የልጅ እያሱ እናት ወ/ሮ ሸዋረጋ ምኒልክ ማን ናቸዉ?

.

--- ወይዘሮ ሸዋረጋ ምኒልክ በ 1859 ዓ.ም ከአባታቸዉ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ እና ከእናታቸዉ ወይዘሮ ደስታ ወለዱ።

--- ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከወሎ ህዝብ ጋር በደም ለመተሳሰር ልጃቸዉን ወይዘሮ ሸዋረጋ ምኒልክ በሀያ አምስት አመቷ 1884 ዓ.ም ለወሎው ገዢ ራስ ሚካኤል አሊ ዳሩለት።

--- ወይዘሮ ሸዋረጋ ምኒልክ እና የራስ ሚካኤልን ትዳር ሁለት ልጆችን ያፈራ ሲሆን የመጀመሪያ ልጃቸዉን በጥር 25 ቀን 1888 ዓ.ም አቤቶ እያሱ ሚካኤልን እና የጎጃሙን ገዢ ንጉስ ተ/ሃይማኖት ተሰማን ልጅ በዛብህ ተ/ሃይማኖት ተሰማ የትዳር አጋር የሆኑት ወይዘሮ ዘነበወርቅ ሚካኤልን ወልደዋል።

--- ወይዘሮ ሸዋረጋ ምኒልክ ልጅ ኢያሱ በተወለዱ በሦስተኛ ወራቸው በወርሀ ሚያዚያ ሞቱ። ይህን ጊዜ ራስ ሚካኤል (በወቅቱ ራስ ነበሩ) ከዳግማዊ ምኒልክ ጋር ለመላቀስ ከደሴ ወደ ሸዋ መጥተው በእንጦጦ ቤተ መንግሥት ከአማቻቸው ጋር ኀዘን ተቀመጡ፡፡ በወቅቱ በልጅ እያሱ እና በተፈሪ መኮነን(አፄ ሀይለስላሴ) መካከል የነበረዉ ዉጥረት ይታወቅ ስለነበረ ከተፈሪ ወገን የነበረች አንዲት የሸዋ አልቃሽ......

“ምነው በቀረባት የወሎ ጋብቻ፣ የወሎ ግዛት፣

ግሸን ወድቃ ቀረች የሸዋ እመቤት”........ ብላ ቤተ መንግሥቱ ዉስጥ አንጎራጎረች፡፡

በዚህን ጊዜ ተሰማ ጎሹ የተባለው የወሎ አልቃሽ በሴትዮዋ እንጉርጉሮ የወሎን ሰው የከፋው መሆኑን ተረድቶ የሚቀጥለውን የለቅሶ ግጥም ገጠመ፡፡

“ምነው ወሎን ገዝታ ግሼን ብትቀበር፤

ግማደ መስቀሉ ካረፈበት አገር፡፡

ከሚካኤል ወዲያስ ምን ክብር ባል ነበር፡፡

አይስሟት ጌታየ የሴትን ወሬኛ፤

እንጦጦን አይፈራም የአምላክ መላክተኛ፡፡

አሁን ምን ያደርጋል የሴት ወዮ ባይ፡

ወሎ የመጣው ሞት ሸዋ የለም ወይ፡፡

ተይ አንቺ ሴትዮ ነገር አታጥብቂ፤

እኛ አልገደልናትም እግዜርን ጠይቂ፡፡........ ብሎ በአንጎራጎረ ጊዜ አፄ ምኒልክ «ተውት ይቅር ይኸ ሁሉ ነገር ምን ያስፈልጋል!» ብለው ለቅሶውን አስቆሙት፡፡

--- አጠር ስናደርገዉ......

ወ/ሮ ሸዋረጋ ምኒልክ

የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ልጅ ፣ የንጉሥ ሚካኤል ባለቤት ፣ የዓፄ ምኒልክ የልጅ ልጅ፣ የልጅ ኢያሱ እናት ነበሩ፡፡