ስለ ዓለማየሁ ገ/ሕይወት
                                                    

ዓለማየሁ ገ/ሕይወት ጎንደር ከተማ ነው የተወለደው። የቄሱንም፣ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም በተወለደባት ጎንደር ተከታትሏል። የመጀመርያ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትያትር ጥበባት አገኘ። ከአብዛኞቹ ሲወዳደር እውቀት የጠማው፣ ታታሪና ጎበዝ ተማሪ እንደነበረ አስታውሳለሁ። በተለይ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ላይ የጥናት ወረቀት እንዲያቀርብ ተመድቦ የሠራው ሥራና አቀራረቡ እስካሁን ያስደንቀኛል። እንደተመረቀ ባህል ሚኒስቴር ነበር የተመደበው ፤- በሥነጽሑፍና ተውኔት ገምጋሚነት። ከሱ በፊት የተመረቁና ባህል ሚኒስቴር የተመደቡ ሁሉ በቢሮ ጥበት ምክንያት በአንድ ትንሽ አዳራሽ ውስጥ የተኮለኮሉ ስለነበረ፣ ደግሞም ብዙ ሥራም ስላልነበረ ጫወታውና ክርክሩ የጊዜ ማሳለፊያ ነበር። ዓለማየሁ ግን ሥራ በሌለበት ሰአት ወደ ዩኒቨርሲቲ ቤተመጻሕፍት ነበር የሚሮጠው። ጊዜውን በንባብ ነበር የሚያሳልፈው። ከዚያም ውጭ የትም ሲሄድ መጽሐፍና መጽሔት ከእጁ የሚለይ አልነበረም። የንባብ ሱስ ነበረበት። የዘወትር አንባቢ ነው ዓለማየሁ።

ከዚያም ጋር በተያያዘ የመድረክ፣ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ተውኔት የመጻፍ ጥረቱ ገና በወጣትነቱ ነው የተጀመረው። እየበሰለ ሄዶም "መንታ መንገድ" የትርጉም ስራው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴያትር ከአንድ ዓመት በላይ ታይቶለታል። ቀደም ብሎ የተረጎመው የኦስካር ዋይልድ ተውኔት "ስጦታ" በሚል ርዕስ በሃገር ፍቅር ቴያትር ለመድረክ በቅቶለታል። ፈላስፋዋ፣ የገንፎ ተራራ፣ ብረትና ሙግት፣ ወቴዎቹ፣ አምሳያ ልጅ፣ ውርክብ፣ ቃለ መጠይቅና ሌሎች ሥራዎቹም በመድረክ፣ በራዲዮና በቴሌቪዥን ቀርበውለታል። በቅርቡም የታዋቂውን አሜሪካዊ ደራሲ የአርተር ሚለርን ተውኔት “የአሻሻጩ ሞት” ብሎ ወደአማርኛ መልሶታል። ዓለማሁ፣ በሁለገብ ጠቢብነቱ አባተ መኩሪያ ባዘጋጃቸው “ያላቻ ጋብቻ” እና “ኢዲፐስ ንጉሥ” እንዲሁም በፍሥሀ በላይ “አልቃሽና ዘፋኝ”፣ በሌሎችም እንደ “የቁም እንቅልፍ”፣ “ምርመራው”፣ “ጋብቻው” ባሉ ትያትሮች ተውኗል። ዓለማየሁ የተዋናይን ዲሲፕሊን የሚያከብር በመሆኑ ለደራኪዎች ምቹ ነበር። “ፍቅር መጨረሻ” በተሰኘው የተስፋዬ ማሞ ፊልም በተዋናይነትም ተሳትፏል።

ዓለማየሁ በማህበራዊ ግንኙነትና አስተዋጽኦ የታደለ ነው። ለሰው ፍቅር፣ ወዳጅነትና መግባባት ልዩ ተሰጥኦ አለው። ገና ከዩኒቨርሲቲ እንደተመረቀ፣ እኛ እጃቸውን ለመጨበጥ ከምንፈራቸው የአገራችን ኮከቦች ከሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን፣ ከሎሬት አፈወርቅ ተክሌ፣ከደራሲ አሰፋ ገብረማርያም ጋር የጠበቀ ወዳጅነትን መስርቶ ነበር። የደራስያን ማህበር ሊቀመንበር የነበረው ጋሼ ደበበ ሰይፉ ወዳጅ ከመሆን አልፎ የቅርብ የስራ አጋሩም ነበር። ዓለማየሁ ከባህል ሚኒስቴር በሁዋላ በአማራ ክልል የባህል፣ ቱሪዝምና ማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊ ሆኖም ለበርካታ ዓመታት አገልግሏል። የሥነጥበብ እንቅስቃሴን በማስፋቱ ረገድ ከእሱ ጋር ሊወዳደር የሚችል የባህል ቢሮ ኃላፊ እስካሁን አልታየም። ሙሉዓለም የባህል ማዕከልን ለመመስረት ግንባር ቀደሙ ዓለማየሁ ነው። ከማንኛውም ክልል በተሻለ የትያትርና ሙዚቃ አቅርቦት ለህብረተሰብ እንዲቀርብ አስችሎ ነበር። አዲስ አበባ የታዩ ተውኔቶች በማእከሉ እንዲታዩም አድርጓል። ታላቅ አበርክቶው ግን እሱ በኃላፊት እስከነበረበት ጊዜ ድረስ ለዓመታት ሳይቁዋረጥ ቀበሌዎች፣ ወረዳዎችና ዞኖች በትያትር፣ በሙዚቃ፣ በሥነጽሑፍና በሥዕል እየተወዳደሩ በማጠቃለያው ይካሄድ የነበረው የክልል ሥነጥበብ ፌስቲቫል ነበር። በዚህ ሂደት ውስጥ ያለፉ ወጣቶች ታዋቂ ደራሲዎችና ተዋናይ ለመሆን በቅተዋል።

ዓለማየሁ ለሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቁዋንቁዋና ሥነጽሑፍ ትምህርት ክፍል ገብቶ ሁሉንም ኮርሶች ካጠናቀቀ፣ የመመረቂያ ጽሑፉን በኢትዮጵያ ዲያስፖራ ሥነጽሑፍ ላይ ለመስራት ወደ አሜሪካ ያቀና ሲሆን እዚያው ለመቆየት ወሰነ። በአሜሪካ ቆይታው በአንድ ዓለማቀፍ የልማት ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ ከአሥራ ሦስት ዓመት በላይ ሠርቷል። ከመደበኛ ሥራው ጎን ለጎንም በጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከል ንቁ ተሳታፊና የቦርድ አባል ሆኖም እየሠራ ነው። እዚያም ሆኖ "እታለም" የተሰኘ የግጥም መድበል በ1999 ዓ.ም. ያሳተመ ሲሆን በተስፋዬ ለማ የተዘጋጀው "የኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ" መጽሐፍ አርታኢም ነው። የተወሰኑ የእንግሊዝኛ ግጥሞቹም “Songs We Learn from Trees” በተሰኘና በ Carcanet Press አማካይነት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2020 እንግሊዝ አገር በታተመ መጽሐፍ ውስጥ ተካተዋል። አሁን ደግሞ “በፍቅር መንገድ” የተሰኘ ልብወለድ ሥራውን ለኅትመት አብቅቷል። በትያትርና ሥነጽሑፍ ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶችን በግልና በጋራ አዘጋጅቷል። ከመስከረም 2010 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በ"ታዛ" የባህልና የሥነጥበብ መጽሔት ላይ በርካታ መጣጥፎችን አቅርቧል። ከመጽሔቱ መስራቾችና ባለቤቶችም አንዱ ነው። በቅርቡም፣ አሜሪካ ያሉ አርቲስቶችን በማስተባበር 100ኛውን የኢትዮጵያ ትያትር ኢዩቤልዩ በድምቀት እንዲከበር ካደረጉት ባለሙያዎች አንዱ ነው።

                                         አቦነህ አሻግሬ 
                                (በአ.አ. ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር)
                                        የካቲት 30/2014



የድርሰት ሥራዎች

1.  ቃለ መጠይቅ

2.  ውርክብ

3.  ውለታ ያሠረው

4.  ብረትና ሙግት

5.  ወቴዎቹ

6.  አባ ኮስትር

7.  የአይን ማረፊያ

8.  ፈላስፋዋ

9.  የገንፎ ተራራ

10. ባለኮፍያው

11. ስጦታ

12. መንታ መንገድ

13. እታለም (የግጥም መድበል)

14. በፍቅር መንገድ (ረጅም ልብወለድ)