የኅልውና ድንጋጤ
የኅልውና ድንጋጤ በኅልውነት ፍልስፍና እያንዳንዱ ግለሰብ ባለው የኅልውና ነጻነት ምክንያት የሚሰማው መሰረታዊ የመንፈስ አለመረጋጋት(ፍርሃት) ነው።
ለምሳሌ አንድ ሰው ከገደል ጫፍ ላይ ቢቆም ሁለት ድንጋጤወች ይጋፈጡታል፣ አንደኛው «"ወድቄ ብከሰከስስ"» የሚል ሲሆን ሁለተኛውና ለምንነጋገርበት ርዕስ ጠቃሚ የሆነው ደግሞ «"ምናልባት እራሴን ብወረውርስ"» የሚል ፍርሃቻ ናቸው ። በዚህ አጣብቂኝ ግለሰቡ "ምንም የሚይዘኝ ነገር የለም" ወይም ደግም "በተፈጥሮየ እራሴን እንዳልወረውር የሚጠብቀኝ እንዲሁ በተቃራኒው እራሴን እንድወረወር የሚገፋፋኝ እድል እጣ ፈንታ የለኝም፣ ሁለቱም እራሴ በማደርገው ምርጫ የሚወሰን ነው" የሚለውን መሰረታዊ የሰው ልጅ ነጻነት ይረዳል። ይህ የመመረጥ ሙሉ ነጻነትና የሚያስከተለው ሙሉ ሃላፊነት በሰው ልጅ ላይ ድንጋጤን ይፈጥራል። የኅልውና ድንጋጤ እንደሌሎች የፍራቻ አይነቶች ሳይሆን አብሮ ከሰው ልጅ ሙሉ የመምረጥ ነጻነት ጋር ምንጊዜም የሚገኝ ነው።