አልነበረም። ካላነበበና ዜና ካልሰማ እስትንፋሱ ያለ አይመስለውም።
ጋሽ ዳሪዮስ ሰውን ቶሎ የማይቀርብና ከቀረበም የእድሜ ልክ እውነተኛ ወዳጅ የሚሆን፣ ትሁት ደግ እና እውቀቱን ያለ ስስት የሚሰጥ ታማኝ ሰው ነበር።
እንደው በቀዝቃዛው በክረምቱ ሰሞን እንከተላለን አንድ ጎበዝ ቀድሞን አይ ጉድ መፈጠር ለመሰነባበት ዳሪዮስን መቼም ማንም አይደርስበት ሮጥን ሮጥን የትም አልደረስንም ማን ይከተለዋል ውድ ዳርዮስን ብለን ለመሰነባበት ከእግዚአብሔር አስገራሚ ስራ አንዱን እንደ ማሳረጊያ እንይ።
ለ43 ዓመታት ከጎኑ ያልተለየችው፣ ለትዳሯም ለልጆቿም ህልውና የደከመችው፣ ልጆቿ እንኳን አይተዋት ስሟ ሲጠራ የሚንሰፈሰፉላት መሳይ፣ ልክ የዛሬ አራት ወር ከሁለት ቀናት ታማ አርብ እለት ሆስፒታል ገባች።
ዳሪዮስም ለመጨረሻ ጊዜ ሆስፒታል የገባው በዕለተ አርብ ነበር። አርብ ለቅዳሜ አጥቢያ ከሌሊቱ 11 ሰዓት በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት ባለትዳሮቹ ነፍሳቸው ተለየች።
ልክ እንደዛሬው በዚህ ስፍራ መሳይን ሸኘናት። ዳሪዮስ ተከተላት። አርብ፣ ቅዳሜ እሁድ በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት ይህችን አለም ተለዩ።”