ጴጥራ
ጴጥራ (ከግሪክ πέτρα /ፕትራ/፤ በአረብኛ البتراء /አል-ባትራ/፤ መጽሐፍ ቅዱስ ሴላ፤ ሁላቸው ማለት «ድንጋይ») በዮርዳኖስ አገር የሚገኝ ጥንታዊ ፍርስራሽ ነው። የሕንጻ አሠራሩ በሙሉ ከዓለት የተሠራ ነው። ደብረ ሖር ዳገት ነው።
በጥንታዊ ግብጽ መዝገቦች ከተማው «ፐል»፣ «ሴላ» እና «ሴይር» ይባላል። በኦሪት ዘጸአት ሙሴ ከዕብራውያን ጋር በዚያ ሥፍራ አለፉ። በብሉይ ኪዳን መሠረት የሖር ሰዎች በዚህ አገር ኖሩ፤ በኋላም ኤዶማውያን። በ6ኛው ክፍለ ዘመን ዓክልበ. ጴጥራ የነባትያ ዋና ከተማ ሆኖ ተሠራ። በ98 ዓ.ም. አራቢያ ፐትራያ የሮሜ መንግሥት ክፍላገር ሆነ። በ355 ዓ.ም. የምድር መንቀጥቀጥ ከተማውን አጠፋ። ከበረሃ ኗሪዎች በቀር ለዓለሙ ተረሳ። በ1804 ዓ.ም. የስዊስ ተጓዥ ዮሐን ሉድቪግ ቡርካርት አየው። አሁን ለሥነ ቅርስም ሆነ ለቱሪዝም አይነተኛ ሥፍራ ሆኗል።