የማርያም ቅዳሴ ገፅ ፲፫
ዘቅዱስ ሕርያቆስ
የማርያም ቅዳሴ ገፅ ፲፫ | |
---|---|
ዘቅዱስ ሕርያቆስ |
፺፪ ፤ ወዮ ካንቺ የተገኘ ጽዋ በማመን ከእርሱ ለሚጠጡ ሰዎች ጥበብን የሚገልጽ ሕይወትንም የሚገልጽ ነው ።
፺፫ ፤ ወዮ ካንቺ የተገኘ ጽዋ በማመን ከእርሱ ለማይጠጡ ሰዎች የሚያሰክርና የሚያፍገመግም የሚጥልና ኃጢአትን ስለማስተስረይ ፈንታ ኃጢአትን የሚጨምር ነው ።
፺፬ ፤ አሁንም ለአንተ ምስጋና ይገባሃል ለመንግሥትህም ምስጋና ይገባል እያልን እናመስግነው ። ከንጹሕ ዕጣን ጋር ምስጋና እናቀርብልሃለን ።
፺፭ ፤ (በዚህ ጊዜ ዕጣኑን ያሳርግ ።) አቤቱ በመንግሥትህ አስበን ።
፺፮ ፤ በጎ ሀብት ሁሉ ፍፁም ዕድልም ሁሉ ከእርሱ የሚገኝ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆነ ከኃጢአት ብቻ በቀር የሰውን ሕግ ሁሉ ፈፀመ የዕብራውያንንም ሕግ ተማረ ።
፺፯ ፤ ከዮሐንስ ዘንድም ተጠመቀ በገዳም ተፈተነ ተራበም ተጠማም ተአምራትንም አደረገ ።
፺፰ ፤ ሰውነቱን ለሞት በሰጠባት በዚያች ሌሊት ለደቀ መዛሙርቱ በብዙ ምልክት አመለከተ የሕማሙንና የስቅለቱን የሞቱን ነገር በሦስተኛውም ቀን የመነሣቱን በሥጋና በነፍስ በአጥንትና በደም ቀድሞ እንደ ነበረው ፣ ደቀ መዛሙርቱ ከርሱ ጋር በቀኙና በግራው ሳሉ ፍጥረቱ ክርዳድ የሚሆን ከስንዴ ጋር የተቀላቀለ ያስያዘው ይሁዳም ከነርሱ ጋር የተቆጠረ ሆኖ ነበረ ።