ክላውድ ሻነን
ክላውድ ሻነን (1908-1993 ዓ.ም.) አሜሪካዊ ሓሳቢ፣ ኤሌክትሮኒክ ኢንጂኔር፣ እና ሥነ ምስጢረኛ (ክሪፕቶግራፈር) የነበር ሲሆን በቅጽል ስሙ የመረጃ ኅልዮት አባት ተብሎ ይታወቃል፡፡ ሻነን በ1940ዓ.ም. በደረሰው አንድ ጽሑፍ የሥነ መረጃ ኅልዮትን እንደመሰረተ ይጠቀሳል፣ ይሄውም በአሁኑ ዘመን ለሚገኘው የኮምፒውተርና ከኮምፒውተር ጋር የተነካኩ ማናቸውም ቴክኖሎጂዎች መነሻ ነው፡፡ በሌላ ጎን ክላውድ ሻነን የዲጂታል ኮምፒውተርና የዲጂታል ዑደት ቅየሳ ኅልዮትን መስራች እንደሆነ ስምምነት አለ። ይሄንንም የፈጸመው በ1929 ዓ.ም. ለድህረ ምረቃው (ማስተርስ) በጻፈው ጽሑፍ ሲሆን በጊዜው ሻነን የ21 ዓመት ወጣት ነበር። በዚህ ጽሑፉ የቡላዊ አልጀብራና የኤሌክትሪክ ዑደት አንድ ላይ ተዳምረው ማናቸውንም የቁጥርና የአምክንዮ ተዛምዶዎች መፍታት እንዲችሉ በማሳየቱ ነበር። በተረፈ፣ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት የሥነ ምስጢር ትንተና በማካሄድ እና የጠላትን ኮድ በመበተን ስሙ ይነሳል።