ኩሩካን ፉጋ የማሊ መንግሥት ሕገ መንግሥት1227 ዓ.ም. እስከ 1637 ዓ.ም. ነበረ። በማንሳ (ንጉሥ) ሱንጃታ ኬይታ ቃል ታዋጀ።

በተለይ ለአፍሪካዊ ግዛት መንግሥት በቀድሞ የታወቀውና በአፍ ቃል የሚወርድና የሚወረስ ሕገ መንግሥት ሆኖ እንደ ኢትዮጵያ ፍትሐ ነገሥት ሳይሆን ከሌላ አኅጉር ልማድ አልተወሰደም።

የማሊ ኅብረተሠብ በዚሁ ሕገ መንግሥት በወገኖች ተከፋፈለ። ከነዚህ 16ቱ 'የፍላጻ ማሕደር ተሸካሚዎች' ተብለው የመከላከል ሀላፊነት ነበራቸው። የ5 ወገኖች ሀላፊነት የሃይማኖት ጠባቂዎች (እስልምና) ነበረ። 4 ወገኖች በየሥራው ላይ (የብረታብረት፣ የእንጨት፤ የቆዳ ሥራ ወዘተ) ተሾሙ። በመጨረሻ 4 ወገኖች የቃል ሊቃውንት ተባሉ፤ የመንግሥት ታሪክ በግጥም ዘገቡ።

በማሊ ንጉሥ ሱንዲያታ የተዋጀው ሕገ መንግሥት

ለማስተካከል
  • አንቀጽ 1፦ ታላቁ ማንዴ ኅብረተሠብ በ16 የፍላጻ ማሕደር ተሸካሚ ወገኖች፣ 5 ሃይማኖት ጠባቂ ወገኖች፣ 4 ሠራተኛ ወገኖች፣ እና 1 ባርያ ወገን ይለያያል። እያንዳንዱ ልዩ ተግባርና ሚና አለው።
  • አንቀጽ 2፦ ሠራተኛ ወገኖች ለአለቆችና ለአማካሪዎቻቸው ዕውነቱን ለመናገርና በሙሉው ግዛት የተመሠረቱትን ገዢዎችና ሥርዓት በቃሉ ለመከላከል አለባቸው።
  • አንቀጽ 3፦ 5ቱ የሃይማኖት ጠባቂ ወገኖች በእስልምና አስተማሪዎቻችን ናቸው። ሰው ሁሉ በማስተንግዶ ሊያክብራቸው ይገባዋል።
  • አንቀጥ 4፦ ሕብረተሠቡ በእድሜ ይከፋፈላል። በ3 አመታት ቅድም ተከተል ጊዜ ውስጥ የተወለዱት ግለሰቦች አንድ ክፍል ናቸው። በልጆችና በሽማግሌዎች መካከል ያለው ክፍል አባላት ስለ ኅብረተሠቡ ጉዳዮች ውሳኔ በመቋረጥ ተከፋፋዮች እንዲሆኑ ሊጠየቁ ይገባል።
  • አንቀጽ 5፦ ሰው ሁሉ የሕይወትና ደህንነቱን የመጠብቅ መብት አለው። ስለዚህ ሰው የባልንጀራውን ሕይወት ለማጥፋት ቢሞክር ኖሮ፣ በሞት ይቀጣል።
  • አንቀጽ 6፦ የምጣኔ ሀብቱን ትግል ለማሸነፍ፣ ስንፍናን ቦዞኔንም ለመዋጋት፣ አጠቃላይ የመቆጣጠር ሥርዓት ተመሠርቷል።
  • አንቀጽ 7፦ በማንዲንካ ሕዝብ መካከል «ሳናንኩያ» (የመቃለድ ጸባይ ወይም ዝምድና) እና የደም ውል ተመሠርቷል። ስለዚህ በነዚህ ወገኖች መካከል የሚነሣው ጠብ ሁሉ የእርስ ብርስ መከባበርን ደንብ ሊያዋርድ አይገባም። በወንድማማችና በእህትማማች መካከል፣ በአያቶችና በልጅ ልጆች መካከል፣ መታገሥና መቃለድ መርኁ እንዲሆን ይገባል።
  • አንቀጽ 8፦ የከይታ ቤተሠብ በመንግሥቱ ላይ ገዢው ቤተሠብ ሆኖ ይሰየማል።
  • አንቀጽ 9፦ የልጆች ትምህርት ኅብረተሠቡን በሙሉ ይጠቅማል። የወላጅነት ሥልጣን እንግዲህ ለሰው ሁሉ የሚወድቅ ነው።
  • አንቀጽ 10፦ እርስ በርስ የጋራ ስሜት (በደስታ ወይም በሀዘን) ሊኖረን ይገባናል።
  • አንቀጽ 11፦ ሚስትህ ወይም ልጅህ ከቤት የሮጠች እንደ ሆነ እስከ ጎረቤት ድረስ አትከተላት።
  • አንቀጽ 12፦ ወራሽነት በአባት በኩል ሆኖ፣ አባቱ እየኖረ ሥልጣን ለልጁ ከቶ አይሰጠም። ዕቃ ቢኖረውም ስልጣን ለልጅ ከቶ አይሰጠም።
  • አንቀጽ 13፦ ባላሙያውን ከቶ አታስቀይሙት።
  • አንቀጽ 14፦ ሴቶችን፣ እናታችንን ከቶ አታስቀይሟቸው።
  • አንቀጽ 15፦ ባልዋ በጉዳዩ ሳይገባ፣ ባለትዳርን ሴት መቸም አትመቱአት።
  • አንቀጽ 16፦ ከሁልቀን ተግባራቸው በቀር፣ ሴቶች በጉዳዮቻችን ሁሉ ውስጥ ሊገቡ ተገቢ ነው።
  • አንቀጽ 17፦ አንድ ውሸት ከ40 አመት በላይ የቆየ እንደ ሆነ፣ እንደ ዕውነቱ ይቆጠር።
  • አንቀጽ 18፦ የበኩሩን መብት ደንብ መጠብቅ ይገባናል።
  • አንቀጽ 19፦ ሰው ሁለት ዓማቶች አሉት። ያጣናት ሴት ወላጆችና ያለ ገደብ የምናቀርብ ንግግር። በመተሳሰብ ልናከብራቸው አለብን።
  • አንቀጽ 20፦ ባርያውን አታጎሳቆለው። ከሳምንቱ የአንድ ቀን ዕረፍት ስጠው፤ ስራውንም በመጠነ ሰዓት ይተወው። የባርያው እንጂ የሚሸክመው አኮፋዳ ባላቤት አይደለንም
  • አንቀጽ 21፦ የአለቃ፣ የጎረቤት፣ የአስተማሪ፣ የቄስ፣ የባልንጀራ ሚስት እንዳታሽኮርመም።
  • አንቀጽ 22፦ ከንቱነት የድካምነቱ ምልክት፣ ትሕትናም የትልቅነቱ ምልክት ነው።
  • አንቀጽ 23፦ እርስ በርስ ከቶ አትከዱ። የክብር ቃላችሁን ጠብቁ።
  • አንቀጽ 24፦ በማንደን (የማሊ መንግሥት)፣ የውጭ አገር ሰውን አትበድል።
  • አንቀጽ 25፦ በማንደን፣ ተልእኮው ምንም አደጋ የለውም።
  • አንቀጽ 26፦ ለአንተ ጥብቅና በአደራ የተሰጠው ወይፈን የበረቱ መሪ ሊሆን አይገባውም።
  • አንቀጽ 27፦ ሴት ልጅ አካለ መጠን በደረሰች ጊዜ፣ ልክ ዕድሜዋ ሳይወሰን በጋብቻ ልትሰጥ ትችላለች። ከእጩዎቹ ቁጥር መካከል የወላጆችዋ ምርጫ ይጸናል።
  • አንቀጽ 28፦ ወንድ ልጅ ዕድሜው 20 አመት በደረሰ ጊዜ ሊያገባ ይችላል።
  • አንቀጽ 29፦ የሚሰጠው ጥሎሽ 3 ላም ይሆናል። ከነዚህም 1ዱ ለሴቲቱ፣ 2ቱ ለአባትዮዋና እናትዮዋ ይሆናሉ።
  • አንቀጽ 30፦ በማንዴ፣ መፈታታት በሚከተሉት ምክንያቶች ብቻ ይታገሣል። የባሉ አለመቻል፣ የአንዱ ባለቤት ዕብድነት፣ ወይም ባሉ የትዳሩን ሀብት አለመቻሉ። ፍቺውም ከመንደሩ ውጭ ይካሔድ።
  • አንቀጽ 31፦ በችግር ላይ የሆኑትን መርዳት ይገባናል።
  • አንቀጽ 32፦ ንብረት በ5 ዘዴዎች በሕጋዊነት ሊገኝ ይቻላል። በመግዛቱ፣ በስጦታው፣ በልውውጡ፣ በሥራውና በመውረሱ ናቸው። ማንኛውም ሌላ ዘዴ፣ የምስክርነት ማስረጃ ካልኖረ በቀር፣ አጠያያቂ ነው።
  • አንቀጽ 33፦ ማናቸውም የተገኘው ዕቃ ቢኖር ባለቤቱም ካልታወቀ፣ አራት አመት ብቻ ከመቆየት በኋላ የጋራ ንብረት ይሆናል።
  • አንቀጽ 34፦ አንዲት ላም በአደራ ለሰው ጥብቅና ስትሰጥ፣ አራተኛው ጥጃ ለሚጠብቀው ሰው ንብረት ይጨመራል። አንዲት ዶሮ በአደራ ጥብቅና ብትሰጥ፣ አራተኛውም ዕንቁላል ለጠባቂዋ ይሂድ።
  • አንቀጽ 35፦ የአንድ ከብት መመምንዘሪያ ዋጋ አራት በግ ወይም አራት ፍየል ይሆናል።
  • አንቀጽ 36፦ ሰው በአኮፋዳው ወይም በኪሱ ምንም ካልወስደ፣ ለማጥገብ ልቅም ማድረጉ ስርቆት አይደለም።
  • አንቀጽ 37፦ ፋኮምቤ የአዳኞች አለቃ ይሰየማል።
  • አንቀጽ 38፦ ቊጥቋጦውን ሳታቃጠል ወደ መሬቱ አትይ፤ ነገር ግን ራስህን ወደ ዛፎች ጫፍ አንሥተህ ፍራፍሬ ወይም አበባ እንደማይኖራቸው ተመልከት።
  • አንቀጽ 39፦ ልማዳ እንስሶች በማረሻ ሰዓት ተስረው ከመከሩ በኋላ ሊፈቱ ይገባል። ይህ ድንጋጌ ግን ለውሻው፣ ለድመቱ፣ ለይብራው ወይም ለዶሮው አያጠቅልልም።
  • አንቀጽ 40፦ ዝምድናን፣ ትዳርንና ጎረቤቱንም አክበራቸው።
  • አንቀጽ 41፦ ጠላቱን መግደል ቢፈቀድም እርሱን ማዋረድ ግን አይፈቀደም።
  • አንቀጽ 42፦ በታላቁ ማህበር፣ በሕጋዊ አመካሪዎቻችሁ ደስ ይበላችሁ።
  • አንቀጽ 43፦ ባላ ፋሴኬ ኩያቴ የሥነ ስርዓት ዋና አለቃና በማንደን ዋና አማላጅ ሆኖ ይሰየማል። እርሱ ከወገኖቹ ሁሉ በተለይም ከንጉሱ ቤተሠብ ጋራ መቃለድ ይችላል።
  • አንቀጽ 44፦ እነዚህን ደንቦች የሚጥስ ሁሉ ይቀጣል። ሰው ሁሉ ተግባራዊ ሆነው እንዲጸኑ ይታዘዛል።