ወልቃይት

ትግራይ ውስጥ የሚገኝ የትግራይ መሬት

ወልቃይት ጠገዴ ማነው? “የወልቃይት ባህልና የማንነት ጥያቄ” የሚለው ፅሁፋ በገጽ 4, 2ኛው አንቀጽ ላይ “ስለዚህ የትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር ወልቃይትን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያለውን ታሪክ በዜሮ ብናባዛው፤ የህዝበ-ውሳኔው ውጤት ከትግራይ ጋር መኖር የሚሹ ወልቃይቴዎች በሰፊ ልዩነት ሊያቸንፉ መቻላቸውን ያበስር ነበር” ይላል። ነገር ግን ይህ የአቶ ሃይሉ የሺወንድም ምኞትና ድምዳሜ ወይም ህወሃታዊ ተልዕኮ ከታሪክና ከተጨባጩ የወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብ አቋምና ምርጫ ፍጹም እንደሚቃረንና እንደሚጋጭ በሁለት ቀደምት የህወሃት አባላት የቀረቡ ምስክርነቶች አጥጋቢ መልስ ስለሚሰጡ እነርሱን እንመልከት። ኢትዮጵያውያን እንደ ዛሬው ህወሃት በለጠፈብን የብሔር ታርጋ ምክንያት የጎሪጥ መተያየት ሳንጀምርና ሃገራችን ጎጥ ጎጥ ከመሽተቷ 37 ዓመታት በፊት በትግራይ ነጻ አውጭ ቡድን በኩል ለወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብ የቀረበው “ወልቃይት ጠገዴ ማነው?” ጥያቄ በወቅቱ የነበሩት ኩሩና በማንነታቸው ላይ ፍጹም ብዥታ ያልነበራቸው ወገኖቻችን የህወሃት ወኪል ለነበረውና ጥያቄውን ይዞ ለመጣው ለአቶ መኮንን ዘለለው በማያዳግም ሁኔታ መልሰውለት እንደነበር ታሪክ ህያው ምስክር ነው። በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ የህወሃት ነባር አባልና የፋይናንስ ኋላፊ የነበሩት አቶ ገብረመድህን አርአያ በዲሴምበር 22, 2015 ኢትዮ- ሚዲያና ጎልጉል ድረ-ገፅ ላይ “በወልቃይት ጠገዴ፤ ጠለምት በአማራው ላይ ህወሃት የፈጸመው የዘር ማጽዳት ወንጀል” በሚል ባወጡት ጥልቅ ሰነድ በገጽ 2 ላይ፤ “በሪጅን 1 የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የነበረው፣ በአባቱ ወልቃይት ፀገዴ፣ በእናቱ ሽሬ የሆነው መኮንን ዘለለው፣ የተወጠነውን ትልእኮ ይዞ ወልቃይት ፀገዴ ፀለምት እየተዘዋወረ ህዝቡን በመሰብሰብ ይህ መሬት የትግራይ መሬት ስለሆነ እናንተ ከእንግዲህ ወዲህ የሰሜን ጎንደር ዜጎች አይደላችሁም፣ የትግራይ መሬት ስለሆነ እንኖራለን ካላችሁ ትግሬዎች መሆናችሁን አምናችሁ ተቀበሉ፤ የትግራይ ዜጎች አይደለንም፣ ሰሜን በጌምድር የትግራይ አይደለም ካላችሁ ደግሞ የድርጅቱን የህወሓትን ውሳኔ ተጠባባቁ፤ የምታምኑበትን አሁን ተናገሩ በማለት ሲያስጠነቅቅ፣ ከህዝቡ በኩል ያገኘው መልስ ግን አንድ ነበር። የቀረበውን ሃሳብ ከህፃን እስከ አዋቂ፣ የወልቃይት ፀገዴና የፀለምት ህዝብ፣ እኛ የሰሜን በጌምድር (ጎንደር) አማሮች እንጂ ትግሬዎች አይደለንም፣ የታሪካችን ስር መሰረቱ የበጌምድር አማሮች ነን። ይህ ቆመህ የምትናገርበት መሬት ሰሜን በጌምድር ይባላል። ከጥንቱ ታሪካችን 3 ብትነሳም ይህ መሬት ታሪካዊ ነው። ያለፉት የኢትዮጵያ ነገሥታት ከጥንት ጀምሮ እስከ አሁኗ ሰአት በመንግሥት እውቅና ያገኘ የጎንደር፣«”የበጌምድር” ጠቅላይ ግዛት እየተባለ የሚጠራ ነው። ዋና ከተማችን ደግሞ ጎንደር ነው። የእናንተም ትግራይ ጠቅላይ ግዛት ይባላል፣ ዋና ከተማው ደግሞ መቀሌ ነው። ስለዚህ ኣናንተ የተሓህት ታግዮች ጉዳዩን ብታሱብበት ጥሩ ነው። ወደ እርስ በርስ ግጭ ያመራል።በተጨማሪም ታሪካዊ የወሰን ክልል አለን፣ እሱም ተከዜ ወንዝ ነው። የትግራይና በጌምድር የድንበር ክልሉ ተከዜ ወንዝ ነው። ከጥንት ጀምሮ የሁለቱ ኢትዮጵያውያን የድንበር ወሰን መሆኑን ልናረጋግጥ እንፈልጋለን በማለት በአንድነት ድምፅ ህዝቡ ራሱ አረጋገጠ።” በማለት ገልፀውታል። ይልቁንም በአቶ መኮንን ዘለለው በኩል ለቀረበላቸው የማንነት ጥያቄ “የበጌምድር አማሮች ነን” የሚለውን የማያወላዳ ምላሽ የሰጡ የማህበረሰቡ ታላላቅና የተከበሩ መሪዎች በአቶ ስዩም መስፍንና በአቶ ግደይ ዘራፅዮን መሪነት ታፍነው ወደ ትግራይ መወሰዳቸውንና በሳሞራ የኑስ ትእዛዝ እንደተረሸኑ እራሳቸው አቶ መኮንን ዘለለው ለኢሳት ቴሌቭዥን በሰጡት ቃለ-መጠይቅ ላይ በዝርዝር አጋልጠዋል። በዚህ “ወልቃይት ጠገዴ ማነው?” በሚለው የህወሃት ያልተቋረጠ ጥያቄ ዙሪያና ህዝባችን በሚሰጣቸው አንድ፤ ግልፅና ቀጥተኛ መልስ ምክንያት ወገናችን የጅምላ ግርፋቶች፤ መፈናቀሎች፤ እስራቶች፤ ግድያዎች፣ ስደቶች፣ ቅስም ሰባሪና፣ ፀያፍ በደሎች ተፈፅመውበታል። ታዲያ ይህ ሁሉ ሰቆቃ አሁንም ሳያባራ የትግራዩ ነጻ አውጭ ቡድን እነሆ ዛሬም እንደገና በእነ አቶ ሃይሉ የሺወንድም በኩል “ወልቃይት ጠገዴ ማነው?” ይለናል። አስቀድሞ በአቶ መኮንን ዘለለው በኩል ቀርቦ ህዝባችንን ለእልቂት የዳረገው ህወሃታዊ ጥያቄ ዳግም ለወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብ መጠየቅ ማለት አንድም ወገኖቻችን በማንነታቸው ጸንተው በመቆማቸው ምክንያት የከፈሉትን መስዋእትነት እንደ “ውሻ ደም” በመቁጠር ለመሳለቅ ወይም በህዝባችን ላይ ለተደገሰው ቀጣይ ህወሃታዊ ፍጅት ሰበብ ለማዛጋጀትና የጥፋት መንገድ ለመጥረግ የታለመ ይመስላል። የህወሃት ሆድ-አደሮች ምን እያሉን ነው? ወልቃይት ጠገዴ ማነው? ለሚለው የህወሃት መላዘን ወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብ ምላሹ ከላይ በአይን እማኞችና በህያው ምስክሮች እንደተረጋገጠ አይተናል። ታዲያ ለምን የዛሬዎቹ ተላላኪዎች “ስለዚህ የትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር ወልቃይትን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያለውን ታሪክ በዜሮ ብናባዛው፤ የህዝበ-ውሳኔው ውጤት ከትግራይ ጋር መኖር የሚሹ ወልቃይቴዎች በሰፊ ልዩነት ሊያቸንፉ መቻላቸውን ያበስር ነበር” እያሉ ሌላውን ህዝብ ለማደናገር ይሞክራሉ? ለምንስ በወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብ በደል ላይ ይዘባበታሉ? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። ከዚህ የሆድ አደሮች ዘመቻ የምንረዳው ነገር ቢኖር ተላላኪዎቹ ቀደም ሲል በተደጋጋሚ እንገልጸው እንደነበረው ሁሉ ከህወሃት የተሰጣቸውን “የወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብን በማዳከምና በመከፋፈል ትግሪያዊነትን አሜን ብሎ እንዲቀበል” የማስቻል ተልእኮ ለማሳካት በሚል በመላው ኢትዮጵያ በተለይም እንደ ጋምቤላ ባሉ አካባቢዎች በሚደረጉ የመሬት ዘረፋዎችና ቅርምቶች (ወልቃይት ጠገዴ ለትግራውያን ብቻ ነው) ቢንበሻበሹም ውጤቱ ግን “ጉም መዝገን” ሆኖባቸዋል። ይልቁንም በሃገር ውስጥ የሚገኘው የወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብ ከምንግዜውም በላይ ተደራጅቶና ከመላው የአማራ ህዝብ ጋር አንድ ሆኖ ማንነቱ ለማስከበር ቆርጦና አምርሮ ሲነሳ ከህወሃት ይልቅ የተጨነቁት በወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብ ስም ድርጎ ሲቀበሉ የከረሙት ናቸው። ከህወሃት በኩል ልምጭ የተቆረጠበት የሚመስለው ሆድ-አደሩ ቡድን መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ያንገሸገሸውንና ህወሃትን እስከ አንገቱ ያነቀውን፤ ይልቁንም በህወሃት/ኢህአዴግ መንደር እውቅና አግኝቶ ከጠ/ሚ እስከ ተራ ካድሬ እየተቀባበለ የሚዘምርለትን “የመልካም አስተዳደር እጦት” በምትባል “የጦስ ዶሮ” በመታከክ የወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብ ያነሳውን ዘርንና ትውልድን ከጥፋት የመታደግና የአማራ ማንነቱን በትግሪያዊነት ከመተካት የማዳን ፈርጀ ብዙ ጥያቄ “የትግራይ ክልል ባለስልጣናት የአስተዳደር በደል ስለፈጸሙበት” ነው እያሉ ማፌዝ በወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብ ቁስል በእሳት የጋለ ብረት እንደመስደድ ይቆጠራል።ያስተዛዝባልም። ይልቅስ አቶ ሃይሉና የጥቅም ተጋሪዎቻቸው በወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብ ላይ የደረሰው በደል የዘር ማፅዳትና በትግሪያዊነት የመተካት ዓለም-አቀፍ ወንጀል መሆኑን የምትስቱት አይመስለንም። ይህን በማንነታችን ላይ የተፈጸመና በዓለም-አቀፍ የፍርድ አደባባይ የሚያስጠይቅን ወንጀል በማኮሰስና “የትግራይ ክልል ባለስልጣናት የአስተዳደር በደል” አድርጎ በማቅረብ ከህወሃት ጋር የገጠማችሁን ኪሳራ ማወራረድ ወይም የሚቆረጥላችሁን ድርጎ ማሳደግ አትችሉም። ኪሳራችሁን ማወራረድም ሆነ ሌላም ማድረግ የምትችሉት ለጌቶቻችሁ እውነቱን በመናገር ብቻ ነው። ምክንያቱም የወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብ ጎንደሬ-አማራ መሆኑን በአንድ ድምጽ ያረጋገጠውና በማንነቱም ምክንያት ለሚመጣ ማንኛውም ነገር ዋጋ ለመክፈል ዝግጁነቱንና ቁርጠኝነቱን በተግባር ያሳየው ገና “የትግራይ” የሚባሉ ገዥዎችና አስተዳደራቸው ከመፈጠሩ እጅግ አስቀድሞ እንደነበር ከወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብ ባልተናነሰ እነ ስብሃት ነጋ ጠንቅቀው ያውቃሉና እራሳችሁን አታታልሉ። ትዝብት ላይም አትውደቁ። በሌላ በኩል ምንም እንኳ ዛሬ ህወሃት እስከ አፍንጫው ቢታጠቅና የሃገሪቱን መንግስታዊ ስልጣንና ሃብት እንዳሻው ቢያዝና ቢናዘዝበትም የወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብ ዛሬም በማንነቱ ላይ ያለውን የቀደመ ጽኑ እምነትና የትውልዱን ምስክርነት ማስለወጥ አልተቻለውም። እንግዲህ ለህወሃትና ለእነ አቶ ሃይሉ የሺወንድም እውነታው እንደ እሬት መራራ ቢሆንባቸውም ታሪክ በደማቁ የመዘገበውና በእያንዳንዱ የወልቃይት ጠገዴ ተወላጅ ህሊና ተጽፎ የሚገኘውና ለትውልድ የምናስተላልፈው እውነታ ግን የወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብ ህወሃት ዕርስታችንን ከመርገጡ በፊትም ሆነ በወረራ በተቆጣጠረ ጊዜ በጎንደሬ-አማራነቱ ጸንቶ በመቆም መራር መስዋእትነት እንደከፈለ ሁሉ ወደፊትም በማንኛውም የከፋ ፈተና ውስጥ ቢያልፍም ከጎንደሬ-አማራነቱ ሊያናውጸው የሚችል ምንም አይነት ምድራዊ ሃይል ያለመኖሩን ነው። ምክንያቱም ወልቃይት ጠገዴ አይደለም ለማንነቱና ለዕርስቱ፤ አምነው ለተጠጉትም አንገት እንደማያስደፋ ትግራውያን ያውቃሉ! ታዲያ ወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብ ማነው? “በአፍ የመጣን በአፍ፣ በመጣፍ የመጣን በመጣፍ” መመለስ የቀደሙ አባቶቻችን ስርዓትና ብሂል በመሆኑና ታሪካዊ ጠላቶቻችንም እንደ አመጣጣቸው መመለስ ተገቢ በመሆኑ ህወሃት በተላላኪዎቹ በኩል በወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብ መካከል ሊዘራ የሞከረውን እንክርዳድና በኢትዮጵያ ህዝብና በታሪካችን ላይ ሊፈጠር የታሰብውን ብዥታ ለማጥራት ሲባልና ለታሪክም ምስክር ይሆን ዘንድ “የወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብ ማነው?” የሚለውን ጥያቄ በአጭሩ እንደሚከተለው ስንመልስ ጥልቁንና ተነግሮ የማይጠገበውን የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ታሪክ ለታሪክ ፀሃፊዎችና ለባለሙያዎች በመተው ነው። 1. የወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብ እንደ ማንኛውም የሰሜኑ ኢትዮጵያ ማህበረሰብ ሁሉ የአካባቢውን ስያሜ በመውሰድ የእራሱ መጠሪያ አድርጎ ኖሯል። ለምሳሌ የጎንደሬ ዘሩ ምንድነው? የሚኖርበት አካባቢ ስያሜ ማን ይባላል? የጎጃሜውስ? የወሎዬው? የጋይንቴው? የምንጃሬው? የስሜንኛው? … ወዘተ ለመሆኑ እነዚህ ወገኖቻችን እራሳቸውን ሲጥሩ “እኛ ማነን” ይላሉ? እኛስ እነርሱን እነማን ናቸው እንላለን? ጎንደሬውን – ጎንደሬ ፤ ጎጃሜውን – ጎጃሜ ፤ ወሎዬውን – ወሎዬ፣ ደብረታቦሬውን – ደብረታቦሬ፤ ጋይንቴውን – ጋይንቴ፤ ስሜንኛውን – ስሜንኛ፤ በለሴውን – በለሴ፣ ወግሬውን – ወገሬ፣ ቋረኛውን – ቋሬ …. ወዘተ እያልን ወልቃይቴውን – ወልቃይቴ፣ ጠገድቼውን – ጠገድቼ፣ ጠለምቴውን – ጠለምቴ አላልንምን? እንላለን እንጂ! 2. ታዲያ የወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብ አባቱ ማነው? የዘር ሐረጉስ ከየት ይመዘዛል ቢሉ? ወልቃይት የሚለው ስም ከስር መሰረቱ የአማራ መስራች አባት የሚባለው የተጠቀሰበት አገር ነው። አማራው ከወልቃይት ወደ ጠለምት ከዚያም ወደ ላኮ መልዛ (የዛሬው ወሎ) እያለ ሌላውን አካባቢ እያስፋፋ እስከ ሞቃዲሾ ተጉዞ ሃገር ያቀና ታላቅ ነገድ ያረፈበት መሆኑ ታሪክ ሁሌም ይመሰክራል። ወልቃይት ጠገዴ አማራ የሆነው ዛሬ ትግሬ ሊያደርጉት እንደሚታትሩት በተዘዋዋሪ ሳይሆን የአማራ አባትና ግንድ በመሆን ነው። ለዚህ ፅሁፍ በሚስማማ መልኩ ታሪካዊ ማስረጃዎችን እንመልከት። አለቃ ታዬ ወልደማርያም የተባሉ ሊቅና የተመሰከረላቸው ታሪክ ፀሃፊ “የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ” በተባለው ዝነኛ መፅሃፋቸው በገፅ 16 ላይ እንዲህ ፅፈዋል። “ከለው ከሳባ ወደ ምዕራብ ወደ ደቡብ ያለ ያማራ የወልቃይት የጠገዴ አባት ነው። ከእነዚህም የኢትዮጵስ ልጆች የወንድማማቾቹ ነገድ ህዝብ ሁሉ በመልካቸውና በቁርበታቸው ይመሳሰላሉ። እኒህም ህዝብ የያዙት አገር በጥቅሉ ባባታቸው ስም ኢትዮጵያ ተብሎ ይጠራል።” በመቀጠልም የአማራው አባት አስገዴ ግንዱ ከወልቃይት ጠገዴ አርማጭሆ ከዚያም እያደገና እየሰፋ አማራ ሳይንት ድረስ የደረስ መሆኑን ገልጸው ጽፈዋል። አቶ አማረ አፈለ “ደም አይፍሰስ በቃ የህወሃት ማኒፌስቶ ያብቃ!” በሚለው መፅሐፋቸው በገጽ 27 ታሪካዊ ምስክርነታቸውን እንደሚከተለው አስፍረዋል። “ከተከዜ ጀምሮ ወደ ደቡብ እስከ ሸላሎ በተዘረጋው ምድር ላይ ያሉት ወረዳዎች ሕዝቡ አፍ መፍቻ ቋንቋው አማርኛ ነው። ከትግራይ ጋር በተከዜ ወንዝ ድልድይነት ጎረቤት ስለሆነ ወዲያና ወዲህ ማዶ ያለው የዐማራና የትግራይ ቋንቋ ቃላት ቢያንስ 80 በመቶ ተመሳሳይ በመሆናቸው መናገሩ አዳጋች አይሆንባቸውም። ይልቁንም የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት መዘጋዎች ጥጥ ስለሚያመርት ብዙ የትግራይ ተወላጆች በጥጥ ለቀማ ወቅት በየዓመቱ ወደነዚህ መዘጋዎች ይመጣሉ። ዐማሮች ከእነርሱ ጋር ለመግባባት ሲሉ ትግርኛውን ይጠቀሙበታል። ከእንግዶች መካከል ሀገሬውን አግብተው የሚቀሩም አይጠፉም። ለዚህም ወደ ኋላ መለስ ብለን ታሪክ ስንመረምር ወልቃይት ጠገዴና ጠለምት በአክሱም፤ በላስታው በሽዋ ሆነ በጎንደር ዘመነ መንግሥት አንድም ግዜ የትግራይ ግዛት አካል ወይም ገባር የሆነበት የታሪክ ወቅት የለም። ይህን እውነት ለመረዳት ከጎንደር ዘመነ መንግሥት በፊት ጀምሮ 20ኛ ምዕተ ዓመት ሁለተኛ አጋማሽ ድረስ የታወቁ የውጭ ሀገር ጉብኝዎችና ታሪክ ፀሐፊዎች በተለያዩ ክፍለ ዘመናት ኢትዮጵያን እየተዘዋወሩ ካዩ በኋላ ስለ ብሔረስቦችና ስለ አስተዳደር ክፍሎች የተውልን ጹሑፎችና ካርታዎች ህያው የታሪክ ማስረጃዎች ናቸው።” “ለአብነት ያህል ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ፤ ጅምስ ብሩስ፤ ዶክተር ሚካኤል ረሥል፤ ማንስፊልድ ፓርኪንስ፤ ስቨንረንሰን ወዘተ…….የተባሉ ታዋቂ ተመራማሪዎች ለትውልድ ያበረከቷቸውን መጻሕፍት መመልከት ይቻላል። ይልቁስ የኢጣሊያን መንግሥት ኢትዮጵያን በ1928 ዓ/ም ከመውረሩ በፊት በጐንደር ከተማና በሌሎች ከተሞች በከፈታቸው የቆንስል ቢሮዎች አማካይነት ባካሄደው ሰፊ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ጥናት ባወጣው አስተዳደር መዋቅር ትግራይ ከኤርትራ ጋር ሲደርብ ጠገዴንና ጠለምትን የአማራ ክልል በማድረግ ትግሬ አለመሆናቸውን አረጋግጧል።”