በጠማማ ጣሳ

(32)በአለቃ ተረብ በተደጋጋሚ ጥቃት ደርሶበት በቁጭት ላይ የነበረ ሰው እርሳቸውን የሚተርብበት ጥሩ አጋጣሚ በማግኘቱ እጅግ በጣም ደስ ይለዋል። ይሄውም አለቃ እሰው ቤት እንጀራ በምስር ወጥ ተጋብዘው እስኪጠግቡ ይበሉና በወጡ የተለቃለቀውን አፋቸውንም ሆነ ከንፈራቸውን ሳይታጠቡ ሰው ወደተሰበሰበበት አደባባይ ይመጣሉ። ሰውዬውም ያገኘውን አጋጣሚ በመጠቀም በሰው ፊት አዋርዷቸው ዝና ሊያገኝ በመጣደፍ፤ «አለቃ! በዛሬው ገበያ የምስር ዋጋ ምን ያህል ነበር?» ይላቸዋል። አለቃም የሰውየውን ተረብ በቅጽበት ይረዱና ቀና ብለው ሰውየውን ሲያዩት ጉንጩ በጣም የከሳና የተጣመመ መምሰሉን ይረዳሉ። ታዲያ ለሰውየው የሚሰጡት መልስ ምን መሰላችሁ። «አይ ልጄ! ምስርማ ዛሬ ተወዶ በጠማማ ጣሳ በብር አንድ ሲሸጥ ውሏል።» በማለት የጉንጩን መጣመም ጠቆም አድርገው ቆሽጡን አሳረሩት ይባላል።