ሰባአዊ መብቶች
አለም አቀፍ የሰብእዊ መብቶች ድንጋጌ መንደርደሪያ • የመላውን የሰው ዘር ተፈጥሮእዊ ክብር እንዲሁም የማይገሰሱ እና እኩል የሆኑ መብቶች ማክበርና እውቅና መስጠት ለዓላማችን ሰላም ፍትህና ነጻነት ዋና መሰረት በመሆኑ፤ • የሰብእዊ መብቶች ጥሰትና አለመከበር አሰቃቂ ለሆኑና ለህሊናም ዘግናኝ ለሆኑ ተግባራት መንሰኤ ሆኖአል። ይህንንም ተከትሎ ሁሉም የሰው ልጆች የንግግርና የዕምነት ነጻነቶችን በሚቀዳጁበት እንዲሁም ከፍርሃት ነጻ ሆነው የሚኖሩበት የአለም አኗኗር ስርእት አሙን መሆን የአያንዳንዱ ሰው ተቀዳሚ ምኞት በመሆኑ፤ • የሰው ልጅ አምባገነናዊነትንና ጭቆናን ለማስወገድ አመጽን እንደ እማራጭ እንዳይወስድ ሰብእዊ መብቶች በህግ የበላይነት መጠበቅ ስለሚገባቸው፤ 1. በሃገራትም መካከል መልካም ግንኙነቶችን ማዳበርና ማሳደግ አስፈላጊ በመሆኑ፤ • የተባበሩት መንግስታት አባል ሀገራት በመሰረታዊ ሰብእዊ መብቶች፤ በሰው ልጅ ክብርና ዋጋ፤ በወንዶችና በሴቶች የአኩልነት መብቶች እንዲሁም በማህበራዊ መሻሻልና የኑሮ ደረጃ አድገት ላይ ያላቸውን ጽኑ እምነት በጋራ መተዳደሪያ ሰነዳቸው ላይ በማረጋገጣቸው፤ • አባል ሃገራት በራሳቸውና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን ለሰብእዊ መብቶችና መሰረታዊ ነጻነቶች መከበርና መስፋፋት ዕውን መሆን ቃል ኪዳን በመግባታቸው፤ • በነዚህ መብቶችና ነጻነቶች ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ መፍጠሩ ለቃል ኪዳኑ ገሃዳዊ ተግበራዊነት ከፍተኛ ጠቀሜታ አና አስተዋጽኦ በመኖሩ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ይህንን እለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ እያንዳንዱ ግለሰብ እና የማህበረሰብ አካል እነዚህን መብቶችና ነጻነቶች ለማስከበር፤ በዕለት ተዕለት በማስታወስ በማስተማርና በማስገንዘብ እንዲሁም ሀገር አቀፍና አለም አቀፍ ሂደታዊ አርምጃዎችን በመውሰድ የስኬታማነት የጋራ መስፈርት ሆኖ የተቀመጠውን የሰብእዊ መብቶችና ነጻነቶች ውጤታማ አለም አቀፋዊ እውቅናና መከበር በአባል ሃገራት ህዝቦችና በመላው አስተዳደራዊ ግዛቶቻቸው ይሰፍን ዘንድ ይህንን አዋጅ አስተላልፏል/አጽድቋል። አንቀጽ 1 የሰው ልጅ በተፈጥሮው ነፃ ነው። በክብርና በመብትም አኩል ነው። የሚያስተውል ህሊናም በተፈጥሮ የተለገሰ በመሆኑ አንዱ ከሌላው ጋር በወንድማማችነት መንፈስ ሊኖር ይገባዋል :: አንቀጽ 2፤ ሁሉም ሰው በዚህ ድንጋጌ ውስጥ የሰፈሩትን ሁሉንም መብቶችና ነፃነቶች ያለምንም ዓይነት የዘር የቀለም የፆታ የቋንቋ የሃይማኖት የፖለቲካ ወይም ሌላ አይነት አስተሳሰብ የብሄራዊ ወይም ማህበራዊ ታሪክ የሃብት የትውልድ ወይም ሌላ አይነት ሁኔታዎች ልዩነት ሳይደረግበት የመጠቀም መብት አለው:: አንቀጽ 3፤ ሁሉም ሰው በነፃነትና በሰላም የመኖር መብት አለው:: አንቀጽ 4፤ ማንም ሰው በባርነትና በባርነት ቀንበር መያዝ የለበትም ባርነትና የባሪያ ንግድ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ ነው:: አንቀጽ 5 ማንም ሰው በስቃይ ወይም በጭካኔ እንዲሁም ኢሰብአዊና ክብረ ነክ ወይም አዋራጅ በሆነ አያያዝ መያዝ ወይም መቀጣት የለበትም :: አንቀጽ 6 ሁሉም ሰው በየትኛውም ቦታ በህግ ፊት እንደሰው የመታየት መብት አለው:: አንቀጽ 7 ሁሉም ሰዎች በህግ ፊት እኩል ናቸው ሁሉም ሰዎች ያለምንም ልዩነት እኩል የሆነ ህጋዊ ከለላ እና ጥበቃ የማግኘት መብት አለው::
አንቀጽ 8 እያንዳንዱ ሰው በህግ ወይም በህገ መንግስት የተሰጡት መሰረታዊ መብቶች ላይ ጥሰት በሚደርስበት ጊዜ ችሎታ ባላቸው ብሄራዊ የፍትህ ተቋማት ውጤታማ የሆነ ፍትህ የማግኘት መብቱ የተጠበቀ ነው :: አንቀጽ 9 ማንም ሰው ያለፍርድ በግዞት መያዝ ወይም መታሰር የለበትም :: አንቀጽ 10 እያንዳንዱ ሰው በመብቶቹ ና በግዴታዎቹ አፈፃፀም እንዲሁም በሚከሰስበት ማንኛውም አይነት የወንጀል ክስ ጉዳዩ ነፃ በሆነና በማያዳላ እንዲሁም ትክክለኛና ፍታዊ በሆነ የፍርድ ሸንጎ እንዲታይለት የማድረግ ሙሉ መብት አለው:: አንቀጽ 11 1. በወንጀል ክስ የተከሰሰ ማንኛውም ሰው ለመከላከያው አስፈላጊ የሆኑትን ሁሉ አቅርቦ በሚከራከርበት የይፋ የፍርድ ሸንጎ ወይም ችሎት ወንጀለኛ መሆኑ በህግ እስከሚረጋገጥበት ድረስ ከወንጀል ነፃ እንደሆነ የመቆጠር መብት አለው:: 2.ማንም ሰው በብሄራዊ ወይም አለምዓቀፍ ህግ መሰረት ወንጀል ሆኖ ያልተደነገገን ተግባር በመፈፀሙ በጊዜው ወንጀለኛ ተብሎ ሊከሰስ አይችልም እንዲሁም ወንጀሉ በተፈፅመበት ጊዜ ከተደነገገው ቅጣት ይበልጥ አይፈረድበትም:: አንቀጽ 12 ማንም ሰው በግል ኑሮው በቤተሰቡ በቤቱ ውስጥ ወይም በሚፃፃፈው ደብዳቤ ላይ ከፍርድ ውጭ ከሚደረግ ጣልቃገብነት ነፃ ነው:: እንዲሁም ክብርና ዝናን ከሚነኩት ማንኝቸውም አይነት ጥቃቶች የተጠበቀ ነው:: እያንዳንዱ ሰው እነዚህን ከመሰሉ ጣልቃ ገብነትና ጥቃቶች ህጋዊ ከለላ የማግኘት መብት አለው:: አንቀጽ 13 1 እያንዳንዱ ሰው በሃገሩውስጥ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስና የመኖር መብት አለው:: 2 እያንዳንዱ ሰው የራሱን ወይም የየትኛውንም አገር ለቆ የመሄድ እንዲሁም ወደራሱም አገር የመመለስ መብት አለው:: አንቀጽ 14 1 እያንዳንዱ ሰው ከጭቆና ሸሽቶ በሌሎች ዓገሮች ጥገኝነት የመጠየቅና በደህና የመኖር መብት አለው :: 2 ፖለቲካዊ ካልሆኑ ወንጀሎች ወይም የተባብሩት መንግስታት ድርጅትን ዋና ዓላማዎችን ከሚቃረኑ ስራዎች የተነሳ በሚደርሱ ክሶች ምክንያት ከሆነ ይህ መብት ሊያገለግል አይችልም:: አንቀጽ 15 1 ሁሉም ሰው የዜግነት መብት አለው :: 2 ማንም ሰው ያለፍርድ ዜግነቱ አይወሰድበትም ወይም ዜግነቱን የመለወጥ መብት አይነፍገውም:: አንቀጽ 16 1 ለአካለ መጠን የደረሱ ወንዶችና ሴቶች በዘር በብሄርና በሃይማኖት ልዩነት ሳይወሰኑ ጋብቻን የመፈፀምና ቤተሰብን የመመስረት መብት አላቸው።ጋብቻ በመፈጸም በት ጊዜና ጋብቻ በሚፈርስበትም ጊዜ እኩል መብት አላቸው :: 2 ጋብቻ የሚፈፀመው ሁለቱም ተጋቢዎች በሚያደርጉት ነፃና ሙሉ ስምምነት መሰረት ብቻ ነው:: 3 ቤተሰብ የማህበረሰብ ተፈጥሮአዊና መሰረታዊ ክፍል በመሆኑ በህብረተሰቡና በመንግስት ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል ::
አንቀጽ 17 1 ሁሉም ሰው በግል ወይም በጋራ ንብረት የማፍራትና የንብረት ባለቤት የመሆን መብት አለው :: 2 ማንም ሰው ያለፍርድ ንብረቱን ሊነጠቅ አይችልም :: አንቀጽ 18 ሁሉም ሰው የሃሳብ የህሊናና የሀይማኖት ነፃነት መብት አለው:: ይህም መብት ሀይማኖቱን ወይም እምነቱን የመለወጥ ነፃነትንና ብቻውን ወይም ከሌሎች ጋር ሆኖ በይፋ የማስተማር በተግባር የመግለፅ የማምለክና የማክበር ነፃነትን ይጨምራል:: አንቀጽ 19 ሁሉም ሰው የሀሳብና ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት አለው :: ይህ መብት ሀሳብንና መረጃን ያለምንም ገደብ የማግኘትን የመቀበልን የማካፈልንና ያለምንም ጣልቃ ገብነት በሀሳብ የመፅናትን ያጠቃልላል:: አንቀጽ 20 1 ሁሉም ሰው በሰላማዊ መንገድ የመሰብሰብና የመደራጀት መብት አለው:: 2 ማንም ሰው የየትኛውም ማህበር አባል እንዲሆን ሊገደድ አይችልም:: አንቀጽ 21 1 ሁሉም ሰው በሀገሩ የመንግስት አስትዳደር ውስጥ በቀጥታ ወይም ነፃ በሆነ ሂደት በተመረጡ ተወካዮች አማካኝነት ተሳትፎ የማድረግ መብት አለው :: 2 ሁሉም ሰው የሀገሩን ህዝባዊ አገልግሎቶች የመጠቀም እኩል የሆነ መብት አለው:: 3 የመንግስት ስልጣን በህዝብ ፍላጎጎትና ስምምነት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት:: ይህም የህዝብ ፍላጎተና ስምምነት አለም አቀፍና ለሁሉም እኩል ቢሆን እንዲሁም በምስጢር በሚደረግ የድምፅ መስጠት ምርጫ ወይም ተመጣጣኝ በሆነ ድምፅን የመግለፅ ሁኔታ በየጊዜውና በትክክል በሚፈፀሙ ምርጫዎች የሚረጋገጥ መሆን አለበት:: አንቀጽ 22 እያንዳንዱ ሰው የህብረተሰብ አካል እንደመሆኑ መጠን ማህበራዊ ደህንነቱ የመጠበቅ መብት አለው:: በተጨማሪም በብሄራዊና አለም አቀፍ ጥረትና ትብብር እንዲሁም በመንግስታዊ ድርጅቶችና የሀብት ምንጬች ለክብሩና ለሰብዓዊ ነፃ እድገቱ አስፈላጊ የሆኑ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና የባህል መብቶች በተግባር እንዲረጋገጡለት የመጠየቅ መብት አለው:: አንቀጽ 23 1 ሁሉም ሰው ስራ የመስራትና ከስራ አጥነት የመጠበቅ መብት አለው:: እንዲሁም ነፃ የስራ ምርጫና ፍትሀዊና ተስማሚ የሆነ የስራ ሁኔታ የማግኘት መብት አለው:: 2 ሁሉም ሰው ያለምንም አድልዎ ለተመሳሳይ ስራ ተመሳሳይ ክፍያ የማግኘት መብት አለው :: 3 በስራ ላ ይ ያለ ሰው ለራሱና ለቤተሰቡ ሰብአዊ ክብር ተገቢ ደህንነት መጠበቂያ ዘዴዎች የተደገፈ ትክክለኛና ተስማሚ ዋጋን የማግኘት መብት አለው :: 4 እያንዳንዱ ሰው ጥቅሞቹን ለማስከበር የሙያ ማህበሮችን የማቋቋምና አባልም የመሆን መብት አለው :: አንቀጽ 24 እያንዳንዱ ሰው እረፍት የማግኘትና የመዝናናት መብት አለው እንዲሁም በአግባብ የተወሰኑ የስራ ሰዓቶችና በየጊዜው የእረፍት ጊዜያትን ከደሞዝ ጋር የማግኘት መብት አለው :: አንቀጽ 25 1 እያንዳንዱ ሰው ለእራሱና ለቤተሰቡ ጤንነትና ደህንነት ምግብ ልብስ ቤትና ህክምና አስፍላጊ የማህበራዊ ኑሮ አገልግሎቶችም ጭምር የሚበቃ የኑሮ ደረጃ ለማግኘት መብት አለው :: ስራ ሳይቀጠር ቢቀር ቢታመም ለመስራት ባይችል ባል ወይም ሚስት ቢሞት ቢያረጅ ወይም ከቁጥጥሩ ውጭ በሆኑ ምክንያቶች መሰናክል ቢገጥመው ደህንነቱ እንዲጠበቅለት መብት አለው:: 2 ወላድነትና ህፃንነት ልዩ ጥንቃቄና እርዳታ የማግኘት መብት አላቸው :: በጋብቻ ወይም ያለጋብቻ የሚወለዱ ህፃናትም በተመሳሳይ ደህንነታቸው የመጠበቅ መብት አላቸው:: አንቀጽ 26 1.እያንዳንዱ ሰው የመማር መብት አለው። ትምህርት ቢያንስ ቢያንስ በመሰረታዊና በአንደኛ ደረጃ በነፃ መቅረብ ይገባዋል:: የአንደኛ ደረጃ ትምህርት መማር ግዴታ ነው:: የቴክኒክና የልዩ ልዩ ሙያ ትምህርት በጠቅላላው የከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ደግሞ በችሎታ መሰረት ለሁሉም እኩል መቅረብ አለበት ::
2.ትምህርት ለእያንዳነዱ ሰው ሁኔታ ማሻሻያና ለሰብአዊ መብቶችም እንዲሁም ለመሰረታዊ ነፃነቶች ክብር ማዳበርያ የሚውል መሆን አለበት:: እንዲሁም የተለያየ ዘር ወይም ሀይማኖት ባሏቸው ህዝቦች መካከል ሁሉ መግባባትን ተቻችሎ የመኖርንና የመተባበርን መንፈስ የሚያጠናክርና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላምን ለመጠበቅ የሚፈፅማቸው ተግባራት እንዲስፋፋ የሚደረግ እና የሚያበረታታ መሆን አለበት ::
3.ወላጆች ለልጆቻቸው ለመሰጠት የሚፈልጉትን ትምህርት ለመምረጥ ቅድሚያ መብት አላቸው :: አንቀጽ 27 1 እያንዳንዱ ሰው በህብረተሰቡ የባህል ሕይወት በነፃ መካፈልና በኪነ ጥበብ ለመጠቀም በሳይንስ እርምጃና በጥቅሞቹም ለመሳተፍ መብት አለው:: 2 እያንዳንዱ ሰው ከደረሰው ማንኛውም የሳይንስ የድርሰትና የኪነጥበብ ስራ የሚያገኘው የሞራልና የሀብት ጥቅሞች እንዲከበሩለት መብት አለው :: አንቀጽ 28 ሁሉም ሰው በዚህ ድንጋጌ ውስጥ የሰፈሩት መብቶችና ነፃነቶች ሙሉ በሙሉ በተገባር ሊውሉ የሚችሉበት ማህበራዊና አለም አቀፋዊ የኑሮ ስርአት አባል የመሆን መብቱ የተጠበቀ ነው :: አንቀጽ 29 1 እያንዳንዱ ሰው ለስብእናው ነፃና ሙሉ እድገት ብቸኛ መሰረት ለሆነው ለሚኖርበት ማህበረሰብ ሊፈፅማቸው የሚገቡ ግዴታዎች አሉት:: 2 እያንዳንዱ ሰው በመብቶቹና በንፃነቶቹ በሚጠቀምበት ጊዜ ገደብ የሚያ ጋጥመው የዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ መሰረታዊ መስፈርቶች የሆኑትን ግብረገብነትን ስርዓተ ማህበርና የጋራ ደሀንነትን ለማረጋገጥ እና የሌሎችን መብቶችና ነፃነቶች ለማሳወቅና ለማክበር በህግ የተቀመጡ ገደቦችን እንዳይተላለፍ ብቻ ነው :: 3 እነዚህ መበቶችና ነፃነቶች በማንኛውም ሁኔታ የተባበሩት መንግስትታት መሰረታዊ አላማዎች በሚቃረን መንገድ ሊፈፀሙ አይገባቸውም :: አንቀጽ 30 በዚህ ውሳኔ ላይ የተዘረዘረውን ሁሉ በዚሁ ውስጥ የተጠቀሱትን ማናቸውንም መብቶች ወይም ነፃነቶች የመጣስ ድርጊትን ለመፈፀም ለማንኛውም መንግስት ወይም ድርጅት ወይም ሰው የተከለከለ ነው ::