እቴጌ ሰብለ ወንጌል (1482- 1560ዓ.ም.) የዓፄ ልብነ ድንግል ሚስት ስትሆን ከንግስት እሌኒ ሞት በሁዋላ በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የነበራት ሴት መሪ ናት። የነበረችበት ዘመን፣ የአህመድ ግራኝ ጦር በቱርክ ጠመንጃ አንጋቢወች ታግዞ ብዙ የኢትዮጵያን ክፍል የተቆጣጠረበት ወቅት ነበር። በዚህ የጦርነት ዘመን የመጀምሪያ ልጇ ፍቅጦር ሲገደል አራተኛው ልጇ ( የወደፊቱ አጼ ሚናስ ) በምርኮ ወደ የመን ተግዞ ነበር። ዓፄ ልበነ ድንግል በ1540 ዓ.ም. በደብረ ዳሞ በህመም ከሞተ በኋላ ሳይቀር እጅ ሳትሰጥ ከተራራው ምሽግ ወርዳ የፖርቱጋልን ጦር በመቀላቀል የአዳልን ጦር እስከመጨረሻው ታግላ አታግላለች።

የእቴጌ ሰብለ ወንጌል መታሰቢያ ቴምብር

ባሏ 1540 ሲሞት ሁለተኛ ልጇ አጼ ገላውዲወስ ንጉስ ሆነ። ይህ ልጇ በደቡብ ክፍል ውጊያ ከፍቶ በመታገል ላይ እያለ በክሪስታቮ ደጋማ የሚመራው የፖርቹጋል ጦር ምጽዋ ላይ አረፈ። ይህ የሆነው እቴ ሰብለ ወንጌል ደብረ ዳሞ ተራራ ላይ ለአንድ አመት እጅ ሳትሰጥ በአህመድ ግራኝ ተከባ ከተቀመጠች በኋላ ነበር። ከተራራው ምሽጓ ላይ ሆና ከፖርቹጋሎቹ ጋር በመደራደር ወጃጅ መሆናቸውን ካረጋገጠች በኋላ ከፖርቹጋሎቹ የጦር ቀጠና ጋር ተቀላቀለች። ከበቅሎዋ ላይ ቁጭ ብላም የፖርቹጋሎቹ 400 ውታደሮች በፊቷ ሲያልፉ ትመረምር እንደነበር ታሪክ ያትታል።

የንግስቲቷን ድጋፍ ተከትሎ የአካባቢው ህዝብ ለፖርቹጋሎቹ ምግብና እርዳታ እንዳደረገ፤ ብዙወችም ይህን ሰራዊት እንደተቀላቀሉ ይነገራል። ቁስለኛውን በማከም፣ የለበሰችውንም ጥምጣም በመቅደድ ባንዴጅ በመስራት፣ ለሞቱትም በማልቀስ በጦር ውሎው ሁሉ ተሳታፊ ነበረች። በ1543 የክሪስታቮና ከደቡብ በኩል የመጣው የገላውዲወስ ሃይሎች ተገናኝተው በማበር አህመድ ግራኝን አሸነፍው ገደሉት። የግራኝ ሚስት ባቲ ድል ወምበሬ ብታመልጥም ልጇ መሃመድ ግን ተማርኮ ነበር።

በዚህ ጊዜ የመን የተጋዘውን የልጇን የሚናስን ጉዳይ ለመፈታት ከድል ወምበሬ ጋር በመልዕክተኛ ለመወያየት ችላለች። ሚናስ በዚህ ጊዜ ለቱርኩ መሪ ሱልጣን ሱሊማን በየመን ተልኮ ነበር። ይህ የተጋዘው ልጇ በድርድሩ መሳካት ምክንያት አይባ ላይ ከእናቱ ከሰብለ ወንጌል ሊቀላቀል ችሏል።

ከ6 አመት ጦርነት በኋላ ገላውዲወስ ተገደለና ሚናስ ስልጣን ላይ ወጣ። ለሚቀጥሉት 4 አመታት፣ እንደቀደመችው ንግስት እሌኒ በመንግስቱ ውስጥ ከፍተኛ ተሰሚነትን አገኘች። ቀጥሎም በካቶሊክ እና በኦርቶዶክስ ሃይማኖት መካከል በተነሳው ሽኩቻ የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን በመደገፍ በጽናት ቆማለች። ይሁንና በዚህ ምክንያት በተነሳው ጸብ የፖርቹጋል ካቶሊኮች ሊገደሉ ሲሉ በማማለድ ስራ ጉዳት እንዳይደርስባቸው አድርጋለች። ቤርሙዴዝ የተባለው ታውቂው የፖርቹጋል ተጓዥም ንጉሱን ገላውዲወስን በማናደዱ ከመገደል የተረፈው በሰብለ ወንጌል ተራዳኢነት ነበር። የስፔኑ ጀስዊት ፓትሪያርክ ኦቨዶም ከሞት የተረፈው በንግስቲቱ ምክንያት ነበር። ሠርፀ ድንግልን ወደስልጣን እንዲወጣም ከጦረኞቹ በላይ ያገዘችው እናት ንግስት ሰብለ ወንጌል ነበረች። ይህ ምርጫዋ የተሳካ ነበር ምክንያቱም ሰርጸ ድንግል ለ34 አመት ሲገዛ አገሪቱን በመከላከል ወደ ሰላም አሸጋግሯል። [1]

ሰብለ ወንጌል በአጼሠርፀ ድንግል ዘመን፣ በ1560 ዓ.ም. አመድ በር በተባለ ቦታ አረፈች።

አጼ ልብነ ድንግል የራሱንና የሰብለ ወንጌልን ምስሎች የክሪት ሠዓሊ በመቅጥር ካሳለ በኋላ ግብጽ ወደ ሚገኘው ቅዱስ አትናቲዮስ ገዳም (st antony monastery) እንዳስላከው ተመዝግቦ ይገኛል [2]። የአጼ ልብነ ድንግል ምስል ከዚሁ ገዳም ይመነጫል።

ማጣቀሻወች ለማስተካከል

  1. ^ ሪታ ፓንክኸርስት http://www.oneworldmagazine.org/focus/etiopia/women2.html Archived ኦገስት 8, 2015 at the Wayback Machine
  2. ^ Abstracts of papers - Byzantine Studies Conference, Volumes 16-19 (1990)
 
የንግስት ሰብለ ወንጌል ባል የነበሩት አጼ ልብነ ድንግል