ናስ ዘመን ወይም የነሐስ ዘመን በ«ሦስቱ ዘመናት» አስተሳሰብ ከድንጋይ ዘመንና ከብረት ዘመን መካከል የነበረው ዘመን ነው። በአጠቃላይ እንደ ተለመደ ከ3125 እስከ 1200 ዓክልበ. ያህል ያመልክታል። በዚህ ዘመን አብዛኞቹ መሣርያዎችና እቃዎች የተሠሩ ከናስ (መዳብና የቆርቆሮ አብረው በአቃላጭ ተቀላቅለው) ነበር።

የናስ ጥቅም በጥንታዊ ግብጽ ከ3125 ዓክልበ. ግድም ጀምሮ ይታወቅ ነበር። ሆኖም በሰርቢያ (አውሮፓ) የተገኙ የናስ ቅርሶች ከ7000 ዓክልበ. እንደ ሆኑ በአንዳንድ ሥነ ቅርስ ሊቆች ተብለዋል፤ ይህ አቈጣጠር ተከራካሪ ነው።

ብረት ቀለጣ ምናልባት ከ1880 ዓክልበ. ግድም ጀምሮ በሐቲ አገር ይታወቅ ነበር (ካሩም ይዩ)። ዳሩ ግን የብረት መሣርዮች በጅምላ ተሥረው የነሐስ እቃዎች የተኩ ከ1200 ዓክልበ. በፊት አልሆነም። ከ1200 ዓክልበ. በኋላ «የብረት ዘመን» ሊባል ይችላል። የብረት ጥቅም ደግሞ በአውሮፓ፣ በእስያና በአፍሪካ በሙሉ ከ400 ዓክልበ. በፊት ተስፋፋ። የናስ ቀለጣም በደቡብ አሜሪካ ይታወቅ ነበር፤ ከ800 ዓም ያህል በኋላ እስከ መካከለኛ አሜሪካ ድረስ ተስፋፋ፤ ከሜክሲኮ ስሜን ግን አውሮፓውያን ሳይገቡ ቀለጣ ከቶ አልተገኘም።