ሻሩሔን (ዕብራይስጥ /ሻሩኸን/፣ ግብጽኛ /ሻርኻን/) በከነዓን ደቡብ በጋዛ አካባቢ የነበረ ከተማ ነው። በመጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 19:6 መሠረት ለነገደ ስምዖን ከተሠጡት ቦታዎች መካከል አንዱ ነበር።

በ1548 ዓክልበ. ግድም የግብጽ ደቡብ ፈርዖን 1 አሕሞስ አሸንፎ ሂክሶስ የተባሉት አሞራውያን ወገን ከግብጽ ሸሽተው ሻሩሔንን ያዙ። 1 አሕሞስ ግን በሥራዊቱ ሻሩሔንን ለ6 ዓመታት ከብቦ፣ በመጨረሻ በ1542 ዓክልበ. አምባው ለግብጽ ወደቀ። ዘመቻው በጦር አለቃው አሕሞስ ወልደ አባና ጽሑፍ ይገለጻል።

የሻሩሔን ሥፍራ በእርግጥ ባይታወቅም፣ በጋዛ አካባቢ ሦስት ልዩ ልዩ ዘመናዊ ሥነ ቅርስ ሥፍራዎች ይግባኝ ጥለዋል።