«እንደ ጦልሃ ጃዕፈር ማን ይወለዳል?»

19ኛው ክ/ዘመን ኢስላም በኢትዮጵያ ከፈራቸው ጀግኖች መካከል ሼክ ጦልሃ ቀዳሚ ብርቅዬ ሙጃሂድ ነበሩ። ሼኹ ሙጃሂድብቻ ሳይሆኑ የዲን መምህር፣ ገጣሚ ፣ ፀሀፊና ዓሊም ጭምር ናቸው። ለጭቆና እጅ የማይሰጡ ፣ ስብዕናቸው ማራኪ፣ አስተሳሰባቸው ምጡቅ የዘመናቸው ዛሂድ ነበሩ።

ጦልሀ ጃእፈር የተወለዱት በ1853 እ.ኤ.አ. አሬራ ፍራ በሚባል ቦታ በአርጎባ ይፋት ነበር። በ1835/6 የሞቱት አያታቸው አባ አሲያ ዩሱፍ ቃንቄ ታዋቂ ዓሊምና ፀሀፊ ነበሩ። የጦልሃ አባት ሐጂ ጃዕፈር ወሎ ደዌ ውስጥ ስርጤ በተባለች መንደር እንደተወለዱ ይነገራል። ቆራጡ ልጅ ጦልሃ ዒልምን ፍለጋ በወሎና በሌሎችም ቦታዎች በመዘዋወር ከተለያዩ መሻኢኾች እውቀትን ቀስመዋል። የቁርአን ተፍሲርን በጨኖሐጂ በሽር አረፍ ልቤ በምትባል ቦታ ተምረዋል። ሸኽ ዒሳ ከተሰኙ ዓሊም ላይ ደቡብ ወሎ-አንቻሮ በዴሳ በተባለች ቦታ የአረብኛ ቋንቋ ሰርፍ ተምረዋል። ተውሂድ ከእናታቸው የተማሩ ሲሆን የፊቅህ ትምርታቸውን ከሐጂ ወራቅ፣ ከሐጂ ቡሽራና ከሌሎችም ዝነኛ የቃሉ ፈቂሆች ብዙ ኢልም ቀርተዋል። በተለይም ከሐጂ ቡሽራ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ነበራቸው።

ሸኽ ጦልሃ ኢስላምን በሚገባ ከተማሩ በኋላ በዳእዋና በማስተማር ተሰማሩ። ኢስላምን ህዝቡ በሚገባው ቋንቋ ከማስተማር ጎን ለጎን የተለያዩ ፅሁፎችንም ያዘጋጁ ነበር። በአማርኛ ከፃፏቸው መፃህፍት መካከል [[ተውሂድና ፊቅህ]]፣ ሂዳየቱ ሱብያንቱህፈቱል ኢኽዋን፣ የተሰኙት ኪታቦቻቸው በስፋት ይታወቃሉ። ከዚህም በተጨማሪ የነቢዩ ሙሀመድን (ሰ.አ.ወ) የህይወት ታሪክ [[ሲየር ረሱሉላህ]] በሚል በ4 ጥራዝ (volume) አዘጋጅተዋል። ለመጀመርያ ጊዜም የቁርአን ትርጉምን በአማርኛ ቋንቋ አዘጋጅተዋል። ሸኽ ቡሽረል ከሪም እንዳሉት ሸኽ ጦህሃ በአጠቃላይ 314 ኪታቦችን ፅፈዋል። ከነዚህም ውስጥ ከሽፉል ጉማቸርነትህአስሀበል ፉቱህሰብልዓ መሳኒ፣ [[ወዕዝ]፣ ጅሀድሱብንሀ አላህአል ዓሊዩል ኸቢርበርሱ ተባረክአስማኡል ሑስና እና አስማኡ ረሱል የተሰኙት በተለያዩ ጥናቶች ሊታወቁ ችለዋል።

ሸኽ ጦልሃ ማቅራት ሲጀምሩ በእጃቸው ኪታብ እያግጋጁ ለተማሪዎች ያድሉ ነበር። ሲሞቱ በእጅ የፃፏቸው ኪታቦች በሰባት ታላላቅ ሳጥኖች ሙሉ ነበሩ። በ1951 የሼኹ "ተውሂድና ፊቂህ" የተሰኘ መፅሀፍ በይሰድ ኢብራሂም ታርሞ ለህትመት በቅቷል። ይህም ለመጀመርያ ጊዜ የታተመ ኢስላማዊ የአማርኛ መፅሀፍ ያደርገዋል። ሸኽ ጦልሃ በወጣትነታቸው ተውሂድን በማስተማር ህዝቡን ከባዕድ አምልኮና ከሺርክ ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ከግጥሞቻቸው መካከል ሺርክን የሚኮንኑ ወደ ተውሂድ የሚጣሩ በርካታ ስንኞች ይገኛሉ። ለምሳሌ ያክል፥፦

በሰላሳ ገዝቶ ቀብድ ተማረድ፣

ደስ ያሰኝ ነበር ለብዙ ዘመድ፣

ለዒሳም ቢታረድ ለኛም ሙሀመድ፣

መበከቱ አይቀርም ሳይሆን ለዋሂድ (ለአላህ)።

ሼኽ ጦልሃ ዘካን ሰብስበው ለደሀው ያከፋፍሉ ነበር፣ የነብዩን ሱና አጥብቀው ይከተላሉ። አለባበሳቸው በሱናው መሰረት ነው። ሱሪያቸው ከቁርጭምጭሚታቸው አይወርድም። ሱሪውን ያስረዘመ ሰው ሲያዩም "እግርህ ይቆረጥ" ይሉ ነበር። የሚለብሱትም በደረሶች የተሰሩ ልብሶችን ነው። ቀለም የበዛበትና ስዕል ያለው ልብስ በፍፁም አይለብሱም (ነጭ ልብስ ያዘወትራሉ)። ልጆቻቸውም በሚድሩበት ጊዜም ሆነ በሌላ ሰርግ ላይ ሸሪዐን የሚቃረን ነገር (የሴትና ወንድ መደባለቅን የመሰለ) እንዳይፈፀም ይጠነቀቁ ነበር። ክፍል ሁለት