የዓለም ሊቀ ሊቃውንት፣ የኪነ ጥበብ ምሑር የተከበሩ ሰዓሊ አፈወርቅ ተክሌ

በዓለም የታወቁና የተከበሩት ኢትዮጵያዊ ሰዓሊ አፈወርቅ ተክሌ በሰሜን ሸዋ በምትገኘው የሸዋ ነገሥታት ከተማ አንኮበር ላይ ጥቅምት ፲፫ ቀን ፲፱፻፳፭ ዓ/ም ከአባታቸው አቶ ተክሌ ማሞ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ፈለቀች የማታወርቅ ተወለዱ። ገና በጨቅላ ዕድሜያቸው ፋሺስት ኢጣልያ ኢትዮጵያን በግፍ ሲወራት፣ የልጅነት ትዝታቸውም ይሄው የግፍ ወረራ እና ጦርነት የሚያስከትለው የሰው፣ የንብረት እና የባህል ጥፋት ፤ ከነጻነትም በኋላ ዐቢዩ ሥራ በወረራ የተበላሸችውን ሀገራቸውን እንደገና መገንባት እንደሆነ ነው። ለዚህም የሀገር ግንባታ አስፈላጊውን እውቀት መሸመት የፈለጉት በ ማዕድን ምሕንድስና ዘርፍ ነበር። ወላጆቻቸውና ዘመድ አዝማዶች ግን የኪነ ጥበብ ስጦታቸውን በቤታቸውና በከተማው ዙሪያ በሚስሏቸው ስዕሎች ተገንዝበውት ነበር።

የመጀመሪያና መካከለኛ ትምህርታቸውን የት እና መቼ እንዳጠናቀቁ የተጻፈ መረጃ ባይገኝም፤ ገና በአሥራ አምስት ዓመታቸው በ ፲፱፻፵ ዓ/ም ለከፍተኛ ትምህርት ተመርጠው የምሕንድስና ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ እንግሊዝ አገር ይላካሉ። ተሰዳጅ ተማሪ ወጣቶቹ ንጉሠ ነገሥቱን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ሲሰናበቱ፣ አፈወርቅ ተክሌ ጃንሆይ የሰጧቸውን ምክር ሁሌም እንደሚያስታውሱት ይናገራሉ። “ንጉሠ ነገሥቱ ተግታችሁ አጥኑ፣ ተማሩ ብለው ከመከሩን በኋላ ጠንክራችሁ መሥራት እና ሀገራችሁ ኢትዮጵያን የምትገነቡበትን ዕውቀት ይዛችሁ ተመለሱ። ስትመለሱ አዕምሯችሁ ዝግጁ የሆነ እውቀታችሁም ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚችል ጥበብን ሸምቶ እንዲመለስ ነው እንጂ አውሮፓ ውስጥ እንዴት ያሉ ረዣዥም ፎቅ ቤቶች እንዳሉ ወይም መንገዶቻቸው የቱን ያህል ስፋት እንዳላቸው እንድትነግሩን አይደለም።” ነበር ያሏቸው።

አፈወርቅ ተክሌ በእንግሊዝ አገር የአዳሪ ተማሪ ቤትን ኑሮ ሲያስታውሱ የባዕድ ባህላት፣ የአየር ለውጥ እና የተለመደው የተማሪ ቤት ዝንጠላ እንዳስቸገራቸው ያወሳሉ። ቢሆንም ትምሕርታቸውን በትጋት ሲከታተሉ ቆዩ። በተለይም በሒሣብ፣ በፖካርሲን (chemistry) እና በታሪክ ትምሕርቶች ጥሩ ውጤት በማምጣት ሰለጠኑ። ነገር ግን አስተማሪዎቻቸው የተፈጥሮ ስጦታቸው ኪነ ጥበብ እንደሆነ ለመገንዘብ ብዙ ጊዜም አልወሰደባቸውም። በነሱም አበረታችነት በእዚህ ስጦታቸው ላይ የበለጠ ለማተኮር ወስነው በሎንዶን የኪነ ጥበብ ማእከላዊ ትምሕርት ቤት (Central school of Arts & Crafts) ተመዝግበው ገቡ:: እዚህ ትምህርት ቤት ጥምሕርታቸውን ሲያጠናቅቁ ለከፍተኛ ጥናት በስመ ጥሩው የሎንዶን ዩኒቨርሲቲ የስሌድ ኪነ ጥበብ ማዕከል (Faculty of Fie Arts at Slade) የመጀመሪያው አፍሪቃዊ ተማሪ (ከተከተሏቸው አፍሪቃውያን አንዱ የሱዳን ተወላጁ ኢብራሂም ኤል ሳላሂ ናቸው) በመሆን ገቡ። እዚህ በስዕል፣ ቅርጽ እና በስየቃ (architecture) ጥናቶች ላይ አተኩረው ተመረቁ። ትምሕርታቸውን አጠናቀው ወደኢትዮጵያ ሲመለሱ፣ የዓለም ሊቀ ሊቃውንት፣ የኪነ ጥበብ ምሑር የተከበሩ ሰዓሊ አፈወርቅ ተክሌ በየጥቅላይ ግዛቶቹ እየተዘዋወሩ፣ በየቦታው እስከ ሦስት ወራት በመቀመጥ የኢትዮጵያን ታሪክ እና የብሔረሰቦቿን ባህልና ወግ ሲያጠኑ ቆዩ። “ምኞቴ በዓለም የታወቀ ኢትዮጵያዊ የኪነ ጥበብ ምሑር መሆን ስለነበር፣ የአገሬን ወግና ባሕል ጠንቅቄ ማወቅና ማጥናት እንዳለብኝ አውቄያለሁ። ሥራዬ የዓለም ንብረት ይሆናል ነገር ግን በአፍሪቃዊነት ቅመም የጣፈጠ ሥራ ነው የሚሆነው።” ይሉ ነበር። ከሁሉም በላይ ግን የዓለም ሊቀ ሊቃውንት፣ የኪነ ጥበብ ምሑር የተከበሩ ሰዓሊ አፈወርቅ ተክሌ፤ የላቀው ድካማቸውና የምናየውም ውጤት፣ የኪነ ጥበብ ሥራቸው የአገራቸውን ታሪክ የሚያንጸባርቅ ሕብረተ ሰብአዊ መሣሪያ እንዲሆን ነው። በውጭ የተማሩ ቢሆኑም፣ እሳቸው ‘ዋጋ ቢስ’ የሚሉትን፣ እንደሌሎች (ምዕራባውያንም ሆኑ ሌሎች) የሚጠቀሙበትን ‘ኩረጃ’ ላለመከተል በትጋት ተፋልመዋል።

ወደ ውጭ ሊሄዱ ሲነሱ የሰሙትን የንጉሠ ነገሥቱን ቃላት ‘….ኢትዮጵያን ለመገንባት አዕምሯችሁ ዝግጁ ይሁን፣ ለዚህም የሚጠቅም ጥበብን ሸምቱ…” ያሏቸው ቃላት አሁንም በውስጠ ጆሯቸው እያስተጋቡ፤ ከውጭ ሲመለሱ የተመደበላቸውን ሚኒስቴራዊ ሥራ ትተው የኪነ ጥበብ ሥራቸው ላይ በማተኮር ስዕሎቻቸውን በአገር ውስጥም በውጭ አገርም እያሳዩ ለማገልገል ቆረጡ። በሀያ ሁለት ዓመታቸውም በ፲፱፻፵፮ ዓ/ም ሥራቸውን የሚያሳይ የመጀመሪያውን የኪነ ጥበብ ትርዒት በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አቀረቡ። ወዲያውም ከዚህ ትርዒት ባገኙት ገቢ ተመልሰው ወደአውሮፓ በመሄድ ለሁለት ዓመት በኢጣልያፈረንሳይእስፓኝፖርቱጋልብሪታንያ እና ግሪክ አገሮች የጠለቀ የኪነ ጥበብ ጥናት አከናወኑ። በተለይም በነኚህ አገሮች ውስጥ በስደት የሚገኙትን የኢትዮጵያ ጥንታዊ ሃይማኖታዊ የብራና መጻሕፍት በጥልቅ አጠኑ። እንዲሁም የመስታወት ስዕል (stained glass art) እና የ’ሞዜይክ’ አሠራርን ጥበብ ተምረው ወደአገራቸው ተመለሱ።

በዚህ በሁለተኛ መልሳቸው ንጉሠ ነገሥቱ የመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንን በሃይማኖታዊ የግድግዳና ጣሪያ ስዕሎች፣ የ’ሞዜይክ’ ሥራዎች፣ መስኮቶቹንም በመስታወት ስዕሎች እንዲያሳምሩት ቀጥረዋቸው አሁን የምናያቸውን እንደ “የዳግማዊ ምጽአት ፍርድ”፣ የእመቤታችንን ንግሠት የሚያሳየው “ኪዳነ ምሕረት”፣ እና የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን የዘውድ ስርዓት የሚያሳዩ ሥራዎቻቸው ይገኙበታል። አከታትለውም አሁን በሐረር ከተማ የሚገኘውን የልዑል ራስ መኮንንን ሀውልት ሠሩ። የስዕል እና ሌላ የኪን ሥራዎቻቸው ወዲያው በ’ቴምብሮች’፣ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የኪነ ጥበብ ትርዒት ላይ እጅግ በጣም እየታወቁና እየገነኑ መጡ።

የዓለም ሊቀ ሊቃውንት፣ የኪነ ጥበብ ምሑር የተከበሩ ሰዓሊ አፈወርቅ ተክሌ ማክሰኞሚያዝያ ፪ ቀን ፳፻፬ ዓ/ም በተወለዱ በ፸፱ ዓመታቸው፤ በቅርብ ባደረባቸው ጽኑ ሕመም በሕክምና እየተረዱ ሳለ በካዲስኮ ሆስፒታል አርፈዋል።

ምንጮች ለማስተካከል