ከተማዋ የተቆረቆረችዉ በ1747 ዓ/ም በልዕልተ ወለተ እስራኤል እንደሆነ ይነገራል፡፡ ልዕልተ ወለተ እስራኤል የጎንደር ንግስት የነበሩት የእቴጌ ምንትዋብ ልጅ ሲሆኑ ለጎጃሙ ባላባት ለደጅ አዝማች ዮሴዴቅ አቤዴብ ተድረዉ ከጎንደር ወደ ጎጃም መጡ፡፡ልዕልቲቱ ቤተክርስትያን ማሰራት ትወድ ስለነበርና ራዕይ ስላየች የሞጣ ደብረገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያንን እንዲመሰረት እንዳደረገች አባቶች ይናገራሉ፡፡ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያንን የተከለችበትን ምክንያትም አባቶች ሲገልጹ ልዕልቲቱ በራዕይ "ቅዱስ ጊዮርጊስን ካስደበርሽ ከተማዋ ታድጋለች የአንች ህይወት ግን ያልፋል ነገርግን መድሃኔዓለምን ቤተክርስትያንን ካስደበርሽ የአንች እድሜ ይረዝማል ከተማዋ ግን አታድግም" የሚል ራዕይ አይታ ስለነበር ከተማዋ ብታድግና የኔ ህይወት ቢያልፍ ይሻላል በማለት የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያንን እንደደበረች አባቶች ይናገራሉ፡፡ የሞጣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስትያን በምስራቅ ጎጃም ዞን በሞጣ ከተማ አስተዳደር ዉስጥ ይገኛል፡፡ቤተ ክርስትያኑ በ1747 ዓ/ም በልዕልተ ወለተ እስራኤል እንደተደበረ የሃይማኖት አባቶች ይናገራሉ፡፡ቤተክርስትያኑ እንደ አብዛኛዉ የጥንት አብያተ ክርስትያናት አሠራር ክብ ሆኖ የተሠራ ባለግርማ ሞገስ ቤተክርስትያን ሲሆን ጥንታዊ የቅርስ ይዘቱን ሳይለቅ በቅርቡ ጥገና ተደርጎለታል፡፡ በቤተክርስትያኑ የዉስጥ ግድግዳ ላይ ረዥም እድሜን እንዳስቆጠሩ በእይታ የሚታወቁ የግድግዳ ላይ ስዕሎች ይገኛሉ፡፡በቤተክርስተያኑ በተለይ የመጽሀፍት ጉባኤ በዘመናዊ መልኩ መማሪያ ክፍል እና መኖሪያ ቤት በመስራት በጥሩ ሁኔታ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ቤተክርስትያኑ የበርካታ ቅርሶች ባለቤት እንደመሆኑ መጠን እነዚህን ቅርሶች ለጉብኝት ክፍት ለማድረግ ይመች ዘንድ ዘመናዊ ሙዝየም በመገንባት ቅርሶችን ለማስጎብኘት ስራ ተጀምርዋል፡፡