አቡ ዩሱፍ የዕቁብ ኢብኑ ኢስሃቅ አል-ኪንዲ800 እ.ኤ.አ. አካባቢ በኩፋ ነበር የተወለደው። አባቱ የኸሊፋ ሃሩን አር-ረሺድ ባለሥልጣን ነበር። አል-ኪንዲ በአል- መእሙን፣ አል-ሙእተሲም እና በአል- ሙተወኪል (የአባሲ ሙስሊም ኸሊፋዎች) ዘመን የኖረ ሲሆን በዋናነትም በባግዳድ ነው ያደገው።

በአል-ሙተወኪል ዘመን ለኸሊፋው ተቀጥሮ በካሊግራፈርነት (የእጅ ፅሁፍ ጥበብ) ሠርቷል። በፍልስፍና አመለካከቱ የተነሣ የሙስሊሞች ኸሊፋ የነበረው አል-ሙተወኪል ተቆጥቶበት መፅሃፎቹንም ሙሉ በሙሉ የወረሰው ሲሆን ኋላ ላይ ግን መልሦለታል። የሞተውም በ873 በአል-ሙተአሚድ ዘመን ነው። አል-ኪንዲ ፈላስፋ፣ የሂሣብ ሊቅ፣ የፊዚክስ ባለሙያ፣ የስነ-ከዋክብት ተመራማሪ፣ የህክምና ሰው፣ አሣሽ (geographer) እንዲሁም በሙዚቃ አዋቂም ነበር። በነኚህ ዘርፎች ሁሉ ዙሪያ ወጥ የሆነ አስተዋፅኦ ማበርከቱ እጅግ የሚገርም ነው። በነኚሁ በርካታ ሥራዎቹም የተነሣ አል-ኪንዲ “የዓረቡ ዓለም ፈላስፋ” በመባል ይታወቃል። በሂሣብ መስክ በቁጥሮች ሥርዓት (number system) ዙሪያ አራት መፅሃፎችን የፃፈ ሲሆን ለአብዛኛው ዘመናዊ አሪትሜቲክ ክፍልም መሠረት ያስቀመጠው እሱ ነው። ምንም እንኳ አብዛኞቹ የዐረብኛ ቁጥሮች የጎለበቱት በእውቁ የሂሣብ ሊቅ በአል-ኸዋርዝሚ ቢሆንም አል-ኪንዲም ተጨማሪ ጉልህ የሆኑ አስተዋፅኦዎችን አክሎበታል። አል-ኪንዲ ለሥነ ከዋክብት ጥናት ለሚያግዘው ስፈሪካል ጂኦሜትሪ / spherical geometry/ ያበረከተው አስተዋፅኦም ቀላል አልነበረም። በኬሚስትሪ በኩል ብረት-ነኬ ቤዞች (base metals) ወደ ውድ ብረቶች (precious metals) ሊቀየሩ ይችላሉ የሚለውን ሀሣብ የተቃወመ ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ በዘመኑ የተንሰራፋውን የአል-ኬሚያን እይታ በመቃወም በኬሚካል ፅግበራ (chemical reactions) የተነሣ የንጥረ-ነገሮች (elements) ትራንስፎርሜሽን (ሙሉ ለሙሉ የንጥረ-ለወጥ) አይከሠትም በሚለው ላይ አፅንኦት ሠጥቷል። በፊዚክስ በኩል ለጂኦሜትሪካል ኦፕቲክስ / geometrical optics/ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከተ ሲሆን በዚሁ ዙሪያም መፅሃፍ ፅፏል። ይህ መፅሃፍ ኋላ ላይ ሮጀር ባኮንን /Roger Bacon/ ለመሣሠሉ እውቅ ሣይንቲስቶች መነቃቃትንና መንገድን አመላክቷል። በህክምናው ዘርፍ ደግሞ በዚያ ዘመን ይታወቁ ለነበሩት መድሃኒቶች ሁሉ ስልታዊ በሆነ መንገድ የአጠቃቃም መጠናቸውን ለማስቀመጥ ከፍተኛ አስተዋፅ ነበረው። ይህም በሃኪሞች ዘንድ በአጠቃቀም መጠን ዙሪያ ይነሣ የነበረውንና መድሃኒት ለማዘዝ ይቸገሩበት የነበረውን ሁኔታ አስወግዷል። በሱ ዘመን ስለ ሳይንሣዊ ሙዚቃ የነበረው እውቀት እጅግ በጣም ኢምንት ነበር። በዚህ ዙሪያም መጣጣምን (harmony) ለመፍጠር የሚያግዙ በርካታ የሙዚቃ ኖታዎች (notes) የየራሣቸው የሆነ ክረዜማ (pitch) እንዳላቸውና በዚህም የተነሣ እጅግ አነስተኛ አሊያም እጀግ ከፍተኛ ኖታ ያላቸው ክረዜማ አስደሳች አለመሆናቸውን አመልክቷል። የመጣጣም ደረጃ በኖታ ድግግሞሽ (frequency of notes) ላይ መወሰኑንም አብራርቷል። ከዚህም ሌላ ድምፅ ሲፈጠር በአየር ውስጥ የጆሮን ታምቡር የሚመታ ሞገድ የሚያመነጭ መሆኑንም ጠቁሟል። ሥራው ክረዜማን በመወሰኑ ዙሪያ ጠቃሚ ማስታወሻዎችን ይዟል። በሌላ በኩል ደግሞ ዉጤታማ ፀሃፊ የነበረ ሲሆን በሱ የተፃፉ መፃህፍትም 241 ያህል ይደርሣሉ። እጅግ የታወቁትን በዚህ መልኩ ልንከፍላቸው እንችላለን:- አስትሮኖሚ 16፣ አሪትሜቲክ 11፣ ጂኦሜትሪ 32፣ ህክምና 22፣ ፊዚክስ 12፣ ፍልስፍና 22፣ ሎጂክ 9፣ ሥነ-ልቦና 5፣ ሙዚቃ 7 ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ በማዕበል (tides)፣ በሥነከዋክብት መሣሪያዎች፣ በአለት፣ በውድ ድንጋዮችን እና በመሣሠሉት ዙሪያ በርከት ያሉና ለሣይንስ እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ፅሁፎችን ፅፏል። የግሪክ ሥራዎችን ወደ ዐረብኛ ከተረጎሙት ቀደምት ሰዎች መካከልም የሚጠቀስ ነው። ነገር ግን ይህ እውነታ በቁጥር በርካታ በሆኑ ወጥ ሥራዎቹ ሊሸፈን ችሏል። ያለመታደል ሆኖ በርካታ መፅሃፎቹ ዛሬ የሉም። ያሉት ግን አል-ኪንዲ የነበረበትን የመጠቀ የእውቀት ደረጃ የሚመሠክሩ ናቸው። አል-ኪንዲ በላቲኖች አልኪንዱስ / Alkindus/ በመባል የሚታወቅ ሲሆን በርካታ መፅሃፎቹም በክሬሞናዊው ጄራርድ (Gherard of Cremona) አማካይነት ወደ ላቲን ተተርጉመዋል። በመካከለኛው ዘመን ወደ ላቲን ከተተረጎሙ መፅሃፎቹ መካከል “ሪሣላ ዳር ተንጂም”፣ “ኢክቲያራት አል- አያም”፣ “ኢላሂያቱ አሪስቱ”፣ “አል-ሙሲቃ”፣ “መድኡ ጀዝር” እና “አድዊያ ሙረከባ” ይገኙበታል። በሣይንስ እና በፍልስፍናው በኩል በዚያን ዘመን ለነበረው የሣይንስ ማንሠራራት የአል- ኪንዲ ተፅእኖ ቀላል አልነበረም። በመካከለኛው ዘመን በዘመኑ ከነበሩት አሥራ ሁለት ትላልቅ ምሁራን መካከል አንዱ እንደነበረ ካርዳኖ /Cardano/ መስክሮለታል። ሥራዎቹ በርግጥም በበርካታ ጉዳዮች ላይ ትልቅ ለውጥና እድገትን ያመጡ ሲሆን በተለይም ፊዚክስ፣ ሂሣብ፣ ህክምናና ሙዚቃ በዋናነት ይጠቀሣሉ።