የቁሶች ጥናት ሳይንስ ወይም ምህንድስና

የቁሶች ጥናት ሳይንስ ወይም ምህንድስና በሲቪል ምህንድስና ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ሚና ይይዛል። የቁሶች ጥናት ሳይንስ ወይም ምህንድስና የቁሶችን ተፈጥሮዋዊ ባህሪ የሚያጠና የሳይንስ ወይም የምህንድስና ዘርፍ ነው። ለግንባታ ከሚውሉ ቁሳቁሶች ውስጥ ኮንክሪት፣ የአስፋልት ኮንክሪት፣ እንደ ብረት እና አልሙኒየም ያሉ ጠንካራ ብረታ ብረቶች ፣ የፕላስቲ ውጤቶችና የመሳሰሉት ይገኙበታል። የቁሶች ጥናት የግንባታ አካላትን ከተለያየ ጥቃት ለመከላከል የሚውሉ ቅባቶችና የመከላከያ ንጣፎችን፣ እንዲሁም አንድን የብረት አይነት ከሌላ የብረት አይነት ጋር በማደባለቅ ለግንባታ ተስማሚ የሆነ ሌላ አይነት የብረት አይነት ማምረት የመሳሰሉ ስራዎችንም ያጠቃልላል።

የቁሶች ጥናት የትግበራ ፊዚክስና (applied physics) የኬሚስትሪ እውቀቶችን የያዘ የምህንድስና ዘርፍ ነው። በቅርቡ እየተስፋፋ የመጣው የናኖ ሳይንስ ወይም ቴክኖሎጂን (ናኖ ሳይንስ የአንድን ቁስአቶምና የሞሎኪዮል አወቃቀር በመቀየር በተፈጥሮ የማይገኙ ለየት ያለ ባህሪ ያላቸውን ቁሶች ለመስራት የሚደረግ ጥረት ነው) ደረጃ ተንተርሶ በአሁኑ ጊዜ የቁሶች ጥናት ከፍተኛ የሆነ የምርምር ድርሻን ይዞ ይገኛል። የቁሶች ጥናት ምህንድስና በምርምር ምህንድስናና የግንባታ አካላት ከጥቅም ውጪ የመሆን መንስኤን ለማጥናት በሚደረጉ ስራዎች ላይ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።