2 አጉም ካክሪሜ እንደሚታሠብ ከካሣውያን ነገሥታት መጀመርያው ባቢሎንን የገዛው ነበር (1507-1483 ዓክልበ. ግድም)። ካሣውያን ለብዙ አመታት በቂ መዝገቦች ስላልጻፉ ይህ እርግጥኛ አይደለም።

«የአጉም ካክሪሜ ጽላት»

ኬጥያውያን መንግሥት ንጉሥ 1 ሙርሲሊ በ1507 ዓክልበ. ከአናቶሊያ (ሐቲ) ደርሶ ባቢሎንን በሙሉ አጠፋት፣ የጣዖቷንም የማርዱክን ሐውልት ዘርፎ ወደ ሐቲ ተመለሰ። ከዚህ በኋላ ባቢሎን «ካርዱኒያሽ» ተብላ በካሣውያን ብሔር እንደ ተገዛች ይታወቃል።

ከዘመኑ የሆነው መረጃ ባይኖርም በኋላ ዘመናት የተቀረጹ ታሪኮች በጣም ትንሽ ይጨምራሉ። ከአንዳንድ ዝርዝሮች መጀመርያው ካሣዊ ንጉሥ «ጋንዳሽ» ተብሏል። እንዲሁም በኒፑር በተገኘ በአንዱ ተማሪ ጽሑፍ ዘንድ (700 ዓክልበ ግ.)፣ «ጋዳሽ» ከ«ባባላም» ጥፋት በኋላ «የአለም አራት ሩቦች፣ የሱመርአካድና ባቢሎን ንጉሥ» ሆነ። ይህ ግን ከብዙ ዘመን በኋላ በመጻፉ እንደ ትክክል መረጃ አይቆጠረም። ብዙ መምህሮች አሁን እንደሚያስቡት፣ ከጋንዳሽ እስከ 2 አጉም ድረስ የተዘረዘሩት ነገሥታት ከባቢሎን ውድቀት በፊት በዛግሮስ ተራሮች የገዙት ነበሩ። 2 አጉም ግን በአንዱ ቅርስ (VAT 1429) የባቢሎን «ቡካሹ» (መስፍን) ስለ ተባለ፣ ባቢሎን ካሣዊ ግዛት መሆኗ በዚሁ አጉም እንደ ጀመረ ዛሬ ይታስባል።

ስለ አጉም ካክሪሜ በተለይ የምናውቀው ድርሰት በነነዌ አሦር በተገኙ ሁለት ቅጂዎች ናቸው። መጀመርያው ጽሑፍ በውኑ በንጉሥ አጉም ካክሪሜ ከተጻፈ ግን አይታወቅም። በዚህ ጽሑፍ መሠረት፣ የአጉም ካክሪሜ ትውልድ ሐረግ ከቀደሙት ካሣውያን አለቆች ታላቁ 1 አጉም፣ 1 ካሽቲሊያሽ፣ አቢ-ራታሽ እና ከአባቱ ኡር-ሺጉሩማሽ ይሰጣል። የአጉም-ካክሪሜ ማዕረግ «የካሣውያንና የአካዳውያን ንጉሥ፣ የባቢሎኒያ ንጉሥ፣ ቱፕልያሽን (ኤሽኑናን) የሰፈረው፣ የአልማንና የፓዳን ንጉሥ፣ እና የጉታውያን ሞኞች ንጉሥ» ይባላል። በዚህም ጽሑፍ ዘንድ፣ የጣዖቱ ማርዱክ ሐውልት ከባቢሎን ተዘርፎ ንጉሥ አጉም-ካክሪሜ ግን ከሩቅ ኻና አገር በክብር ወደ ባቢሎን አስመለሰው። ብዙ መምህሮችም በ«ኻና» ፈንታ ጣዖቱ የተመለሰው ከ«ሐቲ» አገር ማለት ነበረበት ይላሉ።

«የማርዱክ ትንቢት» የተባለ ሌላ ጽላት ከ700 ዓክልበ. ግ. እንዳለው የንጉሥ አጉም ስም ባይጠቅስም የማርዱክ ሐውልት ከተወሰደው 24 አመታት በሐቲ አገር ከቆየ በኋላ ወይም በ1483 ዓክልበ. ወደ ባቢሎን ተመለሰ፣ ይህ ግን ምንም ታማኝ አይታስብም።

ቀዳሚው
ሳምሱ-ዲታና
ባቢሎን ንጉሥ
1507-1483 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
1 ቡርና-ቡርያሽ

መጣቀሻዎች ለማስተካከል