'ትንቢት ትንቢት ምንድን ነው? ትንቢት ወደ ፊት ስለሚመጣው ጊዜ ስለሚኾነው ኹኔታ እና ስለሚደረገው ነገር ማወቅ ማሳወቅ ማናገር መናገር መጻፍ ማጻፍ ነው፡፡ ወደፊት ስለሚመጣው ጊዜ ስለሚኾነው ኹኔታ እና ስለሚደረገው ነገር በምን መልኩ ሊያዉቁ ይችላሉ? ቢሉ ስለብዙ ነገር ያውቃሉ! 1. በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት መንፈስ ቅዱስ ወደፊት የሚደረገውን ነገር አቅርቦ እና አጉልቶ የሚያሳያቸው የተመረጡ የተቀደሱ አባቶቻችን አሉ እነዚህም ነቢያት ናቸው፡፡ ትንቢት ከመንፈስ ቅዱስ የሚሰጥ ሀብት ነውና እንደ ነቢዩ ኢሳይያስ እንደ ነቢዩ ኤርምያስ እንደነ ዳንኤል እንደነ ዮናስ እንደነ ሕዝቅኤል እንደነ ዳዊት ወዘተ ያሉት ሀብተ ትንቢት የተሰጣቸው ቅዱሳን ናቸው፡፡ ትንቢታቸውም ማስፈራሪያና ተስፋ ማስቆረጫ አይደለም! ለምሳሌ ኢሳይያስ -- ናሁ ድንግል ትጸንስ ወትወልድ ወልደ ብሎ ጽንሰተ ወልደተ እግዚእን ይናገራል፡፡  በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንመ ተሸከመ ብሎ መከራ መስቀሉን ያስታውሰናል፡፡ ዳዊት ደግሞ-- ልደቱን - (ቦታ) ናሁ ስማዕናሁ በኤፍራታ ወረከብናሁ ውስተ ዖመ ገዳም፡፡

                     (ማናት) እምነ ጽዮን ይብል ሰብእ፡፡ ወብእሲ ተወልደ በውስቴታ፡፡
   ጥምቀት - (የት)- ባሕርኒ ርእየት ወጎየት ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኅሬኁ፡፡
   ሆሳዕና - እም አፈ ደቂቅ ወሕጻናት አስተዳሎከ ስብሐተ፡፡
  ስቅለት - (መከራ) - ቀነውኒ እደውየ ወእገርየ ወኆለቁ ኩሎ አእጽምትየ፡፡ እሙንቱሰ ጠይቆሙ   ወተዐወሩኒ ወተካፈሉ አልባስየ ለርእሶሙ፡፡
     (የት) - እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ ወገብረ መድኃኒተ በማዕከለ ምድር (ቀራንዮ)

ትንሣኤ- ወተንሥአ እግዚአብሔር ከመ ዘንቃሕ እምንዋም፡፡ ዕርገት- ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ፡፡ ወእግዚእነ በቃለ ቀርን፡፡ 2. በመረጃ ትንተና መረጃዎችን በመሰበሰብና እነዚያን መረጃዎች በመተንተን ወደፊት ስለሚሆነው ነገር መተንበይ ይቻላል፡፡ ይህ ትንቢት ከመንፈስ ቅዱስ የሚሰጥ ሳይኾን መረጃን የመተንተን ችሎታን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ለምሳሌ ደመና በሰማይ ከታየ ከባድ ዝናብ ይጥላል ብሎ መናገር ማለት ነው፡፡ የተካረረ ፖለቲካ ካለ የእርስ በርስ ፍቅር ከጠፋ “ጦርነት ይሆናል” ብሎ መተንበይ ቀላል ነው፡፡ ጦርነት መኖሩን ከተናገሩ ከዚያ ጋር ተያይዞ “ሰው ያልቃል” “ወጣቱ ይገደላል” “ረሐብ ይሆናል” ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ትንቢት የመፈጸም አቅሙ ከፍተኛ ነው፡፡ እነዚህ ነቢያትም የመረጃ ነቢያት ይባላሉ፡፡ ሌላው ከዚሁ ጋር ተያይዞ ትንቢት መናገር በሚፈልፉበት ዙሪያ መረጃ ሰብሳቢዎችን አሰማርተው ግለሰቦች ብቻ የሚያውቋቸውን ምስጢሮች ሳይቀር ይሰበስባሉ፡፡ እነዚህ ከእኛ ውጭ ሌላ ሰው አያውቃቸውም ያልናቸውን ምሥጢሮች ሲነግሩን እውነተኞች እንደሆኑ እናምናለን፡፡ 3. መጻሕፍት ላይ ከተጻፉ ትንቢቶች በመቆራረጥ ማቅረብ እነዚህ የዘመናችን ነቢያት መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተጻፈው ትንቢት ውጭ ሊናገሩ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ትንቢቱ ተነግሯልና፡፡ እነዚህ ሰዎች እየቆራረጡ የሚጠቀሙት ማቴ 24 ላይ ያለውን ጌታ ለሐዋርያት የነገናቸውን ትንቢት ነው፡፡ ወንጌል ላይ ጌታ ለሐዋርያት ምን አላቸው? ማቴዎስ 24ን እናንብብ!