ወደ ሮማውያን ፪
ወደ ሮማውያን በአዲስ ኪዳን የመጀመሪያው መልዕክት ሲሆን ቅዱስ ጳውሎስ በቆሮንጦስ እያለ በ፶፮ - ፶፰ ዓ.ም. የጻፈው መልዕክት ነው ። ይህ ምዕራፍ ፪ ሲሆን በ፳፱ ንዑስ ክፍሎች ይከፈላል ።
ወደ ሮማውያን ፪ | |
---|---|
አጭር መግለጫ | |
ፀሐፊ | ጳውሎስ |
የመጽሐፍ ዐርስት | ወደ ሮማውያን |
የሚገኘው | በአዲስ ኪዳን ፮ኛው መጽሐፍ |
መደብ | የጳውሎስ መልዕክት |
ቅዱስ ጳውሎስ ለሮማውያን መልዕክቱን የጻፈበት ምክኒያት አይሁዳውያንና ሮማውያን በሰላም አንድላይ በሮም ለብዙ ዘመን ሲኖሩ ቆይተው ክርስትና በተመሠረተበት ወቅት ፣ አይሁዳውያን ክርስቶስ እኛን ነው የመረጠን ለመንግሥቱ እናንተን አይደለም... ሲሊ ሮማውያን ደግሞ እናንተ ሰቀላችሁት እንጂ ምን አረጋቹህለት... እየተባባሉ እርስበርሳቸው ጥል ስለፈጠሩ እነሱን ለማስታረቅ ጻፈው ።
ወደ ሮማውያን ምዕራፍ ፪
ቁጥር ፩ - ፲
ለማስተካከል1፤ስለዚህ፥አንተ፡የምትፈርድ፡ሰው፡ዅሉ፡ሆይ፥የምታመካኘው፡የለኽም፤በሌላው፡በምትፈርድበት፡ነገር፡ ራስኽን፡ትኰንናለኽና፤አንተው፡ፈራጁ፡እነዚያን፡ታደርጋለኽና። 2፤እንደዚህም፡በሚያደርጉት፡ላይ፡የእግዚአብሔር፡ፍርድ፡እውነተኛ፡እንደ፡ኾነ፡እናውቃለን። 3፤አንተም፡እንደዚህ፡በሚያደርጉ፡የምትፈርድ፡ያንም፡የምታደርግ፡ሰው፡ሆይ፥አንተ፡ከእግዚአብሔር፡ፍርድ፡ የምታመልጥ፡ይመስልኻልን፧ 4፤ወይስ፡የእግዚአብሔር፡ቸርነት፡ወደ፡ንስሓ፡እንዲመራኽ፡ሳታውቅ፡የቸርነቱንና፡የመቻሉን፡የትዕግሥቱንም፡ ባለጠግነት፡ትንቃለኽን፧ 5፤ነገር፡ግን፥እንደ፡ጥንካሬኽና፡ንስሓ፡እንደማይገ፟ባ፟፡ልብኽ፡የእግዚአብሔር፡ቅን፡ፍርድ፡በሚገለጥበት፡በቍጣ፡ቀን፡ቍጣን፡በራስኽ፡ላይ፡ታከማቻለኽ። 6፤ርሱ፡ለያንዳንዱ፡እንደ፡ሥራው፡ያስረክበዋል፤ 7፤በበጎ፡ሥራ፡በመጽናት፡ምስጋናንና፡ክብርን፡የማይጠፋንም፡ሕይወት፡ለሚፈልጉ፡የዘለዓለምን፡ሕይወት፡ ይሰጣቸዋል፤ 8፤ለዐመፃ፡በሚታዘዙ፡እንጂ፡ለእውነት፡በማይታዘዙትና፡በዐድመኛዎች፡ላይ፡ግን፡ቍጣና፡መቅሠፍት፡ ይኾንባቸዋል። 9፤ክፉውን፡በሚያደርግ፡ሰው፡ነፍስ፡ዅሉ፡መከራና፡ጭንቀት፡ይኾንበታል፥አስቀድሞ፡በአይሁዳዊ፡ደግሞም፡ በግሪክ፡ሰው፤ 10፤ነገር፡ግን፥በጎ፡ሥራ፡ለሚያደርጉ፡ዅሉ፡ምስጋናና፡ክብር፡ሰላምም፡ይኾንላቸዋል፥አስቀድሞ፡ ለአይሁዳዊ፡ደግሞም፡ለግሪክ፡ሰው።
ቁጥር ፲፩ - ፳
ለማስተካከል11፤እግዚአብሔር፡ለሰው፡ፊት፡አያዳላምና። 12፤ያለሕግ፡ኀጢአት፡ያደረጉ፡ዅሉ፡ያለሕግ፡ደግሞ፡ይጠፋሉና፤ሕግም፡ሳላቸው፡ኀጢአት፡ያደረጉ፡ዅሉ፡ በሕግ፡ይፈረድባቸዋል፤ 13፤በእግዚአብሔር፡ፊት፡ሕግን፡የሚያደርጉት፡ይጸድቃሉ፡እንጂ፡ሕግን፡የሚሰሙ፡ጻድቃን፡አይደሉምና። 14፤ሕግ፡የሌላቸው፡አሕዛብ፡ከባሕርያቸው፡የሕግን፡ትእዛዝ፡ሲያደርጉ፥እነዚያ፡ሕግ፡ባይኖራቸው፡እንኳ፡ ለራሳቸው፡ሕግ፡ናቸውና፤ 15፤እነርሱም፡ኅሊናቸው፡ሲመሰክርላቸው፥ዐሳባቸውም፡ርስ፡በርሳቸው፡ሲካሰስ፡ወይም፡ሲያመካኝ፡በልባቸው፡ የተጻፈውን፡የሕግ፡ሥራ፡ያሳያሉ። 16፤ይህም፡እግዚአብሔር፡በኢየሱስ፡ክርስቶስ፡እኔ፡በወንጌል፡እንዳስተማርኹ፡በሰው፡ዘንድ፡የተሰወረውን፡ በሚፈርድበት፡ቀን፡ይኾናል። 17፤አንተ፡ግን፡አይሁዳዊ፡ብትባል፡በሕግም፡ብትደገፍ፡በእግዚአብሔርም፡ብትመካ፥ 18፤ፈቃዱንም፡ብታውቅ፡ከሕግም፡ተምረኽ፡የሚሻለውን፡ፈትነኽ፡ብትወድ፤ 19-20፤በሕግም፡የዕውቀትና፡የእውነት፡መልክ፡ስለ፡አለኽ፥የዕውሮች፡መሪ፥በጨለማም፡ላሉ፡ ብርሃን፥የሰነፎችም፡አስተማሪ፥የሕፃናትም፡መምህር፡እንደ፡ኾንኽ፡በራስኽ፡ብትታመን፤
ቁጥር ፳፩ - ፳፱
ለማስተካከል21፤እንግዲህ፡አንተ፡ሌላውን፡የምታስተምር፡ራስኽን፡አታስተምርምን፧አትስረቅ፡ብለኽ፡የምትሰብክ፡ ትሰርቃለኽን፧ 22፤አታመንዝር፡የምትል፡ታመነዝራለኽን፧ጣዖትን፡የምትጸየፍ፡ቤተ፡መቅደስን፡ትዘርፋለኽን፧ 23፤በሕግ፡የምትመካ፡ሕግን፡በመተላለፍ፡እግዚአብሔርን፡ታሳፍራለኽን፧ 24፤በእናንተ፡ሰበብ፡የእግዚአብሔር፡ስም፡በአሕዛብ፡መካከል፡ይሰደባልና፥ተብሎ፡እንደ፡ተጻፈ። 25፤ሕግን፡ብታደርግ፡መገረዝስ፡ይጠቅማል፤ሕግን፡ተላላፊ፡ብትኾን፡ግን፡መገረዝኽ፡አለ፡መገረዝ፡ ኾኗል። 26፤እንግዲህ፡ያልተገረዘ፡ሰው፡የሕግን፡ሥርዐት፡ቢጠብቅ፡አለመገረዙ፡እንደ፡መገረዝ፡ኾኖ፡ አይቈጠርለትምን፧ 27፤ከፍጥረቱም፡ያልተገረዘ፡ሕግን፡የሚፈጽም፡ሰው፡የሕግ፡መጽሐፍና፡መገረዝ፡ሳለኽ፡ሕግን፡ በምትተላለፈው፡ባንተ፡ይፈርድብኻል። 28፤በግልጥ፡አይሁዳዊ፡የኾነ፡አይሁዳዊ፡አይደለምና፥በግልጥ፡በሥጋ፡የሚደረግ፡መገረዝም፡መገረዝ፡ አይደለምና፤ 29፤ዳሩ፡ግን፡በስውር፡አይሁዳዊ፡የኾነ፡አይሁዳዊ፡ነው፥መገረዝም፡በመንፈስ፡የሚደረግ፡የልብ፡መገረዝ፡ ነው፡እንጂ፡በመጽሐፍ፡አይደለም፤የርሱ፡ምስጋና፡ከእግዚአብሔር፡ነው፡እንጂ፡ከሰው፡አይደለም።