አስተዳደግና የትምህርት ዘመናት ለማስተካከል

ፕሮፌሶር አሸናፊ ከበደ አዲስ አበባ ግንቦት ፰ ቀን ፲፱፻፴ ዓ/ም ተወለዱ።አባታቸው ግራዝማች ከበደ አድነው ሲሆኑ ክልጅነታቸው ጀምሮ የሙዚቃ ስሜትንና ፍቅር ያሳደሩባቸው እናታቸው ወይዘሮ ፋንታዬ ነከሬ ነበሩ። አያታቸው ሊቀመኳስ አድነው ጎሹ ደግሞ የአድዋ አርበኛ እናየንግሥት ዘውዲቱም ታማኝ አማካሪ እንደነበሩ ይነገራል።[1] የሙዚቃ ፍቅርን ገና በልጅነታቸው ያሳደሩባቸው እናታቸው ሲሆኑ ታዳጊው አሸናፊ ገና የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳሉ እኒህ የሚያፈቅሯቸውና ዕድሜ ልካቸውን በኀዘን የሚስታውሷቸው እናታቸው ሞተውባቸዋል።

መሠረታዊ ትምህርታቸውን በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት እና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ኮከበ ጽባሕ) ካጠናቀቁ በኋላ በሐረር የመምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጅ ተመርቀዋል። ከፍተኛ ትምህርታቸውን ደግሞ በኒው ዮርክ ክፍለ-ሀገር ከሚገኘው የሮቼስተር ዩኒቨርሲቲ፣ “ኢስትማን የሙዚቃ ትምህርት ቤት” በ፲፱፻፶፬ ዓ/ም በመጀመሪያ ዲግሪ ከተመረቁ በኋላ ወደኢትዮጵያ ተመልሰው፤ የያሬድ ሙዚቃ ትምሕርት ቤትን መሠረቱ። የዚሁ ትምህርት ቤትም የመጀመሪያው ዳይሬክቶር ከመሆናቸውም ባሻገር በአዲስ አበባው የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወ.ወ.ክ.ማ Y.M.C.A.)፤ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የበጎ አድራጎት ድርጅት መርሓ-ዕውራን ትምህርት ቤት እና በመሳሰሉ የወጣቶች ማኅበራት እየተገኙ የሙዚቃ ትምህርት ይሰጡ ነበር።

በኢትዮጵያ የሥራ አገልግሎት ለማስተካከል

የያሬድ ትምህርት ቤት ዲሬክቶር ሆነው ከ ፲፱፻፶፭ዓ/ም እስከ ፲፱፻፷ ዓ/ም ድረስ ባገለገሉበት ወቅት በንጉሠ ነገሥቱ “ብሔራዊ የሙዚቃ አቀናባሪ”[2] ተብለው ከመሠያማቸውም ሌላ ለባሕላዊ ጉዳዮች ላደረጉት የላቀ ተዋጽዖ በ፲፱፻፶፱ ዓ/ም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በጎ አድራጎት ድርጅት ተሸላሚ ሆነዋል። የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የ፸፭ኛ የልደት በዓል በተከበረበት በዚሁ ዓመተ ምኅረት በሁንጋሪያ መንግሥት ተጋብዘው ወደ ቡዳፔስት በመጓዝ ታዋቂውን «እረኛው ባለዋሽንት» እና «የኢትዮጵያ ሲንፎኒያ” የተባሉትን ሁለት ድርሰቶቻቸውን በአቀናባሪነትና በኦርኬስትራ መሪነት አቅርበው፤ በሸክላ አሳትመዋል። መታሰቢያነቱንም ለጃንሆይ የልደት በዓል አበርክተዋል። ከሸክላው የሚገኘውን ገቢ በወቅቱ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሥር ይተዳደር ለነበረው የመርሐ-ዕውራን ትምህርት ቤት ለግሠዋል። ፕሮፌሶር አሸናፊ ከበደ ‘ጥቁሩ ኮዳሊ’ የሚለውን ማቆላመጫም ያገኙት የረቂቅ ሙዚቃ ድርሰታቸውን በሁንጋሪያ ውስጥ ከ’ፊልሃርሞኒክ ኦርኬስትራ’ው ጋር በሳቸው ሙዚቃ መሪነት ባቀረቡበት ጊዜ ነበር።

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለተመልካቾች ባቀረበው፣ የሕይወት ታሪክ ዳሰሳ ቅንብር ላይ አብሮ አደግ ጓደኛና ሚዜያቸውም የነበሩት፣ ደራሲው አቶ አስፋው ዳምጤ፤ ፕሮፌሶር አሸናፊን ከያሬድ ትምህርት ቤት መልቀቅና ወዲያውም ከአገራቸው ለመሰደድ ያበቃቸው ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ የተማሪዎች የረቂቅ ሙዚቃ ቅንብር በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አዳራሽ አዘጋጅተው፣ ንጉሠ ነገሥቱ እንዲገኙ በሚኒስትሩ በኩል ያቀረቡት ጥሪ እንደሚደርስ ባለመተማመን በሌላ መንገድ አድርሰው ንጉሠ ነገሥቱ በተገኙበት ለሕዝብ ቀርቧል። ሆኖም በዚህ የተቀየሙት ሚኒስትሮችና የቀጥታ ዓለቆቻቸው በያዙት ቂም እሳቸውን ከዲሬክተርነት አውርደው በምትካቸው አንድ ተራ የክቡር ዘበኛ ባንድ ተጫዋች የነበረ የውጭ ዜጋ አስገቡ። “አገር ትቶ ሲሄድ፤ አይ! እኔ መቼም በገዛ አገሬ ሁለተኛ ዜጋ አልሆንም!” ብሎኛል ይላሉ። [3]

በስደት ዘመናት ለማስተካከል

ለከፍተኛ ትምህርት ወደአሜሪካ በተመለሱ ጊዜ የሙዚቃ ጥናታቸውን አጠናቀው፣ የ’ማስተሬት ዲግሪ’ በ፲፱፻፷፩ ዓ/ም፤ በ’ዶክቶር’ነት ደግሞ በ፲፱፻፷፫ ዓ/ም ከ’ዌስሊያን ዩኒቨርሲቲ’ ተመረቁ። ከ ፲፱፻፷፪ ዓ/ም እስከ ፲፱፻፷፰ ዓ/ም ድረስ በኒው ዮርክ ዩኒቨርሲቲ፣ ‘ክዊንስ ኮሌጅ’ እና በማሳቹሴትስ ብራንዲስ ዩኒቨርሲቲ በረዳት ፕሮፌሶርነት ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ለአሥራ ዘጠኝ ዓመታት በፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ፤ መጀመሪያ በፕሮፌሶርነትና በኋላም የዩኒቨርሲቲው “የጥቁር አሜሪካውያን የባህል ማዕከል” ዲሬክቶር በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል። በተጨማሪም የዶ/ር መላኩ በያን የአዕምሮ ጥንሥስ የነበረውን “የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናትና ምርምር ድርጅት” [1] ዳይሬክቶር በመሆን አገልግለዋል።


ፕሮፌሶር አሸናፊ ከመጀመሪያ ሚስታቸው ወይዘሮ ዕሌኒ ገብረመስቀል ጋር ያፈሯቸው ኒና እና ሰናይት የተባሉ የሁለት ሴት ልጆች አባት ሲሆኑ ሰናይት አሸናፊ በአሜሪካ የታወቀች የትዕይንተ-መስኮት ተዋናይ ናት። ሦስተኛ ልጃቸው ያሬድ አሸናፊ ደግሞ ከአሜሪካዊታ ሁለተኛ ሚስታቸው የተወለደ ነው።

የሕይወት ፍጻሜ ለማስተካከል

ፕሮፌሶር አሸናፊ ከበደ የ፷ኛ የልደት በዓላቸው ዕለት በመኖሪያ ቤታቸው ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ሞተው የተገኙ ሲሆን፤ ምናልባት የራሳቸውን ሕይወት ሳያጠፉ እንዳልቀሩ ብዙዎች ይገምታሉ።

አቶ አበራ ሞልቶት የተባሉት ወዳጃቸው ለኢትዮጵያ ቴለቪዥን ቅንጅት በሰጡት ቃለ-ምልልስ ላይ ከዕለተ ሞታቸው በፊት ጽፈውላቸው እንደነበረና ደብዳቤውንም በመጥቀስ፦ «ጋሽ አበራ፤ ስለዚህ ወረቀት ምን ትላለህ? ይህ አዲሱ ሙከራዬ ነው። ግን እንደራዕይ የሚታየኝ ከመጪው ሐምሌ በፊት ወደሌላ አኅጉር እሄዳለሁ። ሞቼ፣ ሥጋዬን ትቼ ከዚህ ወደኒርቫና እሸጋገራለሁ።» እንደሚል አስረድተዋል።

ዘመዳቸው አቶ በቀለ አሳምነው ደግሞ በዚሁ የቴሌቪዥን ቅንብር ላይ ስለዚህ ጉዳይ ሲያብራሩ፦ «“ባባቱ በኩል ታናሽ ወንድም አለው፤ ታዲያ አሸናፊ ወንድሙ ጋ ደውሎ “ከሣምንት በኋላ የለሁም…. ለሰው ልጅ ከስልሳ ዓመት በላይ መኖር ምንድነው ጥቅሙ?» ብሎት ነበር ይሉና ፖሊሶች ከምናየው ሁኔታ የራስን ነፍስ የማጥፋት ድርጊት ይመስላል ማለታቸውን ገልጸዋል።

ፕሮፌሶር አሸናፊ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት ከተቀበሉት ሽልማት ባሻገር የሱዳንን የዳንስ እና የድራማ ኢንስቲቱተ በማቋቋማቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሳይንስና የባሕል ድርጅት ሽልማትም ተቀብለዋል።

ድርሰቶች ለማስተካከል

ፕሮፌሶር አሸናፊ ከሙዚቃ ድርሰቶቻቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂነትና ተወዳጅነትን ያተረፈው ‘እረኛው ባለዋሽንት’ ብቻ ሳይሆን ከሌሎቹም አንዳንዱን ለመጥቀስ፦ ‘ሰላም ለኢትዮጵያ’፤ ‘የአገራችን ሕይወት’፤ ‘የተማሪ ፍቅር’፤ ‘እሳት እራት’፤ ‘ኮቱሬዥያ’ እና ‘ኒርቫኒክ ፋንታሲ’ የሚባሉት ድርሰቶች የሚጠቀሱ ናቸው። በሥነ-ጽሑፍ ረገድ ደግሞ በተማሪነታቸው ዘመን በ፲፱፻፶፮ ዓ/ም የደረሱት እና ያሳተሙት “ንስሐ” ወይም Confessions የተባለው መጽሐፍ እና “የሙዚቃ ሰዋሰው” እንዲሁም በርካታ የጥናትና ምርምር ድርሰቶች ይጠቀሳሉ።

ማጣቀሻዎች ለማስተካከል

  1. ^ Cynthia Tse Kimberlin (እ.አ.አ. 1999)፣ ገጽ 322
  2. ^ Olsen (5aug98)
  3. ^ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፤ “የሙዚቃ ሰዎችና ሥራዎቻቸው”

ዋቢ ምንጮች ለማስተካከል

  • Kimberlin, Cynthia Tse; The Scholarship and Art of Ashenafi Kebede (1938-1998); Ethnomusicology Vol. 43, No. 2 (Spring - Summer, 1999), pp. 322-334; Published by: University of Illinois Press; http://www.jstor.org/stable/852737
  • የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናትና ምርምር ድርጅት [2]