ውክፔዲያ:ታሪካዊ ማስታወሻዎች/ጥር 13
ጥር ፲፫ ቀን፣
- ፲፰፻፷፬ ዓ.ም.፣ ደጃዝማች ካሳ ምርጫ (አባ በዝብዝ) በአክሱም ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ስመ መንግሥታቸው "ዮሐንስ ራብዓዊ" (ዮሐንስ ፬ኛ) ተብሎ፣ በጳጳሱ በብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ እጅ ተቀብተው በሥርዓተ መንግሥት ንጉሠ ጽዮን፣ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብለው ነገሡ። በታሪክ እንደተመዘገበው በዚሁ ንግሥ ምክንያት ሦስት ቀን በዓል ሆኖ፣ ለግብር ፬ ሺህ ሰንጋ ታርዶ፣ ፶ ጉንዶ ማር የፈጀ፣ ፻፶ ሺህ ገንቦ ጠጅ ቀርቦ፣ በደስታ ሲበላ ሲጠጣ ሰንብቷል።
- ፲፱፻፴፫ ዓ/ም የፋሺስት ኢጣሊያን ሠራዊት ጠራርጎ ለማስወጣት የተቀጣጠለውን ዘመቻ ከፍጻሜ ለማድረስ ከሱዳን ድንበር ወደ ኢትዮጵያ የዘለቁት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ አርበኞችና የእንግሊዝ ጦር፣ በኦሜድላ ላይ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ የሆነውንና የይሁዳ አንበሳ ከመሐሉ የሚገኝበት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማን ተከሉ፤ አውለበለቡ።
- ፲፱፻፵፬ ዓ.ም. ለአዲስ አበባ ሕዝብ የውሃ አገልግሎት የሚሰጠው የገፈርሳ ግድብ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተመረቀ።
- ፲፱፻፶፬ ዓ.ም. ኢትዮጵያ ሦስተኛውን የአፍሪቃ እግር ኳስ ውድድር የግብፅን ቡድን አራት ለ ሁለት አሸንፋ ዋንጫውን ተሸለመች። ለኢትዮጵያ ቀዳሚውን ግብ ያስቆጠረው የቴሌው ግርማ ዘለቀ ሲኾን፣ የጊዮርጊሱ መንግሥቱ ወርቁ በ፹፬ኛውና በ፻፲፯ኛው ደቂቃ ሁለተኛና አራተኛውን፣ ኢታሎ ቫሳሎ በ፻፩ኛው ደቂቃ ሦስተኛውን ለማስገባት ችለዋል። ያልተደገመውንና ሕዝቡም እየናፈቀ ያለው የአፍሪቃ ዋንጫ ለኢትዮጵያ ያስገኙት ፩. ጊላ ሚካኤል ተስፋ ማርያም ፪. ክፍሎም አርአያ ፫. አስመላሽ በርሔ ፬. በርሔ ጎይቶም ፭. አዋድ መሐመድ ፮. ተስፋዬ ገብረ መድኅን ፯. ግርማ ዘለቀ/ተክሌ ኪዳኔ ፰. መንግሥቱ ወርቁ ፱. ሉቻኖ ቫሳሎ (አምበል) ፲. ኢታሎ ቫሳሎ ፲፩. ጌታቸው ወልዴ ሲሆኑ ተጠባባቂዎች ደግሞ ጌታቸው መኩሪያ፣ እስማኤል ጊሪሌ፣ ብርሃኔ አስፋው፣ ኃይሌ ተስፋ ጋብር፣ ነፀረ ወልደሥላሴ ነበሩ። አሰልጣኞች ይድነቃቸው ተሰማ፣ ፀሐየ ባሕረና አዳሙ ዓለሙ፣ ወጌሻው ጥላሁን እሸቴ ነበሩ፡፡