የኅሊና ነፃነት ማለት ማንኛውም ግለሠብ ምንምን ሀሣብ፣ እምነት ወይም አስተያየት በጽናት ለመያዝ የሚረጋገጥበት ነጻነት ነው። የሌላ ሰዎች እምነት ምንም ቢሆንም፣ ይህ ነጻነት ለየግለሠቡ ጽኑእ ሆኖ ይቆጠራል።

ኅሊና ነጻነት ለሰዎች ለመከልከል ቢሞከር ኖሮ ይህ የሰው ልጆች መሠረታዊ መብት (ሰው ለራሱ ለማሰብ) እንደ መከልከል ይቆጠራል።

የኅሊና ነጻነት ፍሬ ነገር እያንዳንዱ ግለሠብ ለራሱ የቱን እምነት ለመምረጥ ስለሚሰጥ፣ 'የሃይማኖት ነጻነት' ጽንሰ ሐሳብ ከዚህ ጋር ተያይዟል። በአንዳንድ ህብረተሠብ ወይም መንግሥት በተግባር የሃይማኖት ነጻነት ወይም የእምነት ነጻነት ባይከበርም፣ በሌሎች ህብረተሠብ ወይም ሕገ መንግሥታት ግን በተለይ በምእራቡ አለም ይህ ነጻነት በታሪክ እጅግ ተከብሯል። ለምሳሌ በአሜሪካ ሕገ መንግሥት 1ኛ ማሻሻያ አንቀጽ መሠረት ሃይማኖት ወይም ንግግር የሚከለክል ሕግ እንደማይጸና ይረጋገጣል። ዛሬ በአለም ዙሪያ ደግሞ አብዛኛው ሕገ መንግሥታት የእምነት ነጻነት የሚያረጋግጡ ናቸው። በ1948 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የወጣ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 40 አባባል እንዲህ ነው፦

«የሕዝቡን መልካም ጠባይ ወይም ፀጥታን ወይም በፖለቲካ ረገድ የሚያውክ ካልሆነ በቀር በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ግዛት የሚኖሩ ሰዎች በሕግ መሠረት የሃይማኖታቸውን ሥርዓት አክብረው በነፃ ከመፈጸም አይከለከሉም።»

«የሰብዓዊ መብት አቀፋዊ መግለጽ» አንቀጽ ፲፰ ደግሞ እንደሚለው፣

«እያንዳንዱ ሰው፡ የሃሳብ የሕሊናና የሃይማኖት ነጻነት መብት አለው። ይህም መብት ሃይማኖቱን ወይም እምነቱን የመለወጥ ነጻነትንና ብቻውን ወይም ከሌሎች ጋር በኀብረት በይፋ ወይም በግል ሆኖ ሃይማኖቱን ወይም እምነቱን የማስተማር፣ በተግባር የመግለጽ የማምለክና የማክበር ነጻነትን ይጨምራል።»

እንዲሁም በአንቀጽ ፲፱ ዘንድ፣

«እያንዳንዱ ሰው የሐሳብና ሐሳቡን የመግለጽ መብት አለው። ይህም መብት ያለጣልቃ ገብነት በሐሳብ የመጽናትንና ዜናን ወይም ሐሳቦችን ያላንዳች የድንበር ገደብ የማግኘትን የመቀበልን ወይም የማካፈልን ነጻነትም ይጨምራል።»

የኅሊና ነጻነት ስለ መከልከል

ለማስተካከል

አንድ ተራ ሰው ልጅ ሌሎቹ ሁሉ በእውነት ምን ምኑን እንደሚያሥቡ ለማወቅ ስንኳ ይሁንና ለማስተዳደር በፍጹም አለመቻሉ ግልጽ ስለሚሆን፣ ይህ ኹኔታ የህሊና ነጻነትን ለመከልከል ለሚያስቡ ሰዎች ጽኑ መሰናከል ነው።

የሰውን ሀሣብ ለማስተዳደር በፍጹም እንደማይቻል መጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፈ መክብብ 8፡8 እንዲህ ያስተምራል፦

«በመንፈስ ላይ ሥልጣን ያለው ሰው የለም፤ በሞቱም ቀን ሥልጣን የለውም...»

ተመሳሳይ አስተያየት በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ይገኛል። እዚህ የባልንጀሮቻቸውን ስሜት ለማስተዳደር በከንቱ የሚጣሩ ሰዎች «በገበያ የሚቀመጡትን ልጆች»ን ያስመስላቸዋል፤ ደስታ በእምቢልታ ልቅሶም በሙሾ ለማስገኘት ይሞክራሉና ባለመቻላቸው በቅሬታ ይጮሃሉ። (ማቴ. 11፡16)። ጽንሰ ሃሳቡ እንደገና በቅዱስ ጳውሎስ የተለማ ሲታይ ውሏል። («አርነቴ {ኤለውጠሪያ} በሌላ ሰው ሕሊና {ሱነይዴሰዮስ} የሚፈረድ ኧረ ስለ ምንድር ነው?» 1 ቆሮ. 10፡29)

በሰው ጭንቅላት ውስጥ ምን እንደሚታሠብ ለመወሰን የሚሞክሩ ድንጋጌዎች በታሪክ አጠያያቂ ሆነዋል። ለምሳሌ የእንግሊዝ ንግሥት 1 ኤልሳቤጥ (16ኛው ክፍለ ዘመን) እንዲህ አይነት ሕግ በሠረዙት ጊዜ፣ 'በሰዎች ነፍስና ግል ሀሣብ ላይ መስኮት ለመስራት አልወድም' ብለዋል።

የኅሊና ነጻነት ለዴሞክራሲ መሠረታዊ መርኅ ሲባል፣ የኅሊና ነጻነት የሚከለከልበት ሙከራ የፈላጭ ቁራጭ ወይም አምባገነን መንግሥት ባኅርይ ሆኖዋል። አፈና፣ ማሳደድ፣ መጽሐፍ መቃጠል፣ ወይም ፕሮፓጋንዳ ሁሉ የንግግር ነጻነት ሲወስኑ ይህ ሁናቴ ለኅሊና ነጻነት ጤነኛ አይደለም። ለምሳሌ በሂትለር ዘመን በጀርመን ባለሥልጣናቱ ያልወደዱት ብዙ መጻሕፍት ተቃጥለው ነበር። ዛሬም ባንዳንድ አገራት ውስጥ የንግግር ነጻነት ለመቆጣጠር ሲያስቡ በኢንተርኔት ላይ ማገጃ የሚጣሉ መንግሥታት አሉ። በአንዳንድ ክርክር ዘንድ ደግሞ፣ አደንዛዥ ዕጽ የተለወጠ ሀሣብ ሊፈጥር ስለሚችል፣ እንግዲህ ሕገ ወጥ መሆኑ የኅሊና ነጻነት እንደ መከልከል ሊባል ይችላል።

መጋቢት 2006 ዓ.ም. የሚከተሉት አገራት ፌስቡክትዊተር ወይም ዩ ቱብ ላይ ማገጃ ጥለዋል፦[1]

  • የቻይና ሕዝባዊ ሪፐብሊክ። ፌስቡክ፣ ትዊተርና ዩ-ቱብ ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ ተከለክለዋል። ከመስከረም 2006 ዓም ጀምሮ ግን በሻንግሃይ ከተማ ብቻ ተፈቀዱ።
  • ኢራን። ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ ፌስቡክ፣ ትዊተርና ዩ ቱብ አብዛኛው ጊዜ ተከለክለዋል።
  • ኤርትራ። ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ዩ ቱብ ተከለክሏል።
  • ቬት ናም። ከ2004 ዓ.ም. ፌስቡክ እንደ ተከለከለ ተብሏል፤ ዜጎች ግን በቀላሉ ሊደርሱት ይችላሉ። በመስከረም 2006 ደግሞ ዜጎች መንግሥትን በፌስቡክ እንዳይተቹ የሚል ሕግ ወጣ።
  • ፓኪስታን። ከመስከረም 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ዩ ቱብ ተከለክሏል። በ2002 ዓ.ም. ደግሞ ለጊዜው ፌስቡክን ከለከለ።
  • ቱርክ። በመጋቢት 2006 ዓ.ም. ትዊተርንና ዩ ቱብን ከለከለ።
  • ስሜን ኮርያ። ኢንተርነት በሙሉ በስሜን ኮርያ ለባላሥልጣናት ብቻ ይፈቀዳል።

ባለፉት ጊዜ የሚከተሉት አገራት ለጊዜው ድረ ገጾቹን ተክለክለው አሁን ግን እንደገና ፈቀደዋል።

ደግሞ ይዩ።

ለማስተካከል

የመንግሥት ሃይማኖት

  1. ^ http://www.motherjones.com/politics/2014/03/turkey-facebook-youtube-twitter-blocked
  2. ^ https://opennet.net/research/map/socialmedia