==ለደብረ ሥልጣንኢየሩሳሌም አባቶች== [1]

ማኅበሩ በጎሣ ምክንያት መጣላቱ እንደማይረባቸው፤ አንድነታቸውን አጽንተው በበለጠ ክብር እንዲኖሩ ለማኅበሩ የጻፏቸው ምክርና ተግሳጽ።

የተላከ ከእቴጌ ጣይቱ፤ ብርሃን ዘኢትዮጵያ ይድረስ ከማህበረ ዴር ሥልጣን ወደብረ ገነት ዘኢየሩሳሌም

እጅጉን እንዴት ናችሁ፡ እኔ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ፡፡ እስካሁንም አለመላኬ ጠብና ድብልቅልቅ እያደረጋችሁ ባትስማሙ ነው። አሁን ግን መስማማታችሁን አድነታችሁን ብንሰማ እጅግ ደስ አለን። እንግዴህ እንዲህ ከተስማማችሁልን አንድነታችሁ ካማረ እናንተን አባቶቻችንን አትርሱን ለማለት እንተጋለን። እናንተም እዘኑ ሐዘናችሁ እንኳን ለኛ ለሌላም ሰው ትተርፋላችሁ። እኔ ጎጃሜ ነኝ፣ እኔ ትግሬ ነኝ፣ እኔ ሸዋ ነኝ እያሉ መጣላቱ ቀርቶ ፩ ልብ ሆናችሁ ዳዊታችሁን ድገሙ። ወትሮ የሚቸግራችሁ በገንዘብና የታዳጊ እጦት ነበር። እኛ ደህና ከሆን እንግዲህ ይህ ሁሉ አይቸግራችሁም። ታኅሣሥ ፴ ቀን ፲፰፻፺፪ ዓመተ ምሕረት አዲስ አበባ ከተማ ተጻፈ።

የግርጌ ማኅተም፡ ዝማኅተም ዘእቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዮጵያ



የራስጌ ማኅተም፡ ዝማኅተም ዘእቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዮጵያ

የተላከ ከእቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዮጵያ፤ ይድረስ ከማህበረ ዴር ሥልጣን ወደብረ ገነት ዘኢየሩሳሌም፣ እንዴት ሰንብታችኋል፡ እኔ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ።

እናንተ ብትስማሙ እርስ በርሳችሁ ብትፋቀሩ አንድነትችሁን ብታፀኑ ይሻላል እንጂ ትግሬ የብቻ ነው፣ ሸዋ የብቻ ነው፣ ቤገምድር ጎጃም የብቻ ነው እያላችሁ ጎሣ እየለያችሁ ብትጣሉ ምን ትረባላችሁ። እኛስ በኢየሩሳሌም ነገር ይህንን ያህል መድከማችን ያነን ያህል ብር ባንክ አግብተን የዚያን ወለድና ከቤቱ የሚወጣውን ክራይ መስጠታችን እንዳትቸገሩ የሰው ፊት እንዳታዩ ያነን እየበላችሁ ለኛም የጌታችን ደም ከፈሰሰበት ላይ ዳዊት እንድትደግሙልን እንድታዝኑልን እናንተም ፩ነታችሁ እንዲጸና ብለን ነው እንጂ ገንዘቡ ተርፎ ባገራችን በኢትዮጵያ ለምንሰጠው ሰው አጥተን አይደለም። አሁንም ስለ እግዚአብሔር ብላችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተፋቀሩ፡ ለኛም ዳዊት ድገሙልን እዘኑልኝ። ሳትቸገሩ እንዴት የድፍን አውሮፓ መሳቂያ ትሆናላችሁ። አሁንም ይኸው እማሆይ ወለተ ተክሌ መቃብሬ ከዚያው ይሁን ብላ መጥታለችና አደራችሁን ምኑም በምኑም ነገር እንዳታስቀይሟት። እንግዲህ እሷ እንዲህ አደረጉኝ ብላ የላከችብኝ እንደሆነ እናንተንም እጣላችኋለሁ እኔንም እንዳታስቀይሙኝ። ሰኔ ፳፱ ቀን ፲፱፻ ዓመት አዲስ አበባ ከተማ ተጻፈ።

ዋቢ ምንጮች ለማስተካከል

  1. ^ ማቴዎስ፣ አባ፤ “ደብረ ሥልጣን በኢየሩሳሌም” (፲፱፻፹፰ ዓ/ም)፤ ገጽ 48