ወርቅነህ እሸቴ
ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ የኢትዮጵያ ምርጥ ልጅ ነበሩ።
አዛዥ ወርቅነህ / ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ የመቅደላ ጦርነት ጊዜ በእንግሊዝ የጦር መኮንን በሕጻንነታቸው ወደ ሕንድ አገር ተወስደው እዚያው ያደጉ፤ የኖሩ እና በቀዶ ጥገና ሙያ የተሠማሩ ሰው ሲሆኑ አሳዳጊ አባቶቻቸው በሰጧቸው ስሞች ቻርልስ (በወሰዳቸው መኮንን ስም)፤ ማርቲን (ባሳዳጊያቸው ሐኪም ስም) (Charles Martin) ይባሉ ነበር። አዛዥ ወርቅነህ በሎንዶን የኢትዮጵያ ዋና መላክተኛነቱን ሥልጣን ሲሾሙ የሹመት ማስረጃቸውን መጀመሪያ ለንጉሥ ጆርጅ አምስተኛ ሐምሌ ፲፰ ቀን ፲፱፻፳፯ ዓ/ም፤ በኋላ ደግሞ ለንጉሥ ኤድዋርድ ስምንተኛ ጥር ፳፯ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ/ም አቅርበዋል። በዚህ ዕለት የኢትዮጵያን ግዛት ከግንቦት ፩ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ/ም ጀምሮ የምወክለው እኔ ነኝ ያለችው የኢጣሊያ መላክተኛም የሹመት ማስረጃውን አብሮ አቅርቧል። በሎንዶን ፲፯ ‘ፕሪንስስ ጌት’ (17 Princes Gate) የሚገኘውን የኢትዮጵያ መላከተኞች መኖሪያ እና መሥሪያ ቤትን በአገራቸው ስም የገዙትም ዋና መላክተኛ አዛዥ ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ናቸው።