ደብተራ ማለት ድንኳን ማለት ነው፤ አንድም ካህንን አገልጋይ መዘመር አንድም በእውቀቱ ከፍ ያለ ሊቅ ማለት ነው።

●የደብተራ ትርጓሜ በመዛግበተ ቃላት ወጥበባት ደስታ ተክለ ወልድ በመዝገበ ቃላቸው፡-

 ‹‹ደብተራ – ድንኳን፡፡ ደበተረ – ደብተር ዘረጋ፣ ጻፈ፣ ከተበ ፡፡ ተደበተረ – ተዘረጋ፡፡ ደብተራ – የድንኳን ስም፡፡ ደብተራ – ዜማ. ቅኔ፣ ሳታት (ሰዓታት) የሚያውቅ፣ በደብተራ (በድንኳን) ውስጥ የሚመራ፣ የሚቀኝ፣ የሚዘምር፣ መንፈሳዊ አገልጋይ፣ ካህን፣ አወዳሽ ሳታት ቋሚ፡፡ ደብቴ – ከፊለ ስም ወይም ቁልምጫ፣ የደብተራ ወገን፣ የኔ ደብተራ ማለት ነው፡፡›› ይሉናል፡፡

● #ግእዙም፡-

‹‹ደብተረ› ማለትን በአወራረዱ ሕግ በተንበለ ቤት አስገብቶ ሲያበቃ ‹‹ተከለ›› ሲል ይተረጕምና ለድንኳን ይሰጠዋል፡፡

ግእዝ ድንኳን ለሚለው ቃል ከደብተራ በተጨማሪ ኀይመትና ደበና ማለትን ይጠቀማል፡፡ ደበና የንጉሥ ድንኳን የሚጠራበት ስም ነው፡፡ ደበናንሳ (ባለእጅ) የሚለው ቃል ከዚህ ስም ጋራ ስለመያያዝ አለመያያዙ አላውቅም! ●የፕ/ር ሥርግው አማርኛ የቤ/ክ መዝገበ ቃላት፡- ‹‹ደብተራ የቃሉ ቀጥተኛ ትርጕም ድንኳን ማለት ነው፡፡ ግን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቅኔ ማኅሌት የያሬድን ዜማ የሚዘምር፣ የሚመረግድ እንዲሁም ቅኔን የሚቀኝ ደብተራ ይባላል፡፡›› ብሎናል፡፡