ይርጋ ዱባለ የኢትዮጵያ ታዋቂ ዘፋኝ ሲሆን ብዙ ባህላዊ የሙዚቃ ስራወችን በማቅረብ ይታወቃል።

ይርጋ ዱባለ

የህይወት ታሪክ ለማስተካከል

ይርጋ ዱባለ የተወለደው ጎንደር ከተማ አርባያ በምትባል መንደር ግንቦት 16 ቀን 1922 ዓ.ም ነው። አባቱ ከሌላ የወልዷቸው በርካታ ልጆች ቢኖሩም ከአንድ አባት የተወለዱ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ግን ነበሩ። እንዳጋጣሚ ግን ሁለቱም አሁን በህይወት የሉም።

ይርጋ ዱባለ የ10 ዓመት ልጅ እያለ፣ ታናሽ ወንድሙ ባዘዘው ዱባለ ደግሞ የ 7 ዓመት ልጆች ሆነው ማሲንቋቸውን ይዘው ሲጫወቱ “እኒያ ልጆች የታሉ?” እየተባሉ እየተጠየቁ ጠረጴዛ ላይ እያወጧቸው ነበር የሚያዘፍኗቸው። ወደ አዲስ አበባ ተወስዳችሁ ትዘፍናላችሁ ሲባሉ እናታቸው “ልጆቼን ሊቀሙብኝ ነው” በሚል ስጋት አባ ጊዮርጊስ የሚባል ቦታ ወስደው የደበቋቸው። ይርጋ እንደሚለው በወቅቱ ደጃዝማች አርአያ ገ/መድህን ወረዳ አስተዳዳሪ ነበሩና ህጻናቱን ድምጻዊያን በደንብ ጠብቀዋቸዋል። ከይርጋ በድምጽም በመሰንቆ ጨዋታም የሚበልጠው ባዘዘው ግን ወደ ስምንተኛ ዓመት ዕድሜው ሊሻገር ሲል ሞተ። “ጥላ ወጊ ገደለብኝ.. ደጃዝማች አርአያ ገ/መድህን ግን ቱልቱላና ጥሩምባ እያስነፉ በክብር አስቀብረውታል” ይላል ይርጋ ስለወንድሙ ሲናገር። እሱ ከሞተ በኋላ ይርጋ ከአባ ጊዮርጊስ ወደ ጎንደር ተመለሰ።

ሶስት ልጆች ወልደው አንድ ብቻ የቀራቸው የይርጋ እናት ልጃቸውን ቶሎ ድረው የልጅ ልጆች ማየትን ቸኮሉ። እናም የስድስት ዓመት ልጅ አጩለት። ወዳጅ ዘመድ ተቃውሞ ነበር። “ይህች ህጻን ምን ልትሆን ነው? ይልቅ አንድ ልጅሽ ነውና ቶሎ ለመውለድ የምትበቃውን ሴት ዳሪው” ብለው መከሩ፣ እናት አልሰሙም። ከነ ሞግዚቷ በበቅሎ ተጭና የመጣቸውን ሙሽራ የልጃቸው ሚስት እንድትሆን በአደራ ተቀበሉ። ጎረምሳው ይርጋም እንዴት ይሆናል ብሎ ማሲንቆውን አንጠልጥሎ የቤተሰቡን ሃብት ንብረት ትቶ ከተማ ገባ – እየዘፈነ ሊኖር።

ከከተማ ሲመጣ ለዚያች ህጻን ከረሜላ ይዞ ይመጣል። “አያያ መጣ” ትላለች በእናቱ ቤት በሞግዚት የተቀመጠችው የወደፊት ሚስቱ። እሷ ታላቅ ወንድሟ ነበር የሚመስላት። ደስታ ከረሜላውን እየሰጠ፣ እያሻሸ እያጫወተ እንድትለምደው ያደርግ ነበር። እሷም እያደገች መጣች። በመጨረሻም እሱ ሌላ ሴት ሳያውቅ፣ እሷም ሌላ ወንድ ሳታውቅ ተጋቡ። 46 ዓመታትም በትዳር ኖሩ፣ አስር ልጆችም አፈሩ፣ ከነዚያ ውስጥ አራቱ ግን በህይወት የሉም። ስድስት ልጆችና አምስት የልጅ ልጆች ዛሬም አሉ።

ከ1955 በኋላ ይርጋ ዱባለ ባለቤቱን ጎንደር ከተማ አስቀምጦ ወደ አዲስ አበባ መጣ። ሽለላና ቀረርቶ ስለሚችልም የምድር ጦር ሰራዊት ሊቀጠር ነበር ሃሳቡ፡ የሚቀጠርበትን ደሞዝ ሲሰማ ግን ሊተወው ፈለገ – 70 ብር በወር ነበር። እምቢ ሲል 300 ብር እንስጥህ አሉት፣ እሱንም አልፈለገም፣ ሌላው ቀርቶ ሠርግ እዚያው ጎንደር ቢሰራ፣ ሽልማቱ ብቻ ከሶስት መቶ ይበልጥ ነበር፣ ስለዚህ አዲስ አበባን ትቶ ወደ ጎንደር ተመለሰ። ጦር ሰራዊቶች ግን ዝም አላሉትም ጎንደር ሄደው አስረው አመጡት። እየጠፋ ሲመለስ፣ እንደገና እያሰሩ ሲያመጡት .. ቀስ በቀስ ለመደውና አዲስ አበባ ቀረ። በቀዳማዊ ሃይለሥላሴ ጊዜ የነበሩ ሚኒስትሮች ይወዱት እንደነበር የሚናገረው ይርጋ፣ በርካታ ጠመንጃና ሽጉጦች በሽልማት መልክ ይሰጡኝ ነበር ይላል። እሱ ግን አንዲት ሽጉጥ ብቻ አስቀርቶ ሌላውን ለነጋዴዎች እንደሸጠ ይናገራል።

ይርጋ በጣም የታወቀበት “የፍየል ወጠጤ” ተብሎ የሚጠራው ሽለላ ነበር። ይህን ሽለላ በ1957 ዓ.ም አስመራ ውስጥ ነበር የተጫወተው። ይርጋ አስመራ የሄደው ለሠርግ ሥራ ነበር – ግን ማምሻውን አንድ ቡና ቤት ገብቶ ሳለ፣ ወቅቱ ጦርነት ጦርነት የሚሸትበት ጊዜ ነበረና ይርጋ ይሸልል ጀመር ..

በአዳፍኔ ጠመንጃ፣ ወንዝ የሚያሻገር

በኤም ዋን ብረት ሰባብሮ የሚጥል

ሲመጣ እንደንፋስ የሚወረውር፣

በተላከው ጠረፍ የማያሳፍር፣

ያባ ጠቅል አሽከር .. ..እያለ ይፎክራል። ያን ጊዜም አንድ ሰው በተደጋጋሚ ይርጋን ይሸለም ጀመር።

ከዚህ በኋላ የተፈጠረውን ይርጋ እንዲህ ሲል ያስታውሳል “ሰውየው ደጋግሞ ሸለመኝና ፣ መጨረሻ ላይ እፈልግሃለሁ ብሎ ወደ ውጭ አወጣኝ.. ውጭ አንድ ጂፕ መኪና ቆሟል .. ግባ አለኝ፣ ምን አጠፋሁ ብዬ ደነገጥኩ። ሰውየው ግን ሽለላዬን እንደወደደውና ወደፊትም ሊያሰራኝ እንደሚፈልግ ነግሮኝ፣ ሆቴል ተከራየልኝ፣ በማግስቱም ጂፕ መኪና ተላከልኝና ወታደሮች ይዘውኝ ሄዱ – ወስደውም ያ ማታ የሸለመኝ ሰው ፊት አቆሞኝ፣ ደነገጥኩ፣ በሚሊተሪ ልብስ ተንቆጥቁጦ ቆሟል .. ማን መስላችሁ ..ጄኔራል አማን አንዶም!”

እናም በማግስቱ ጃንሆይ ምጽዋ ይመጣሉና እዚያም ትሸልላለህ ተባልኩ፣ እኔም አዲስ ግጥም ጽፌ አደርኩ፣ የምጽዋው ዝግጅትም በሬዲዮ ተላለፈ፣ ያኔ ነው ያ ሽለላ የተቀረጸው።

የፍየል ወጠጤ፣ ልቡ ያበጠበት፣

እንዋጋ ብሎ ለነብር ላከበት፣

የማትረባ ፍየል ዘጠኝ ትወልዳለች -

እነሱም ያልቃሉ እሷም ትሞታለች” አልኩ።

ይርጋ እንደሚለው ይህ ዘፈን ለሱዳን እና ለሶማሌ የተዘፈነ ቢሆንም፣ ደርግ ሥልጣን ሲይዝ ለራሱም ተጠቀመበት። ከዚያ በኋላ ለውጥ መጣ፣ ይርጋም ጎንደር ላይ ሰርቷቸው የነበሩት 13 ቤቶች ተወረሱበት። እሱም ጠቅልሎ አዲስ አበባ ገባ። በኋላም በልጅነቱ ከአባቱ የሰማውን ግጥም፦

“የአሳማ ገበሬ የዝንጀሮ ጎልጓይ የጅብ ዘር አቀባይ …

ሁሉም እንብላው ባይ የለውም ገላጋይ”

የሚለውን ፉከራ ማሰማት ሲጀምር ግን ነገር መጣበት። ያን ጊዜም እስራኤል ኤምባሲ ገብቶ ቪዛ በመጠየቅ ወደ እስራኤል ሄደና መኖር ጀመረ። እስራኤል በገባ በስምንት ወሩ ያለፈው መንግስት ሥርዓት በማብቃቱ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ።

ከዚያ ወዲያ አሜሪካም አውሮፓም እያለ “የሰው የለው ሞኝ”ን በመጫወት ቤተስቡን ያስተዳደር ገባ። ይርጋን ለየት የሚያደርገው የምሽት ክበብ ሰርቶ አለማወቁ ነው። ሰርግ ወይም ግብዣ ወይም ትልቅ የሙዚቃ ዝግጅት ላይ እየሰራ ነው ልጆቹን ያሳደገውና ንብረት ያፈራው።

የዛሬ ስምንት ዓመት ታዲያ ይርጋ ዱባለ በነርቭ በሽታ ተይዞ አልጋ ላይ ዋለ። የበሽታውን ምክንያት ሲናገር “22 ማዞሪያ አካባቢ ዮሃንስ ክትፎ ቤት አጠገብ ቤት ለመግዛት የከፈልኩትን 200ሺ ብር የተቀበለኝ ሰው ስለካደኝ በብስጭት በሽተኛ ሆንኩ” ነው ያለው። ከጊዜ ብዛት ግን በተለይ ፕሮፌሰር ጉታ በሚባሉ ሃኪም ድጋፍ እየተሻለው መጥቶ ነበር። ውስኪና ጮማ ትቶ አትክልት ብቻም እየተመገበ ህይወቱ እስካለፈበት ቀን ድረስ ቆይቷል። የጎንደር ልማት ማህበርም ለአገልግሎቱ ትልቅ ዝግጅት አድርጎ ስለሸለመው ሁልጊዜ ምስጋናውን እንዳቀረበ ነበር። ሰው ምንም ቢኖር ከሞት አይቀርምና በተወለደ በ 81 ዓመቱ፣ ግንቦት 8 ቀን 2003 (ሜይ 16/2011) 82 ዓመት ሊሞላው አንድ ሳምንት ሲቀር ከዚህ ዓለም አልፏል። የቀብሩ ሥነ ስር ዓትም በማግስቱ ግንቦት 9 ቀን አዲስ አበባ ከተማ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።

ስለባህል ሙዚቃ ተጫዋች ይርጋ ዱባለ ባለቤቱ ወ/ሮ እናት ምስክር በህይወት እያለ እንዲህ ሲሉ ምስክርነት ሰጥተው ነበር “የጋሼ ይርጋን ባልነት ተዉት፣ ገነት ነው። መድሃኒዓለምን ፣ ብር ሰርቶ አምጥቶ ኪሱ እንኳን አይከትም፣ ሁሉንም እንቺ ነው የሚለኝ፣ እኔንም እንኳ ንፉግ አደረገኝ፣ እንዲህ ሰርቶ አምጥቶ እየሰጠኝ እንዴት ነው የማባክነው እያልኩ አስባለሁ፣ የሚታገዝ ቢሆን በሽታውን ባገዝኩት፣ ይርጋን የመሰለ ባህል አይገኝም፣ አይማታ፣ አይቆጣ፣ አይነዛነዝ፣ አያሳርዘነ፣ አያስርበነ፣ .. እኔንም እንደ ሚሽት፣ እንደ እህት እንደ እናት ነው አንቀባሮ የያዘኝ፣ ምቾተኛ ነኝ፣ ማጣትን አላውቀውም”

የስራ ዝርዝር ለማስተካከል

ማጣቀሻወች ለማስተካከል