የጊንጥ ዱላ
የጊንጥ ዱላ የግብጽ ጥንታዊ መንግሥት ቅርስ ሲሆን በነቀን (ሄራኮንፖሊስ) ከተማ የተገኘ ስብብር የዱላ ራስ ነው። ከበሀ ድንጋይ ተሠራ። በትልቁ ክፍል የተቀረጸው ትርዒት ንጉሥ ጊንጥ ስለሚያሳይ፣ ቅርሱ «የጊንጥ ዱላ» ተብሏል።
ይህ «ንጉሥ ጊንጥ» ከፈርዖኖች ዘመን አስቀድሞ በግብጽ የነገሠ አለቃ መሆኑ ይታወቃል። ጥንታዊው መንግሥት በ«ሔሩ ወገን» እንደ ተመሠረተ ሁሉ፣ ዱላው በአረመኔው አምላክ በሔሩ ቤተ መቅደስ ፍርስራሽ በ1890 ዓ.ም. ተገኝቶ ነበር። በተቀረጸው ትርዒት፣ አለቃው ከሰው ረጅም ሆኖ መኮትኮቻም ይዞ በራሱ ላይ «የላይኛ ግብጽ ነጭ ዘውድ» አለበት። አጠገቡ የጊንጥ ምልክት አለ፤ የዚሁ ቃል ግብጽኛ አጠራር ምናልባት «ሠልክ» ነበር።
አለቃውን የሚያገልግሉት ሰዎች በመነጻጸር በጣም አጭር ሆነው ያሳያል። ከሱም በላይ የዓላማዎች ተርታ ሊታይ ይችላል። ከነዚህ ሁለቱ ዓላማዎች «የሴት ወገን» ምልክት እሱም «የሴት እንስሳ» (አዋልደጌሳ ወይም ቀበሮ) አለባቸው። ከየአላማው ደግሞ እንደ ወፍ የሚመስል ፍጡር በአንገት ይሰቀላል። የዚህ ትርዒት ትርጉም በእርግጥ ባይታወቅም፣ በጥንታዊ ግብጽ ለመግዛት የተነሡት ወገኖች ታሪክ እንደሚነካ ይገመታል።