አባ አፍፄ
አባ አፍፄ
ጻድቁ የተወለዱት እስያ ውስጥ በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሆን ወላጆቻቸው አቡሊዲስና አቅሌስያ ይባላሉ። ገና በሕፃንነታቸው ብሉይ ከሐዲስ ጠንቅቀው ወደ ግብጽ ወርደዋል። በዚያም በአባ መቃርስ እጅ መንኩሰዋል። አባ አፍፄ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በአልዐሜዳ ዘመን ከስምንቱ ባልንጀሮቻቸው ጋር ነው።
ጻድቁ ጠበል እያፈለቁ ብዙ ድውያንን ፈውሰዋል። ትግራይ ውስጥ የሐ የተባለው ቦታም ማረፊያቸው ነበር።
ስለ ጻድቁ በጥቂቱ እነዚህን እንጠቅሳለን።
፩.ከመቶ ዓመት በላይ አበ ምኔት ሆነው በኖሩበት ገዳማቸው በፍጹም ትጋት በጾምና በጸሎት አገልግለዋል።
፪.በመጀመሪያ ያስከተሏቸውን ሦስት መቶ ስልሳ ስድስት ደቀ መዛሙርት ጨምሮ ብዙ መናንያንን አፍርተው በሃገራችን ገዳማዊ ሕይወትን አስፋፍተዋል።
፫.ቅዱሳት መጻሕፍትን ከሱርስትና ከጽርዕ ቋንቋ ወደ ግዕዝ ተርጉመዋል።
፬.በስብከተ ወንጌል ለሃገራችን ብርሃንን አብርተዋል። ሕዝቡ በጣዕመ ስብከታቸው ይገረም ስለ ነበር "አፍፄ (አፈ-ዐፄ)" ብሏቸዋል። "የዐፄ (የንጉሥ) አንደበት ያለው" ወይም "ንግግር አዋቂ" (Speaker) ማለት ነው።
ጻድቁ ከሁለት መቶ ዓመታት በላይ ቤተ ክርስቲያንን አገልግለው በዚህች ቀን በ፮፻፹፬ ዓ.ም ተሠውረዋል። እግዚአብሔርም በስማቸው ለተማጸነ ገዳማቸውን ለተሳለመ የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል።