ቴዎፍሎስ
በእትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጥቅምት 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ✞✞✞ +"23ተኛ ሊቀ ዻዻሳት ቅዱስ ቴዎፍሎስ ሊቅ "+
✞✞✞ በምድረ ግብጽ ከተነሱና ለቤተ ክርስቲያን አብዝተው ከደከሙ አባቶች አንዱ አባ ቴዎፍሎስ ነው:: የተወለደው በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ሲሆን ቴዎፍሎስ (ታኦፊላ) በመባል ይታወቃል:: ገና ልጅ እያለ ቴዎዶስዮስ ከሚባል ባልንጀራው ጋ በተመሳሳይ ሌሊት ተመሳሳይ ሕልምን ያያሉ::
+2ቱ ሕጻናት ያዩት እንጨት ሲለቅሙ ነበር:: ሕልምን የሚተረጉመው ሰውም ቴዎዶስዮስን "ትነግሣለህ" ሲለው ቴዎፍሎስን "ፓትርያርክ ትሆናለህ" አለው:: ለጊዜው አልመሰላቸውም::
+ከዚያም ወደ ት/ቤት ገብተው: መጻሕፍትን ተምረው ቴዎዶስዮስ ወደ ንጉሡ ከተማ ቁስጥንጥንያ ሲሕድ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ግን የታላቁ ሊቅ አባ አትናቴዎስ ደቀ መዝሙር ሆነ:: በዚያም ከቅዱሱ እየተማረ: እያገለገለ ዘመናት አለፉ::
+ቅዱስ አትናቴዎስ ካረፈ በኋላም ለ2 ፓትርያርኮች ረዳት ሆኖ ተመርጧል:: በመጨረሻ ግን ሕልም ተርጉዋሚው ያለው አልቀረምና ቴዎዶስዮስ 'ታላቁ' ተብሎ በቁስጥንጥንያ ላይ ሲነገሥ ቅዱስ ቴዎፍሎስም ፓትርያርክ (ሊቀ ዻዻሳት) ተብሎ በመንበረ ማርቆስ ላይ ተቀመጠ::
+በ384 ዓ/ም የእስክንድርያ 23ኛው ሊቀ ዻዻሳት ከሆነ በኋላ የመጀመሪያ ሥራው በዘመኑ ገነው የነበሩ መናፍቃንን መዋጋት ነበር:: ለዚህም ይረዳው ዘንድ የእህቱ ልጅ የሆነውን ቅዱስ ቄርሎስን ወስዶ አስተማረው:: 2ቱ አባቶች እየተጋገዙም ቤተ ክርስቲያንን ከአራዊት (መናፍቃን) ጠበቁ:: ዛሬ በሃይማኖተ አበው የምናውቀውን ጨምሮ ቅዱሱ በርካታ ድርሰቶችንም ደረሰ::
+ቅዱስ ቴዎፍሎስን ለየት ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል ጥቂቶቹን እንመልከት:-
1.ቅዱሱ በዘመኑ ከመንበረ ዽዽስናው በር ቁጭ ብሎ ይተክዝ ነበርና አንዲት ባለ ጸጋ ሴት መጥታ "አባቴ! ምን ያስተክዝሃል?" ስትል ጠየቀችው::
+ሊቁም "ልጄ! እዚህ የቆምንበት ቦታ ውስጥ ወርቅ ተቀብሮ ሳለ ነዳያን ጦማቸውን ያድራሉ:: አባቴ አትናቴዎስ እንዳዘነ አለፈ:: እኔም ያው ማለፌ ነው" አላት:: ባዕለ ጸጋዋም "አባ አንተ ጸሎት: እኔ ጉልበትና ሃብት ሁነን እናውጣው" አለችው::
+"እሺ" ብሏት ሱባኤ ገባና ከመሬት በታች 3 ጋን ሙሉ ወርቅ ተገኝቶ ደስ አላቸው:: ግን በላያቸው ላይ ተመሣሣይ "ቴዳ: ቴዳ: ቴዳ" የሚል ጽሑፍ ነበረውና ማን ይፍታው:: በዚህ ጊዜ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ወደ እመቤታችን አመልክቶ ምሥጢር ተገለጠለትና ሲተረጉመው ማሕተሞቹ ተፈቱ::
+ሲተረጐምም ቴዳ 1 "ክርስቶስ" ማለት ሆነ:: ይሔም ለነዳያን ተበተነ:: ቴዳ 2 "ቴዎፍሎስ" ማለት ሆነ:: አብያተ ክርስቲያናት ታነጹበት:: ቴዳ 3 ደግሞ "ቴዎዶስዮስ" ሆነ:: 'የቄሣርን ለቄሣር' እንዲል 3ኛው ጋን የአቡነ ኪሮስ ወንድምና የገብረ ክርስቶስ መርዓዊ አባት ለሆነው ለደጉ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ተላከለት::
+ንጉሡ ግን ከወርቁ ጥቂት ለበረከት ወስዶ ለአባ ቴዎፍሎስ መለሰለት:: አብያተ ጣዖቶችን እያፈረሰ አብያተ ክርስቲያናትን እንዲያንጽም ስልጣን ሰጠው:: ቅዱስ ቴዎፍሎስም በዚህ ገንዘብ በመቶ የሚቆጠሩ አብያተ ክርስቲያናትን እንዳነጸበት ይነገራል::
+በተለይ ደግሞ የቅዱስ ሩፋኤልን ቤት በአሣ አንበሪ ጀርባ ላይ ያነጸው እርሱ ነው:: (ድርሳነ ሩፋኤል) የድንግል ማርያምን ሲያንጽም እመቤታችን ተገልጣለታለች::
+የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቁን አጽም አፍልሦ ከነቢዩ ኤልሳዕ ጋር ቤቱን ሲቀድስለትም ተአምራት ተደርገዋል:: የሠለስቱ ደቂቅን ቤተ ክርስቲያን አንጾ የቀደሰ ጊዜ ደግሞ ቅዱሳኑ ከሰማይ ወርደውለታል::
2.ቅዱስ ቴዎፍሎስ እመቤታችንን ይወዳት ነበርና ለ8 ጊዜ ያህል ተገልጣ አነጋግራዋለች:: "ደፋሩ አርበኛ" ስትል ጠርታ: ሙሉ ዜና ስደቷንና ሕይወቷን አጽፋዋለች:: (ተአምረ ማርይም) 3.ሕጻናትን ሲያጠምቅም ከብቃት የተነሳ የብርሃን መስቀል ይወርድለት ነበር:: ቅዱስ ቴዎፍሎስ በሊቀ ዽዽስና በቆየባቸው 28 ዓመታት እንዲህ ተመላልሶ በ412 ዓ/ም ዐርፎ ቅዱስ ቄርሎስ በመንበሩ