አያሌው መስፍን
አያሌው መስፍን ታዋቂ ኢትዮጵያዊ ዘፋኝ ነው።
የሕይወት ታሪክ
ለማስተካከልአያሌው መስፍን በ፲፱፻፵፪ ዓ.ም. በወሎ ክፍለ ሀገር በየጁ አውራጃ ተወለደ። አያሌው ገና በልጅነቱ የሙዚቃ /የዘፋኝነት/ ሙያ ፍቅር ስለነበረበት ወላጆቹ ወደ ትምህርት ቤት ሲልኩት እሱ ግን የሚውለው አዝማሪዎች በማሲንቆ በሚጫወቱበት ሥፍራ ነበር። ይህንንም በውስጥ የሚነደውን የሙዚቃ ፍቅር ለማርካት ከወሎ ጠፍቶ በ፲፱፻፶፮ ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ መጣ። አዲስ አበባ እንደመጣም ብሔራዊ ቲያትር ድምፃውያንን ለመቅጠር ማስታወቂያ አውጥቶ በነበረበት ጊዜ የተሰጠውን የመግቢያ ፈተና መቶ ከሚሆኑ ተወዳዳሪዎች በአንደኛነት ቢያልፍም ወላጆቹ በተለይም አባቱ የአያሌውን ዘፋኝ መሆን በሬዲዮ ከሰማ አዝማሪ ሆነ ብሎ ይጠላኛል በማለት ፈርቶ ሳይቀጠር ቀረ። ከእዚያም አባቱ እንዳይቀየሙት በማለት ሙያውን ትቶ በቀድሞው የክብር ዘበኛ ሠራዊት ውስጥ በወጣት ሻምበልነት ተቀጥሮ እስከ ፲፱፻፶፱ ዓ.ም. ድረስ ቆየ። ሆኖም አያሌው ዓላማና ፍላጎቱ በሙዚቃ ሙያ ውስጥ ገብቶ ስሜቱን ማርካት በመሆኑ ወደ ሙዚቃው ዓለም የሚገባበትን መንገድ ቀይሶ በጊዜው በነበረው አንድ ባንድ ውስጥ ተቀጥሮ በ፲፱፻፶፱ ዓ.ም. ወደ ጅማ ሄደ።
አያሌው ከጅማ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ ፈጣን ኦርኬስትራ በመባል በሚታወቀው በወ/ሮ አሰገደች አላምረው ቤት (ፓትሪስ ሉሙምባ የሚባል የማታ ክበብ ውስጥ) በሳምንት አምስት ብር እየተከፈለው ተቀጥሮ ይሰራ ነበር። ሆኖም ግን በዚያን ጊዜ ማለት በነሐሴ ወር ፲፱፻፶፱ ዓ.ም. ፲፮ የሚሆኑ ዘፈኖቹን አዘጋጅቶ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሬዲዮ አቀረበ። ከዚያ በኋላ ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ፍቅርና አድናቆትን አትርፎ ክፍያው በቀን ወደ አሥራ አምስት ብር ከፍ አለ።
ከዚያም በ፲፱፻፷፪ ዓ.ም. አያሌው የፈጣን ኦርኬስትራን ትቶ ብሔራዊ ቲያትር ገባ። ብሔራዊ ቲያትርም ለ፫ ወራት ያህል ብቻ ከሰራ በኋላ ክፍሉን ለቆ በፖሊስ ሠራዊት የሙዚቃ ክፍል ተቀጥሮ እስከ ፲፱፻፷፮ ዓ.ም. የዘመን መለወጫ በዓል ድረስ ሲያገለግል ቆይቶ ከ፲፱፻፷፮ ዓ.ም. በኋላ ጥቁር አንበሳ የተባለ የግሉ የሙዚቃ ጓድ አቋቁሞ በ፲፬ቱም ክፍላተ ሀገራት ተዘዋውሮ የሙያ ግዳጁን ተወጥቷል።
የሥራዎች ዝርዝር
ለማስተካከልአያሌው ከ፫፻ የሚበልጡ ዘፈኖችን የተጫወተ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ «ቻለው ሆዴ»፣ «ማሩኝ ዘመዶቼ»፣ «ማን ልበል ወዳጄ»፣ «በምላስ በስሎ»፣ «አላጎበድድም»፣ «ቀኔን እገፋለሁ»፣ «ወልደሽ ያሳደግሽኝ እናቴ ናፈቅሽኝ»፣ የተሰኙት በሕዝብ ዘንድ በጣም ተወዳጅ ናቸው።
ማጣቀሻ
ለማስተካከል- ናሽናል ቢብሊዮግራፊ ቡድን፣ የአንጋፋ አርቲስቶች መዝገበ የሕይወት ታሪክ፣ መጋቢት ፳፻፣ ገጽ 11-12 Archived ሴፕቴምበር 29, 2011 at the Wayback Machine