Belay Getaneh

/ተዋናይ፣ደራሲ፣ዳይሬክተር፣ፕሮዲውሰር/


በላይ ጌታነህ የተወለደው 1977 አሰላ ከተማ ውስጥ ሲሆን አባቱ ጌታነህ ወ/አማኑኤል ነጋዴ ሲሆኑ እና እናቱ ፋንታዬ በቀለ ደግሞ የቤት እመቤት ነበረች። ሁለት እህት እና ሁለት ወንድም ሲኖረው እሱ የቤቱ የመሀከለኛው ልጅ ነው። ትምህርቱን ከአምስት አመቱ ጀምሮ በመዋለህፃናት/ኬጂ ሲጀምር ከሁለት አመት ቆይታ በኃላ በሚሲዮናውያን ት/ቤት በሆነው በአሰላ ቅ/ገብርኤል ት/ቤት ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ክፍል ሲማር በኃላ በእናቱ ሞት እና በአባቱ የንግድ ኪሳራ የተነሳ በቤተሰቡ ላይ በደረሰው የአቅም ማጣት ምክንያት  አባትየው 5 ልጆቹን ማሳደግ ባለመቻላቸው  እሱና ከታላቅ ወንድሙ ጋር በመሆን በ8 አመቱ በጊዜው በተከፈተው በጀርመኖች እርዳታ በኦርቶዶክስ ቤ/ክርስቲያን የማደጎ ድርጅት ውስጥ ይገባሉ።


ከዛ በኃላ ባሉት አመቶች አስራ ስምንት አመት እስኪሞላው ድረስ ደብረ ቅዱስ በተባለው ህፃናት ማሳደጊያ ውስጥ ኑሮውን ያደረገ ሲሆን የቀረውን የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በከተማው ሌላ አቅጣጫ ባለ ዶሻ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ተምሮ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በጭላሎ ተራራ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ጨርሶ በመጣለት ነጥብ መሰረት የከፍተኛ ትምህርቱን ለመማር ወደ አዲስአበባ ኮሜርስ ኮሌጅ ተመድቦ በመምጣት የሁለት አመት የፉይናንስ እና ኢንሹራንስ ት/ቱን በዲፕሎማ ተከታትሎ ይወጣል።


ከዛ በኃላ ወደ ስራው አለም ከመቀላቀል ይልቅ ከልጅነቱ ጀምሮ የነበረውን የጥበብ ፍላጎቱን በተለይም የቴአትር እና የፊልም ፍላጎቱን ለማሳካት ወደ ጥበቡ አለም ጎራ ማለት ጀመረ። የበላይ የጥበብ ፍላጎት የጀመረው ከሰባት እና ስምንት አመቱ ጀምሮ አባቱ እየገዛ የሚያስቀምጣቸውን ልቦለድ እና ታሪካዊ መፅሀፍትን ማንበብ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ነው።


በኃላ ይህ ፍላጎቱ ወደ ህፃናት ማሳደጊያው ሲገባ ተመሳሳይ ፍላጎት ካላቸው ታዳጊዎቹ ጋር የበዓላት እና የቅዳሜ ልዩ የትርኢት ፕሮግራም በሚል የዳበረ ሲሆን የሀያስኩል ትምህርት ላይ እያለ ባገኘው ልዩ የቴአትር ስልጠና ተመሳሳይ ፍላጎት ካላቸው የከተማው ወጣቶች ጋር ነፀብራቅ የሚል የቴአትር ክበብ በማቋቋም እና የተለያዩ ቴያትሮችን በመስራት በከተማው እና በወረዳ ከተማዎች እያሳያ የቆየ ሲሆን ወደ አዲስአበባ ከመጣ በኃላም ከትምህርቱ ጎን ለጎን የተለያዩ ቴአትር ቤቶች አካባቢ በተደጋጋሚ ያዘወትር ነበር። በዚህም ምክንያት ከታዋቂዋ ዳይሬክተር አይዳ አሸናፊ ጋር የመጀመሪያውን የትወና ስራዉን የሰራበትን የኤችአይቪ ማስተመሪያነት ላይ ትኩረት አርጎ የተሰራውን ዶክ ድራማ ‘እፎይ’ን በ1996 ከታዋቂ ተዋናዮች ጋር ይሰራል።


ከዛ በኃላ ተስፍዬ አበበ የቴያትር ማደራጃ ውስጥ በመግባት የትወና ስልጠናን በመውሰድ ጎንለጎን የተለያዩ የጥበብ ስራዎች በማድረግ ይቆያል በዚህ ጊዜም በ1997 በሀገሪቱ የምርጫ ዝግጅት ወቅት እንወያይ በተባለ የሰብኣዊና ዲሞክራሲ ተቋም ጋር በመሆን የሰብዓዊ መብቶች እና የዲሞክራያሳዊ ምርጫ አስፈላጊነትን የሚሰብኩ ቴያትር አቅራቦቶችን በሀገሪቱ አራቱም አቅጣጫዎች በመዘዋወር አሳይቷል።


ይህን አይነት እንቅስቃሴ እያደረገ ከቆየ በኃላ ከአንድ ጓደኛው ጋር በመሆን በ1998 ‘መታገስ’ የተሰኘ ፊልም በዝግጅት እና በዋና ተዋናይነት ይሰራል፤ የዚህ ፊልም ፕሮዲውሰር እሱና ጓደኛው ሲሆኑ በስራው ትርፋማ ስላልነበሩ ተስፍ ቆርጦ ባሉበት ሁኔታ እያለ በ1998 መጨረሺያ ላይ የመጣለትን በጊዜው ከፍተኛ አውቅና ያገኘውን የመጀመሪያው የቪሲዲ ወጥ ካራክተር ላይ የተመረኮዘውን ‘ሰው በልኬ’ ወይንም ‘ኦ ማይ ክርስቶስን’ የተሰኘውን ኮሜዲ ፊልም በስክሪፕት ራይተርነት እና በዝግጅት ሰራ በመቀጠል በ1999 በትወናው ተወዳጅ የሆነለትን ‘ሾተል’ የተሰኘ የቪሲዲ ፊልም ሰራ።


በዚህ ወቅት የፊልም ስራ ጥበቡን ከፍ ለማድረግ በ2000 አመተምህርት በቶም ቪድዮግራፊ የሰርተፍኬት ትምህርቱን እና በፊልም ኮርፕሬሽን የሚሰጠውን የፊልም ድርሰት አፃፃፍ ትምህርትን ተከታተሎ ጨረሰ። ጎን ለጎን ቆይቶ የወጣውን ‘እንደቢራቢሮ’ የተሰኘውን የሲኒማ ፊልም በድርሰት፣ በዋና ገፀባህሪ ትወናና በፕሮዲውሰርነት በ2001 ላይ ሰራ።



ከቆይታ በኃላ አብረውት በተስፋዬ አበበ ቴያትር ማደረጃ ይማሩ ከነበሩት ሦስት ጓደኞቹ ጋር በመሆን አስካሁንም ከፍ ያለ ዝናን ያተረፈውን በአለም አቀፍ ደረጃ በኒዮርክ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ምርጥ አለምአቀፍ ሮማስ ኮሜዲ ተብሎ የተሸለመውን፤ በሀገር ውስጥ የተለያዩ ሽልማት ያገኘውና በድርሰት የተሸለመበት እንዲሁም በዳይሬክቲንግ የታጨበት ‘ስላንቺ’ የተሰኘውን ፊልም በጋራ ፀሀፊነት እና በዳይሬክተርነት 2002 ላይ ሰራ።




ከዛ በኃላ 2003 ላይ የመጀመሪያውን የሀይስኩል ፊልም ‘ሌዲስ ፈርስት x’ ን በድርሰት፣ በዳይሬክተርነት፣ እና በፕሮዲውሰርነት ከሰራ በኃላ በመቀጠል እጅግ ተወዳጅ የነበረውን እና በአመቱ ምርጥ የተመልካች ፊልም ተብሎ የተሸለመውን ‘ያንቺው ሌባ ቁ1’ ፊልም 2004 ላይ በደራሲነት እና በዳይሬክተርነት ሰራ።



ሲቀጥልም የወጋገን ኮሌጅ የቴያትር ትምህርቱን እየተከታተለ 2006 ላይ ‘ላ ቦረናን’ በስክሪፕት ራይተርነት እና በዳይሬክተርነት ‘አስታራቂ ቁ1’ 2005 ላይ በደራሲነት ከሰራ በኃላ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን በማታ መርሃግብር በመቀላቀል የመጀመሪያ ዲግሪውን ትምህርትን እየተከታተለ ጎን ለጎን ‘እንቆጳን’ 2007 ላይ በ2008 በስክሪፕት ራይተርነት፣ በዳይሬክተርነት እና በፕሮዲውሰርነት ‘ለኔ ካለሽን’ ሰራ በ2009 ደግሞ ‘ያንቺው ሌባ ቁ2’ን በደራሲነት፣በዳይሬክተርነት እና በፕሮዲውሰርነት ሰራ።



ከዛ በኃላም ባሉት ጊዚያት 2011 ላይ በደራሲነት ‘ጥም ቆራጭ’ እና 2012 ላይ ‘እንሳሮን’ ሰራ። በአሁኑ ሰዓት ከ3 በላይ የሲኒማ ፊልሞች እና ከ6 በላይ የኢንተርኔት ፊልሞች ሁለት የቴሌቪዥን ድራማዎችን በሽያጭ እና በራሱ ፕሮዲውሰርነት እየሰራ ይገኛል።



በተጨማሪምከ2005 ጀምሮ በፌስቡክ የኢትዮጵያ ፊልምሰሪዎችን ግሩፕ በመክፈት በርካታ ፊልም ነክ ጉዳዮችን ሲያወያይ እና መረጃ ሲያለዋውጥ የቆየ ሲሆን  ከ2012 ጀምሮ የፊልም ቋንቋ የቴሌቪዥን እና ፊልም አካዳሚ የሚባል የኢንተርኔት ነፃ የፊልም ትምህርት ቤት በመክፈት በፊልም ርዕሰጉዳዮች ላይ ተከታታይ ትምህርቶችን ለሀገሩ የፊልም እድገት በሚረዳ መልኩ እያቀረበ ይገኛል።